የአቡበከር ናስር ወደ ታላቅነት ጉዞ

በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ እግርኳስን የሚከታል ሁሉ ቅድሚያ ሊጠራው የሚችለው የተጫዋች ስም ግልፅ ነው። አቡበከር ናስር! ከእድሜው የቀደመው ትንሹ ልጅ ዘንድሮ እጅግ በአስደናቂ መንገድ ላይ ይገኛል። እኛም የኢትዮጵያ ቡናውን አጥቂ ከሰፈር ሜዳ እስከ ዘመኑ ኮከብነት ያለፈበትን የእግርኳስ ጉዞ እንዲህ ቃኝተነዋል።

ትውልድ እና እድገቱ በመዲናችን አዲስ አበባ በተለምዶ ሾላ ገበያ ተብሎ የሚጠራ አካባቢ ነው። በአካባቢው የሚገኘውና በአዲስ አበባ ለምልክት ከቀሩ የመጫወቻ ክፍት ቦታዎች አንዱ የሆነው “ጉቶ ሜዳ” ኳስን ማንከባለል የጀመረበት፣ ከመጫወት በዘለለ ብስክሌት ለማሽከርከር ለሚመጡ ወጣቶች በማከራየት ገቢ ለማግኘት የሚጥርበት ነበር።

በሰፈር ከእኩዮቹ ጋር ከመጫወት አልፎ በታዳጊ ቡድኖች የመቀላቀል ዕድል ያገኘው በፍጥነት ነበር። በ2006 ነገ ተስፋ በሚባል በአሰልጣኝ ደግፌ በሚመራ ቡድን ውስጥ ታቅፎ መሥራት ጀመረ። በአቡበከር እድገት ትልቅ ሚና ከተጫወቱት ግለሰቦች አንዱ የሆነው አሰልጣኝ ደግፌ የታዳጊው አቡበከር ሁኔታን ትናንት የሆነ ያህል ያስታውሰዋል። “አቡበከርን ማየት የጀመርኩት የካቲት ትምህርት ቤት ከ9–13 ዓመት ታዳጊዎች የፉትሳል ውድድር ላይ ነው። በ2004 እና 2005 አካባቢ ማለት ነው። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እርሱ ወደሚገኝባቸው ሜዳዎች ሁሉ ምግብ ሳልበላ እየተከተልኩ አየው ነበር። በሚገርም ሁኔታ ከልምምድ ይልቅ ጨዋታዎችን የሚወድ ነበር። ብዙ ልምምድ ላይ ትኩረት አያደርግም ነበር። የውድድር ሰው ነው። አብረውት ከሚጫወቱ ተጫዋቾች ሁሉ እርሱ ላይ የተለየ አቅም አይበት ነበር። አብረውት እንደ ቡድን የሚጫወቱት እምብዛም ኳስ ላይ ያላቸው መረዳት እምብዛም የነበሩ ‘የማይችሉ’ ልጆች ነበሩ። ውድድር ላይ እርሱ ከእነርሱ የተሻለ ስለነበረ ይዘውት እንዲጫወትላቸው ይመጡ የነበረ ይመስለኛል። በዚህ መሐል እርሱ ጎልቶ ይወጣ ነበር። አቅሙ ከፍ ያለ ስለ እግርኳስ የአዕምሮ መረዳቱ ከፍተኛ የሆነ በጣም ተስዕጦ ያለው ልጅ ነበር። እርሱን ሳየው ሰውነቴን ሁሉ ውርር ያደርገኝ ነበር። ገና ብዙ ነገር ከእርሱ እጠብቃለሁ።”

የአቡበከር የጨዋታ ዝግጁነት ከልጅነቱም የነበረ እንደሆነ የሚናገረው አሰልጣኝ ደግፌ በወቅቱ ያለውን አቅም እንዳያወጣ ሊያግዱ የሚችሉ ሁኔታዎችም እንደነበሩም ያስታውሳል። ” የሆነ ሰዓት ድንገት መጫወት አቆሞ ጥፍት ይልና እንደገና በራሱ ሰዓት በድጋሚ ይጫወት ነበር። በዚህ ምክንያቶች በፍጥነት የታዳጊ ቡድኔ ውስጥ እንዳልቀላቅለው ፈተና ሆኖብኝ ነበር። በትምህርት ምክንያት ሊሆን ይችላል፤ አልያም በሳምንት ሦስት ወይም አራት ቀን በልምምድ ማድረግ ስላለበት ከሚኖርበት ሠፈር ወደ የካቲት 19 ሜዳ መጥቶ ለመሥራት የትራንስፖርት ችግር የሚያጋጥመው ይመስለኛል። ያም ሆኖ ታላቅ ወንድሙ ጅብሪል እኔ ጋር ይሰለጥን ስለነበረ አቡበከር እኔ ጋር እንዲሰራ እጠይቀው ነበር። መጨረሻም 2006 የነገ ተስፋ የሚባል የኔ ቡድን ውስጥ ገብቶ ይሰራ ጀመረ።” ይላል።

አቡበከር በነገ ተስፋ ቡድን ብዙም ሳይቆይ ፈለቀ በሚባል ግለሰብ አማካኝነት ታዳጊዎችን በማፍራት ጥሩ ስም ወዳለው ኒያላ ታዳጊ ቡድን ሙከራ እንዲያደርግ እድል ተመቻቸለት። ሆኖም የቡድኑ የልምምድ ሜዳ ከመኖርያ ቤቱ መራቅ እክል መፍጠሩ አልቀረም። ለጥቂት ጊዜ እስከ ቃሊቲ እየተጓዘ ልምምድ ማድረጉ ሲከብደውም ለማቆም ተገደደ። የዚህ ጊዜ ነበር የእግርኳስ ህይወቱን መልክ ወዳስያዘለት ሐረር ሲቲ ያመራው። ክለቡ አዲስ አበባ መቀመጫውን አድርጎ የሚወዳደር ታዳጊ ቡድን ለማቋቋም በ2007 ምልመላ ሲያካሂድ የታዳጊ ቡድኑ ምክትል አሰልጣኝ ደግፌ ለቡድኑ እንዲጫወት አደረገውና በድጋሚ ተገናኙ። በቀድሞው አጥቂ እስማኤል አቡበከር በሚመራው ሐረር ሲቲ እንደተጫዋች መገራት እና መጎልበትም ጀመረ።

አቡበከር እንደታዳጊ የመጫወት ፍላጎቱ ከፍተኛ ነበር። በአካባቢው የኳስ መጫወቻ ሜዳ ከመኖሩ እና ቤተሰቡም ከኳስ ጋር ጥሩ ቁርኝት ያለው እንደመሆኑ ለኳስ የነበረው ፍቅር “ለጉድ” ነበር። ይህ የኳስ ፍቅሩም በሐረር ሲቲ ይበልጥ ራሱን እንዲገልፅ እና እንዲያብብ ረዳው። በቡድኑ አሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር ከፍተኛ እገዛ እዚህ እንደደረሰ የሚናገረው አቡበከር ወደ ልምምድ ለመሄድ የትራንስፖርት ለመክፈል ሲቸገር እንኳ ከኪሱ እያወጣ እንደሚሰጠው በአንድ ወቅት ለድገፃችን ተናግሯል።
በቡድኑ ውስጥ እድገት ቢያሳይም ከሌሎች የተለየ የአዕምሮ ብስለት የነበረው መሆኑ ጎልቶ እንዲወጣ ሳያደርገው አልቀረም። ” ከሌሎች ተጫዋቾች የተለየ የሚያደርገውና በጨዋታ መሀል እርሱ ጎልቶ እንዲወጣ የሚያስችለው ኳስ አያያዝ፣ ኳስ አገፋፍ፣ ለጓደኛ የማቀበል ዕይታ፣ የቦታ አጠቃቀሙ፣ እያሰበ መጫወቱ በስልጠና ያልዳበረ የተፈጥሮ ችሎታ እንደነበረ ያስታውቅ ነበር። አቡበከር ጎልቶ መውጣት የነበረበት አሁን ሳይሆን ገና ከልጅነቱ ዕድሜ ጀምሮ መሆን ነበረበት። ከሲ ቡድን ነተስቶ ነው በቀጥታ ዋናው ቡድን መጫወት የቻለው። ይህ የአዕምሮ ብስለቱን ያሳያል” ይላል።

ዓይን ገላጩ ዕድል

በሐረር ሲቲ መጫወቱን የቀጠለው አቡበከር በ17 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በማድረግ ለቀጣይ ፈተና ራሱን አዘጋጀ፤ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን። ለቁጥር የሚታክቱ በርካታ ተጫዋቾችን ሞክረው የመጨረሻ ዝርዝር ውስጥ ያከተቱት አሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ ለሠሩት ድንቅ ቡድን አቡበከርን ፊት አውራሪ እንዲሆን ሲመርጡት እርግጠኝነት ይታይበቸው ነበር።

” ሲጀመር ልጁ ቀድሞም በሳል ነው። በተፈጥሮ ሰውነቱ ደቃቃ እና ቀጭን የነበረ በመሆኑ ‘እንዴት ትመርጠዋለህ? የምንጫወተው ከአፍሪካ ቡድኖች ጋር ነው’ ይሉ ነበር። ሆኖም አቡበከር የእግርኳስ አዕምሮ እንዳለው የሚታይ ነገር ነበረው። የአዕምሮ ምጥቀቱ ከፍተኛ ነበር። ዘመኑ የሚፈልገው ነገር ስለነበረው መርጨዋለው። ቡድኑንም በወቅቱ ውጤታማ አድርጓል። እኛ ጋር በወጣቶች ላይ ብዙ አለመሰራቱ ነው እንጂ ብዙ ልጆች እንዳሉ አቡበከር አንድ ማሳያ ነው። በእግርኳስ አካላዊ ቁመና ብቻ ሳይሆን አዕምሮም ትልቅ ቦታ እንዳለው ጥሩ ምሳሌ መሆን የሚችል ልጅ ነው።” ሲሉ የምርጫቸውን ትክክለኝነት አስረድተዋል።

ከረጅም ዓመት ዕቅድ ይልቅ እንደነገሩ ተጫዋቾች ተሰባስበው ቡድን በመመስረት ወደ ማጣርያ ውድድር መቅረብ በተለመደበት የኢትዮጵያ እግርኳስ አሰልጣኝ አጥናፉ በፍጥነት ቡድን አዋቅረው ለ17 ዓመት በታች ውድድር ለማለፍ በሚደረገው ማጣርያ ጠንካራዋ ግብፅን ለመግጠም ተዘጋጁ። አሁን በፕሪምየር ሊጉ እየደመቁ የሚገኙት አቡበከር ናስር፣ ሚኪያስ መኮንን፣ ሳሙኤል ተስፋዬ፣ ጫላ ተሺታ፣ ረመዳን የሱፍ፣ ፋሲል ገብረሚካኤል እና እዮብ ዓለማየሁን የመሳሰሉ ተጫዋቾችን ያቀፈው ቡድን ለመጀመርያ ጨዋታ ወደ ግብፅ ሲያመራ ለዓመታት ከግብፅ ጋር መጫወት አንገት ከመድፋት ጋር ተቆራኝቶ ኖሮ ጨዋታውን “ጉዳዬ” ብሎ የተከታተለው አልነበረም። ሆኖም ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆኖ አቡበከር እና ጓደኞቹ የግብፅ መገናኛ ብዙሀንን የአድናቆት ቃላት እንዲያወጡ ያስገደደ ምሽት አሳለፉ። ሦስት ለአንድ ባሸነፉበት ጨዋታ ከመመራት ተነስተው በጫላ የመጀመርያ፣ በአቡበከር ሁለተኛ እንዲሁም የሚኪያስ እጅግ አስደናቂ ሦስተኛ ጎል ድል አድርገው ተመለሱ።

ከአስደናቂው ምሽት በኋላ ትኩረቶች ሁሉ በአብሮ-አደጉ ሚኪያስ መኮንን ላይ አረፉ። ሦስት የግብፅ ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂውን ሁሉ አልፎ ድንቅ ግብ ማስቆጠሩ ባለ ክህሎቱ የመስመር ተጫዋች ላይ ዓይን እንዲበዛበት አደረገ። የመልሱ ጨዋታ ድሬዳዋ ላይ ሲደረግ የደጋፊን ትኩረት ማግኘት የቻሉት ታዳጊዎች ጫና እንደሚሰማቸው ግልፅ ነበር። ግብፆችም ካይሮ ላይ ጉድ የሰሯቸው ጫላ እና ሚኪያስ ላይ ክትትል እንደሚያደርጉ የገባቸው አሰልጣኝ አጥናፉ ትልቁን ኃላፊነት ለአቡበከር ሰጥተው ጨዋታውን ጀመሩ። እሱም አላሳፈራቸውም ሁለት ጎል አስቆጥሮ ኢትዮጵያ በአጠቃላይ አምስት ለሁለት ድል ወደ ቀጣይ ዙር አለፈች።

የኢትዮጵያ ቀጣይ ተጋጣሚ ማሊ ነበረች። 2009 መጀመርያ ላይ የተደረገው ጨዋታ ለኢትዮጵያ እጅግ ፈታኝ የነበረ ሲሆን በድምር 4-1 ሽንፈት ከውድድሩ ወጣች። ሆኖም የተጫዋቾቹ ዕምቅ አቅም በሚገባ ከተያዘ የወደፊቱ ከዋክብት እንደሚሆኑ በሚገባ ያሳዩበት ነበር። በዛ ዓመት ከሐረር ሲቲ ታዳጊ ቡድን ጋር ሁለተኛ ዓመቱን የሳለፈው አቡበከርም ቀጣይ ምዕራፍ ከፊቱ ይጠብቀው ነበር።

ጉዞ ወደ ኢትዮጵያ ቡና

የወንድማማች ያህል የማይነጣጠሉት አብሮ-አደጎቹ አቡበከር እና ሚኪያስ ከሐረር ሲቲ የሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ቡና አመሩ። ሆኖም በወቅቱ ሁለቱ ተጫዋቾች ወደ ቡና የተዛወሩበት መንገድ አጨቃጫቂ የነበረ በመሆኑ እስከ ዓመቱ አጋማሽ ድረስ ውዝግቡ ቀጥሎ ነበር።

ለሁለቱ ወደ ቡና መዘዋወር ትልቁን ሚና የተጫወተው የወቅቱ የቡና የ17 ዓመት በታች ቡድን አሰልጣኝ ታዲዮስ የወቅቱን ውዝግብ እና የተፈታበትን መንገድ እንዲህ ያስታውሳል።

” አቡበከር እና ሚኪያስ በሐረር ሲቲ ቀሪ ኮንትራት ነበራቸው። እኛ ደግሞ ምንም እንኳን ኮንትራት ቢኖራቸውም ሐረር ሲቲ በመፍረሱ እና የሁለት ወር ደሞዝ ስላልተከፈላቸው ወደፈለጉበት ክለብ መሄድ ይችላሉ ብለን ክርክር ይዘን ነበር። ሆኖም በኋላ የፈረሰውን ክለብ በድጋሚ አቋቁመው በማስቀጠላቸው ልጆቹን ላለማጣት ሲባል ሰልሳ፤ ስልሳ ሺህ ብር ለሁለቱም ውል ማፍረሻ ከፍለን አስገባናቸው። በነገራችን ላይ ልጆቹን መከታተል የጀመርኩት ከ17 ዓመት በታች ከብሔራዊ ቡድን በፊት ነው። በብሔራዊ ቡድን ጥሩ መሆን ሲችሉ ፈላጊ ክለቦች ስለበዙ ድሬዳዋ ድረስ በመሄድ አሳምኜያቸው ባልፀደቀ ውል አስቀድሜ አስፈርሜያቸው ነበር።” ይላል አሁን አቡበከር ያለበትን ደረጃ ሲመለከት “እንኳንም ይህን አደረግኩ” የሚለው ታዲዮስ።

በመጨረሻም የሁለቱ ወገኖች ልዩነት ተፈታና አቡበከር ከጓደኛው ጋር ከልጅነቱ ጀምሮ ሲደግፈውና ማልያውን ለመልበስ ሲመኘው የነበረው ኢትዮጵያ ቡናን ተቀላቀለ። ” ኢትዮዽያ ቡና የልጅነት ህልሜ ነው፡፡ ለቡና መጫወትን አስብ ነበር። የቡናም ደጋፊ ነበርኩ፡፡ ካታንጋ እየገባሁ ከሰፈር ልጆች ጋር ጨዋታ እመለከት ነበር። የ17 ዓመት በታች ቡድን አሰልጣኙ ታዲዮስ ነው ወደ ቡና እንድገባ ያመጣኝ፡፡ ከሐረር ሲቲ ወደ ቡና ከመዘዋወሬ ጋር ተያይዞ ክርክሮች ነበሩ። ችግሩ በውይይት ተፈትቶ በመጨረሻም ልገባ ችያለው፡፡” ሲል በወቅቱ ለሶከር ኢትዮጵያ የተናገረው አቡበከር ምንም እንኳ ከመስከረም ወር 2009 ጀምሮ ከዋናው ቡድን ጋር ሲሰራ ቢቆይም የመጫወት ፈቃድ ያገኘው መጋቢት ወር መጀመርያ ላይ ነው።

መጋቢት 2009 የአቡበከር እና የቡና ትስስር መጥበቅ የጀመረበት ወቅት ነበር። ችግሮች ዕልባት ካገኙ በኋላ የዋናው ቡድን አካል የሆነው ትንሹ ልጅ በፍጥነት ነበር ማስገረም የጀመረው።

መጋቢት 22 ቀን 2009 በሀዋሳ ዓለምአቀፍ ስታዲየም ለዋንጫ እየተፎካከረ የሚገኘው ሲዳማ ቡና በወሳኙ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናግዳል። ደመቅ ያለ ድባብ በነበረበት ጨዋታ ላይ ትንሹ አቡበከር ትልቁን 10 ቁጥር መለያ ለብሶ በመጀመርያ ተሰላፊነት ወደ ሜዳ ገባ። ቀድሞውንም በየትኛውም አጋጣሚ ጨዋታ ለማድረግ እና ኃላፊነት ለመውሰድ ያለው ዝግጁነት የተመሰከረለት አቡበከር ከፈርጣማዎቹ የሲዳማ ቡና ተከላካዮች ጋር ሲፋለም ውሎ በሊጉ ላይ ስሙን አስፃፈ። በአርባ ሦስተኛው ደቂቃ ላይ “እንደ አርዓያ የምመለከተው” ከሚለው መስዑድ መሐመድ ከማዕዘን የተሻማለትን ኳስ በግንባር በመግጨት ቡድኑን አቻ አደረገ። የኋላ ኋላ ቡና ለጠንካራው ሲዳማ ቡና እጅ ቢሰጥም ታዳጊው በኢትዮጵያ እግርኳስ አዲሱ የመነጋገርያ ርዕስ መሆን ቻለ።

የነገሮች በፍጥነት መቀያየር አቡበከርን ብዙም ጫና ውስጥ የከተተ አልነበረም። ገና ከጅምሩ የመጡለት የአድናቆት ቃላትም አላታለሉትም። በወቅቱ ከጨዋታው በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው ቃል በጨዋታው ካሳየው አቋም ይልቅ የወደፊቱ ላይ ማተኮርን መርጦ ነበር። “በጣም ነው የምጠነቀቀው፡፡ ገና የመጀመርያ ጨዋታዬ ነው፡፡ ገና ብዙ ይቀረኛል፡፡ ወደ ፊት ከኢትዮዽያ ቡና ጋር ረጅም ጉዞ መጓዝ እፈልጋለሁ፡፡ በዋናው ብሔራዊ ቡድን መጫወት እና ከኢትዮጵያ ወጥቶ የመጫወት ፍላጎቱ ስላለኝ አድናቆቱ አያዘናጋኝም፡፡”

ከድንቅ ጅማሬው በኋላ አቡበከር በቀሪዎቹ ስምንት ሳምንታት ጥቂት ጨዋታዎችን ተጫወተና በሦስት ጎሎች የውድድር ዓመቱን አጠናቀቀ። ይህ ገና በአስራዎቹ ዕድሜ ክልል ለሚገኝ ተጫዋች ጥሩ ጅምር ነበር። ቀጣዩ የውድድር ዓመትን በትልቅ ተነሳሽነት እንዲጀምር የሚያደርግም ነበር።

ሆኖም የ2010 የውድድር ዓመት ለአቡበከር ቀላል አልነበረም። በሰርቢያዊያኑ ድራጋን ፖፓዲች እና ኮስታዲን ፓፒች ስር የመሰለፍ እድል ተነፈገው። የአዳዲስ አጥቂዎች ወደ ቡድኑ መካተትም ባለ ብሩህ ተስፋውን ታዳጊ ምሬት ውስጥ የከተተ ነበር። “ዘንድሮ ከዐምናው (2008) የተሻለ ነገር ነበር የጠበቅኩት። ሆኖም አዳዲስ ተጨዋቾች መጥተዋል። ከፍለህ በከፍተኛ ብር ካመጣሀቸው ደግሞ አሰልጣኞች ለእነሱ ነው ቅድሚያ የሚሰጡት።” ሲል በወቅቱ ለድረገፃችን የተናገረው አቡበከር የመጫወት እድል የሚያገኘው በጥቂት አጋጣሚዎች በተለይም ቡድኑ እየተመራ በነበረበት ወቅት በመሆኑ ራሱን ለማሳየት ፈተና እንደሆነበት ተናገረ።

በ2010 አጋማሽ ከፈረንሳዊው አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ወደ ቡድኑ መምጣት በኋላ ተነፍጎት የቆየው ዕድል እየተፈጠረ መጣ። ሳሙኤል ሳኑሚን ጨምሮ በቆይታቸው ስኬታማ ያልሆኑ የውጪ ዜጋ አጥቂዎችን በስብስቡ ባካተተው ቡድን የሚያገኘውን የጨዋታ ጊዜ በአግባቡ በመጠቀም ወደ ዋና ተሰላፊነት መንደርደር የጀመረውም በዛ የውድድር ዘመን ነበር። መጋቢት ወር ላይ ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ እየተዘጋጀ ለነበረው ቡድን በተጠራበት ወቅት ኢትዮጵያ ቡና በጨዋታዎች ላይ ተጠቅሞ በፍጥነት ወደ ዝግጅት እንደሚመልሰው በደብዳቤ መጠየቁም ቡድኑ በተጫዋቹ ላይ ምን ያህል ዕምነት እያሳደረ እንደመጣ የሚያሳይ ነበር። በቀሪው የውድድር ዓመትም በሁሉም ውድድር አምስት ጎሎችን አስቆጥሮ በዳግም በተስፋ ዓመቱን አገባደደ።

በቀጣዩ ዓመት ይበልጥ በቡድን ስብስቡ የተሻለ ስፍራ እያገኘ የመጣው አቡበከር ይበልጥ በራስ መተማመኑን ከፍ የሚያደርግ ውሳኔ በክለቡ ተወሰነለት። ቡድኑን ሲቀላቀል ሲያገኘው የነበረው ደሞዝ እንዲጨምር ተደርጎ ከቡድን ጓደኞቹ ሚኪያስ እና ኃይሌ ገብረተንሳይ ጋር አዲስ የተሻሻለ ኮንትራት ፈረመ። በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የውድድሩ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን እና በፍፃሜው. ሁለት ጎል አስቆጥሮ ዋንጫ በማንሳት ዓመቱን የጀመረው አጥቂ በርካታ ጨዋታ ባደረገበት በዚህ የውድድር ዓመት ቡድኑ አስደሳች ውጤት ይዞ ማጠናቀቅ ባይችልም በግሉ አስራ አንድ የፕሪምየር ሊግ ጎሎችን በማስቆጠር ዕምነት ሲጣልበት ምን ማድረግ የሚችል ተጫዋች እንደሆነ በሚገባ አሳይቷል።

ቀጣዩ የውድድር ዓመት ስለ መደበኛ ተሰላፊነት የሚጨነቅበት ጊዜ አልነበረም። ይልቁንም ብዙ ያነጋገረው ካሣዬ አራጌ ከረጅም ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ቡና መመለስን ተከትሎ የአቡበከር እድገት ከምን ይደርሳል የሚለው ነበር። ክለቡ የውጪ ተጫዋች ላለማስፈረም መወሰኑ በተለያዩ የውጪ ዜጋዎች ቦታው ተይዞ እድገቱን ገድቦበት ለቆየው አቡበከር መልካም አጋጣሚ ነበር። የተጫዋቾችን አቅም በማውጣት የማይታሙት አስልጣኝ ካሣዬ በመጀመርያዎቹ ሳምንታት ለአቡበከር ትክክለኛውን የመጫወቻ ቦታ ለመወሰን ብሎም ከሚመርጡት አጨዋወት ጋር ለማዋሀድ ጊዜ እንዳስፈለጋቸው ግልፅ ነበር። ከግራ መስመር በመነሳት እንዲሁም በመሐል አጥቂነት እንዲጀምር የተደረገው አቡበከር ቀዝቀዝ ያለ አጀማመር ቢያርግም ቀስ በቀስ ማንነቱን እያገኘ በመምጣት ጎሎችን ማስቆጠር ጀመረ። የውድድር ዓመቱ በኮሮና ምክንያት ሲቋረጥም ስምንት ጎሎችን አስቆጥሮ በቡና መለያ የመጀመርያ ሐት ትሪኩን ሰርቶ ነበር ወደ ረጅሙ እረፍት ያመራው።

የቡና የወደፊት መልኮች

በቡናማ እና ቢጫው መለያ በርካታ ድንቅ ተጫዋቾች ተጫውተው አልፈዋል። ውለታ የዋለላቸው ተጫዋችን በልባቸው ለማንገሥ በማይሳሱት ደጋፊዎች የነገሡ እልፍ ባለ ታሪኮችም አሉ። ከነዚህ መካከል በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሰው አሸናፊ በጋሻው የዕውቅና መርሐ ግብር ሲዘጋጀለት የአሁኑ ትውልድን ወክለው በስፍራው የተገኙት ጓኛሞቹ አቡበከር እና ሚኪያስ ነበሩ። ባደረጉት ንግግርም “ሌሎቹ አሸናፊ በጋሻዎች” ለመሆን ዝግጁነታቸውን ገልፀዋል።

የሁለቱ ቃል በቃልነት ብቻ አላለፈም ከቀናት የኋላ ወደተግባር ተቀየረ። ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በቡና ቤት ለመቆየት ውላቸውን በማራዘም የወደፊቱ ቡና ማሳያ መስታውት መሆናቸውን አሳዩ።

ወደ ኮከብነት መሸጋገር

የዘንድሮ የውድድር ዘመን ላወቀበት እጅግ ወሳኝ ዓመት ነው። ራስን ለማሳየት እና ወደሻለ ምዕራፍ ለመሸጋገር ብሎም ራስን ለማስተዋወቅ የጨዋታዎች በቴሌቪዥን መተላለፍ ትልቅ ዕድል ነው። በአንድ ቦታ መደረጋቸው ትኩረትን ለመሰብሰብ እና የጉዞ ድካምን ለመቀነስ አመቺ ሆኗል። በዚህ ረገድ የአቡበከር ናስርን ያህል የተጠቀመበት እንደሌለ በድፍረት መናገር ይቻላል።

የውድድር ዓመቱን የጀመረው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዝግጅት እና የማጣርያ ጨዋታዎች ላይ ስብስቡን በመቀላቀል ነበር። አጥቂው የስምንት ወራት ረጅም ዕረፍቱ የተስማማው እንደማይመስል በሚያሳብቅ ሁኔታ በጉዳት የተወሰኑ የልምምድ እና የወዳጅነት ጨዋታዎች አለፉት። ቡድኑ ከኒጀር ጋር ለሚያርገው ጨዋታ የመኖሩ ጉዳይም አጠራጣሪ መልክ ይዞ ነበር። ሆኖም የኢትዮጵያን የውድድሩ እጣፈንታ በሚወስኑት ሁለቱ የማጣርያ ጨዋታዎች ላይ በመጀመርያ ተሰላፊነት መጫወት ቻለ።

ከብሔራዊ ቡድኑ መልስ የፕሪምየር ሊጉ መጋረጃ ተከፈተ። የአቡበከር የዝና እና የታላቅነት ጉዞም በከፍተኛ ፍጥነት መምዘግዘግ የጀመረው ገና በመጀመርያው የጨዋታ ሳምንት ነበር። ወልቂጤ ከተማን ገና በመጀመርያው አጋማሽ በሁለት ጎል ልዩነት መሪ እንዲሆኑ ያስቻሉ ሁለት ጎሎችን በስሙ አስመዘገበ። የመጨረሻ ሰዓት ጎሎች ሙሉ ሦስት ነጥብ አሳጥተውት አጀማመሩን ምሉዕ እንዳይሆን ያደረጉበት አቡበከር ከቀናት በኋላ በተደረገው ጨዋታ ልዩነት ፈጣሪነቱን ማሳየት የቻለበትን ቀን አሳለፈ። ቡድኑ ፋሲልን ለረጅም ደቂቃ በጎዶሎ የተጫዋች ቁጥር ገጥሞ ሲረታ ወሳኝ ጎል በፍፁም ቅጣት ምት ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ለሀብታሙ በማመቻቸት ድንቅ ዕለት አሳለፈ። ሆኖም ያ ጨዋታ ለአቡበከር ቀላል አልነበረም፤ ከህመም ጋር እየታገለ ጨዋታውን ሲያደርግ ቆይቶ በመጨረሻ ተቀይሮ ለመውጣት ተገደደ። በቀጣዩ የድሬዳዋ ጨዋታ ላይም ሳይጫወት ቀረ።

ትንሹ ልጅ ከጉዳቱ አገግሞ በአራተኛው ሳምንት ከሀዋሳ ጋር በተደረገው ጨዋታ ወደ ሜዳ ቢመለስም የተለመደ ተፅዕኖ መፍጠር ሳይችል ሽንፈት ያስተናገደው ቡድኑንም ሳይታደግ ከሜዳ ወጣ። ሆኖም ይህ ለብዙ ጊዜ የቀጠለ አልነበረም። በቀጣዩ ጨዋታ ሰበታን ሲያሸንፉ በሁለት ጎሎች ወደ ጎል አስቆጣሪነት ተመለሰና ከሀገሪቱ ተጠባቂ የደርቢ ጨዋታ በፊት በምርጥ አቋም ላይ ስለመገኘቱ ለደጋፊዎቹም ለተቀናቃኞቹም መልዕክት አስተላለፈ።

አዲሱ የሸገር ኮከብ

ከፕሪምየር ሊጉ ውልደት ወዲህ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ፍልሚያ የሀገሪቱ ብቸኛ ደርቢ እስኪመስል ድረስ በከፍተኛ ውጥረት፣ በአስደማሚ ድባብ፣ በጋለ የተጠባቂነት ደረጃ ላለፉት ሩብ ክፍለ ዘመናት ተከናውኗል። አስደናቂ የግለሰብ አቋሞች፣ አሉታዊ ጥላ ያጠሉ ክስተቶች፣ ውዝግቦች፣ ብሎም አፍ አስከፋች ትዕይንቶች የማያጣው “የሸገር ደርቢ” ባለፉት ጥቂት ዓመታት እጅግ የወረደ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በማሳየቱ ምክንያት የእግርኳስ አፍቃሪው ትኩረት ሙሉ ለሙሉ የደጋፊ ድባብን በአንክሮ መመልከት ብቻ ሆኖ ነበር።

ይህ ደብዛዛ ስም እያገኘ የመጣ ደርቢ ዘንድሮ ሊጉ እየተደረገ በሚገኝበት የውድድር አካሄድ ምክንያት “ምን ይውጠው ይሆን?” ተብሎለት ነበር። “አንድ የሚታይ ነገር ያለው የደጋፊው ድባብ ነበር። አሁን በዝግ ስታዲየም ተደርጎ ምን ልንመለከት ነው?” የሚለውን ስጋትም ብዙሀኑ የተጋራው ሀሳብ ነበር።

ከ2009 ወዲህ በተደረጉ በፕሪምየር ሊጉ እና በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የሸገር ደርቢ ጨዋታዎች ላይ የተሳተፈው አቡበከር ፈረሰኞቹ ላይ ጎል አስቆጥሮ አለማወቁ ለጨዋታው የነበረው ተነሳሽነት ከፍ እንዲል ያደረገው ይመስላል። በፍልሚያው ዋዜማ ለሶከር ኢትዮጵያ “የደርቢ የጎል አካውንቴን እከፍታለሁ” ሲል የተናገረው አጥቂው ማሸነፍ ሦስት ነጥቦችን ከማግኘት በላይ በሆነው ጨዋታ ላይ ለቡና አስፈላጊው ተጫዋች ከመሆኑ ጋር ተደምሮ ትልቅ ኃላፊነት ይዞ ገባ።

ይህ ጨዋታ ሲጠናቀቅ የብዙሀኑ ስጋት የነበረው ቀዝቃዛ የፉክክር ጨዋታ ሳይታይ ቀረ፣ ይልቁንም እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ በትዕይንት የተሞላ ድንቅ ፉክክር አስመለከተን። ኢትዮጵያ ቡና የደርቢው አሸናፊ ሆነ፣ አቡበከርም ቃሉን ጠበቀና በደርቢው የወቅቱ ኮከብነቱን አወጀ!

ኢትዮጵያ ቡና በአቡበከር አምበልነት እየተመራ ጨዋታውን 3 ለ 2 አሸነፈ። ከቀደሙት ዓመታት የተለየ ግሩም የሜዳ ላይ ፉክክር ባስመለከተን ጨዋታ አቡበከር የጨዋታውን ውጤት መወሰን የጀመረው ገና በአስረኛው ደቂቃ በፈጣን ሩጫ ከተካላካዮች አምልጦ ከፓትሪክ ማታሲ ጋር ሲገናኝ ነበር። ኬንያዊውም አጥቂውን ጠልፎ በማስቀረቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲሰናበት አቡበከርም የመጀመርያ ጎሉን በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጠረ። በጎዶሎ ተጫዋቾች ቁጥር የፈተናቸው ጊዮርጊስ ታናሽ ወንድሙ ሬድዋን ናስር በራሱ ላይ ባስቆጠረው ጎል አቻ ቢሆኑም በድጋሚ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ አደረገ። አሁንም ጊዮርጊሶች አስቆጠሩና በአቻ ውጤት ጨዋታው ዘለቀ። በሁለተኛው አጋማሽ የተገኘውን ሌላ የፍፁም ቅጣት ምት ወደ ውጪ ሰደዳትና የቡና የማሸነፍ ተስፋ የተመናመነ መሰለ። ሆኖም የመጨረሻው ፊሽካ ከመሰማቱ በፊት የለዓለምን ስህተት በአግባቡ ተጠቅሞ ሐት ትሪክ በመስራት ቡናን ወደ አሸናፊነት የመራች ታሪካዊ ጎል አስቆጠረ። የዚህች ጎል ታሪካዊነት የማሸነፍያ ጎል ብቻ በመሆኗ አልነበረም። በደርቢው የፕሪምየር ሊግ ታሪክ የመጀመርያ ሐት ትሪክ ሰሪ የሚል ስም በማሰጠቱም ጭምር ነበር።

በሸገር ደርቢ በሁሉም ረገድ የተዋጣለት ዕለት ያሳለፈው ኮከብ ከዛ ወዲህ ስሙ በሁሉም ሰው አፍ ውስጥ የሚገኝ ዝነኛው ተጫዋች ሆኗል። ከሌላው ጊዜ በተለየ በስታዲየም ከሚገኝ ተመልካች ውጪ በርካታ ህዝብ የተመለከተው ጨዋታ ላይ በደማቁ ያንፀባረቀው አቡበከር ዝናው የናኘ ቢሆን የሚያስገርም አይሆንም።

የአዲስ አበባ ውድድሩን በስኬት ያገባደደው አቡበከር ለሌላ ፈተና ወደ ጀማ አመራ። ቡድኑ አራፊ በመሆኑ የመጀመርያ ጨዋታ ያደረገው ከአስተናጋጅ ከተማው ቡድን ጅማ አባ ጅፋር ጋር ነበር። የተለመደ አስደናቂ የአጨራረስ ብቃቱ ገና የመጀመርያው አጋማሽ ሳይጋመስ አሳየና ጨዋታው ቀጠለ። ጅማዎች አስቆጥረው ለቡና ነገሮችን ቢያከብዱባቸውም በመጨረሻ ጨዋታውን አሸንፈው ወጡ። በቀጣይ በድቻ ላይ ጎል ማስቆጠሩን ቢቀጥልም ያልተጠበቀ ሽንፈት ሲያስተናግዱ ከባህር ዳር ሁለት አቻ ሲለያዩም የአቻነቷን ጎል አስቆጠረ። በጅማ ቆይታው ባደረጋቸው ጨዋታዎች ሁሉ ጎል ያስቆጠረው አቡኪ እንደ አዲስ አበባ ሁሉ የጅማ ቆይታውንም ያገባደደው ሐት ትሪክ በመሥራት ነበር። ቡድኑ ሲዳማ ቡናን አምስት ለምንም ሲደቁስ ሦስቱን አስቆጥሮ ሁለቱን አመቻችቶ የጨዋታው ሁሉ ነገር መሆን ቻለ።

የቡድኑ እና የአቡበከር ቀጣይ ፈተና ባህር ዳር ነች። ውቧ ከተማ አቡበከርን በምቹ የመጫወቻ ሜዳዋ ተቀብላው እሱም የእግርኳስ ህይወቱ እጅግ አሰደናቂ ጊዜን እያሳለፈባት ይገኛል። ከሆሳዕና ያለ ጎል በተያዩበት ጨዋታ ተፅእኖ መፍጠር ባይችልም በቀጣዩ ጨዋታ አዳማ ላይ ሐት ትሪክ በመሥራት ሌላ የብቃቱን ከፍታ አሳየ። ወልቂጤን ሲያሸንፉ ያስቆጠራቸው የውድድር ዓመቱ 18ኛ እና 19ኛ ጎሎች ደግሞ ምንም እንኳ ቡድኑ በከፍተኛ ብልጫ የጎል ዕድሎችን በመፍጠር ለማሸነፍ የሚጥር ቡድን ቢሆንም በሚቸገርበት ወቅት ምን ያህል ጨዋታን በራሱ መወሰን የሚችል ተጫዋች እንደሆነ በሚገባ ያሳየ ነበር።

ጉዞ ወደ ሪከርድ

የአቡበከር አስፈሪ አቋም በሀገራችን ባለው ደካማ የመረጃ አያያዝ ምክንያት በቁጥሮች እንዳይጎላ እንደሚያደርገው ግልፅ ነው። በውድድር ዓመቱ ሦስት ሐት ትሪክ መሥራቱ፣ በሸገር ደርቢ ሦስት ጎል ማስቆጠሩ እና የጎል መጠኑ በፍጥነት ማሻቀብን ከሌሎች የሊጉ ታሪካዊ አጥቂዎች ጋር በቁጥር አወዳድሮ ለማቅረብ እንዳንታደል አድርጎናል። የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሲነሳ “አንድ ለናቱ” የሆነችው የተመዘገበች ሪከርድ በአንድ ዓመት በርካታ ጎሎች የማስቆጠር በመሆኗ ለጊዜው አቡበከር ለመስበር የሚነሳው በ2009 በጌታነህ ከበደ በ25 ጨዋታ የተያዘውን ክብረ ወሰን ነው። ገና 11 ጨዋታ እየቀረው ከወዲሁ የጎሉ መጠን 19 የደረሰው አጥቂ ይህን ያሻሽል ይሆን? ከጌታነህ በፊት ይህን ክብር ለአስራ ስድስት ዓመታት ይዞ የነበረው ዮርዳኖስ ትንሹ ልጅ ይህን ታሪክ እንደሚሰራ ያምናል። የቡድን አጋሩ ታፈሰ ሰለሞንም “ገና ዓመቱ ሲጀመር ይህ እንደሚሆን ለጌታነህ ጭምር ነግሬዋለሁ” ብሏል።

ቀጣይ ፈተናዎች

የአቡበከር ቀጣይ ፈተና ራሱን በብሔራዊ ቡድን ደረጃ አጉልቶ ማሳየት ነው። በሁሉም የዕድሜ እርከኖች ተጫውቶ ከ2012 ጀምሮ ለዋናው ብሔራዊ ቡድን መጫወት የጀመረው አቡበከር አራት የነጥብ ጨዋታዎችን በቋሚነት መጫወት ችሏል። በዋልያዎቹ ማልያ የመጀመርያ ጎሉን ማስቆጠር እና የፕሪምየር ሊግ አስፈሪነቱን በዓለምአቀፍ ጨዋታዎች ላይም መድገም ከእሱ በቀጣይ የሚጠበቅ ነው። የባህር ዳሩ ውድድር ከተጠናቀቀ በኋላ ከማዳጋስካር እና አይቮሪኮስት ጋር ጨዋታ የሚጠብቃት ኢትዮጵያም ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለምታደርገው ጉዞ የአቡበከር ልዩነት ፈጣሪነትን ከምንጊዜውም ጊዜ በላይ ትፈልገዋለች።

የአቡበከር ተሰጥኦ፣ የአዕምሮ ዝግጁነት እና ለኳስ ያለው ፍቅር ከዕድሜው ለጋነት ጋር ተዳምሮ ይበልጥ ወደፊት እንደሚጓዝ ብዙዎች ጥርጣሬ የላቸውም። ግን ደግሞ የሙገሳ ቃላት መብዛታቸውን ተከትሎ የሚመጣ ጫና ሰለባ እንዳይሆን መጠንቀቅ እንዳለበት የቀድሞ አሰልጣኞቹ ይናገራሉ። “ስለ እርሱ ብዙ ነገር መነገር አለበት ብዬ አስባለው። ግን ከፍ አድርገን ባወራን ቁጥር እንዳይጠፋ ፍራቻ አለኝ። ሚዲያው እርሱን መቆጣጠር አለበት። ምክንያቱም ከዚህ በኃላ ብዙ ዓመት ልናየው የሚገባ ተጫዋች ነው። ከፍተኛ አቅም ያለው ተጫዋች እንደመሆኑ መጠን በጥንቃቄ ሊጠበቅ ይገባል።” የሚለው አሰልጣኝ ደግፌ ሲሆን አሰልጣኝ አጥናፉም በዚህ ይስማማሉ።

ሌላው የእግርኳስ ቤተሰብ ስጋት የሰውነቱ ደቃቃነት እና ለጉዳት ያለው ተጋላጭነት ነው። የሰውነቱ ቅጥነትን የሚመለከቱ ሁሉ ከፍተኛ ጉዳት እንዳያስተናግድ ፍራቻቸውን በመግለፅ ተጋላጭነቱን ለመቀነስ መሥራት እንደሚገባውም ብዙዎች ይናገራሉ። አሰልጣኝ አጥናፉም የዚህ ስጋት ተጋሪ ናቸው። ” በእርግጥ የሚጎሉት ነገሮች አሉ፤ እኔም አንድ ሰነድ አዘጋጅቼ ሰጥቸዋለው። ይሄም ከ17 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ የነበረውን የክብደት መጠን፣ ቁመት በየጊዜው ያመጣው ለውጥ አለ። ከ20 ዓመት በታች ሲገባም እንዲሁ ያመጣው ለውጥ በሰነድ ተዘጋጅቶ የተቀመጠ አለ። በእንደነዚህ ያሉ የሚጎሉትን ነገሮች ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገለት ቢጫወት ልጁ ከፍተኛ የእግርኳስ አዕምሮ ያለው በመሆኑ በብዙ መልኩ ይለወጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። አሁን በብዙ ነገር ተለውጧል፤ ያም ቢሆን ድጋፍ ያስፈልገዋል። ለምሳሌ አምና ብዙ ጉዳቶች ያስተናግድ ነበር። እግርኳስ የንኪኪ ጨዋታ ነው። ስለዚህ የአካል ብቃቱ ላይ ለውጥ ማምጣት መቻል አለበት። ይሄንንም ለእርሱ ለራሱ ጠቆም አድርጌዋለሁ።”

አቡበከር ገና ከወዲሁ ብዙ ታዳጊዎች እንደ አርዓያ እየተመለከቱት ይገኛል። በቴሌቪዥን ተመልክተውት እንደርሱ ለመሆን የሚያልሙ በርካቶች እንደሆኑም አያጠራጥርም። በታዳጊዎች ላይ እየሰራ እንደመሆኑ ምስክር ሊሆን የሚችለው አሰልጣኝ ደግፌም ይህን ሀሳብ ያጠናክራል። ” ለብዙዎች ታዳጊዎች ትልቅ ተነሳሽነት እየፈጠረ ነው። እርሱን መሆን የሚፈልጉ በርክተዋል። አቡበከርን ለማየት ቡናን የሚደግፉ ታዳጊዎችም ሆነ አዋቂዎች በዝተዋል። አቡበከር ቡናን በማስተዋወቅ ከፍ እያለ ነው። የኢትዮጵያ እግርኳስ ደረጃ ምንያህል እንደሆነ አበቡበከር ማሳያ ነው።”

ወጣቱ ተጫዋች በሜዳ ላይ ብቻ ሳይሆን ከሜዳ ውጪም ታዳጊዎች ሊከተሉት የሚገባ ስብዕና ባለቤት ስለመሆኑ ይነገርለታል። ከሌላው ኢትዮጵያ ያልተለየ የኑሮ ደረጃ ካላቸው ቤተሰቦች የተገኘው ኮከብ ከእግርኳስ ያገኘውን ገንዘብ የቤተሰብ ኑሮን በማቃናት ላይ ቀዳሚ ትኩረት ስለማድረጉም በቅርብ የሚያውቁት ሰዎች ይናገራሉ።

የእግርኳሱ ዓለም በፍጥነት እየተለዋወጠ ይገኛል። ቀን ሌላ ቀንን ሲተካ እርሱም ወደታላቅነት መሮጡን የቀጠለው አቡበከርንም ነገ በሌላ ታላቅ የእግርኳስ ምዕራፍ እንመለከተው ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ