ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለክለቡ ገቢ የሚያስገኙ ሱቆችን አስመረቀ

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ረጅም ታሪክ ያለው የኢትዮ ኤሌክትሪክ ክለብ ራሱን ማስተዳደር ይችል ዘንድ ያስገነባቸውን በርካታ ሱቆች በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ የገዘፈ ስም ካላቸው ክለቦች መካከል የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ አንዱ ነው፡፡ክለቡ በዚህ ረጅም ታሪኩ ውስጥ በርካታ ስመ ጥር ተጫዋቾችን ከታችኛው ቡድን በማሳደግ ለራሱ ዋና በድንም ሆነ ለሀገራችን ለሚገኙ ሌሎች ክለቦች አልፎም እስከ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድረስ በማብቃት ተወዳዳሪ የለሽ ስም ተክሎ ይገኛል፡፡ ክለቡ የፋይናንስ ምንጩ ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ መብራት ኃይል በጀት የነበረ ሲሆን አሁንም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና ኃይል ተብለው በሚጠሩ ተቋማት እየተደገፈ የሚገኝ ሲሆን በቀጣይ ግን ራሱን በራሱ ማስተዳደር እንዲችል የስፖርት ክለቡ የበላይ አካላት ከቀድሞው ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ደንድር የመጣላቸውን መልካም ሀሳብ በመቀበል ተግብረው በዛሬው ዕለት ፈፅመዋል፡፡ ይህም ክለቡ ከመንግሥት ጥገኝነት እንዱላቀቅ ሠላሳ ስምንት ሱቆችን ጎፋ በሚገኘው የክለቡ የልምምድ ሜዳ ዙሪያ ገንብቶ 2ሺህ ተመልካቾችን ከሚይዘው ትሪቡን ጋር በጋራ አስመርቋል፡፡

የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ጫላ አማን ዛሬ ረፋድ የነበረውን የምርቃ ፕሮግራም እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት በቅድሚያ ንግግራቸው የጀመሩ ሲሆን ይህ ግንባታም ከ21.6 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደወጣበት በዝርዝር ለታዳሚው አስረድተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ክለቡ ህዝባዊ መሠረት እንዲይዝ እንዲህ ዓይነት ሥራዎችን ክለቡ መጀመሩ ይበል እንደሚያሳኝም ጭምር በእንኳን ደህና መጣችሁ የመጨረሻ ንግግራቸው ገልፀዋል፡፡

በመቀጠል ክለቡን ከዚህ ቀደም በፕሬዝዳንትነት የመሩት የዚህ በጎ ሀሳብ ጀማሪ እና ፈፃሚ የሆኑት አቶ ኢሳያስ ደንድር የክለቡ የበላይ አካላት ትኩረት ሰጥተው ተፈፃሚ እንዲሆን ከጎን በመሆን ሲያደርጉ ለነበሩት ከፍተኛ ድጋፍ በማመስገን ክለቡ ከዚህም ከፍ ብሎ ወደ ቀደም ክብሩ ይመለስ ዘንድ ሁሉም ከዚህ አንጋፋ ክለብ ጎን ሊቆም ይገባልም ብለዋል።

በመቀጠል የተገነቡትን ሱቆችም ሆኑ የትሪቡን ግንባታውን አቶ አሸብር ባልቻ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሺፈራው ተሊላ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ እንዲሁም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ሠውነት ቢሻው እና የፅህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን በጋራ በመሆን መርቀውታል፡፡ ክለቡ ዛሬ ያስመረቃቸውን ሱቆች በክለቡ ታሪክ በሰሩ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ስምም ሰይሟል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ