ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

በአስራ አምስተኛ ሳምንት ላይ ያተኮሩ የአሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች እና ዐበይት አስተያየቶችን እንደሚከተለው ቀርበዋል።

👉 አሰልጣኝ ማሒር ዳቪድስ እየረፈደባቸው ነው?

ከጥቂት የጨዋታ ሳምንታት በፊት በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በተከታታይ ነጥቦችን በመጣሉ ከመሪው ፋሲል ከነማ በ10 ነጥብ ርቆ ለመቀመጥ ተገዷል።

ሥራቸው ጫና ውስጥ የሚገኘው የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ በተከታታይ እያስመዘገቡ የሚገኙት ውጤት ያሉበትን ሁኔታ ከማረጋጋት ይልቅ ይበልጡኑ ጫና ውስጥ የሚከቱ እየሆኑ መጥተዋል። አሰልጣኙ ከዚህ በኋላ በምንም ዓይነት ሁኔታ ነጥብ የሚጥሉ ከሆነ እጃቸው እየወጣ የሚገኘውን የዋንጫ ፉክክር ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍ እያለ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታቸው እጅግ ወሳኙ ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ።

አሰልጣኝ ለማሰናበት ምንም ርህራሄ እንደሌላቸው የቀደመው ልምዳቸው የሚያሳየው የክለቡ አመራሮች ክለቡ ከዋንጫው ፉክክር እየራቀ መምጣቱን ተከትሎ ቀጣይ ውሳኔያቸው ለአሰልጣኙ ጊዜ መስጠት ወይስ ማሰናበት የሚለው የሚጠበቅ ነው።

👉 ሀዘን ውስጥ ሆነው ጨዋታ የመሩት ደግአረግ ይግዛው

ከጥቂት ቀናት በፊት አያታቸውን በሞት የተነጠቁት የወልቂጤ ከተማው አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው ለሀዘናቸው መፅናኛ የሚሆንን ድል ጅማ አባ ጅፋር ላይ ተቀዳጅተዋል።

ከጨዋታውም በኃላ ከሱፐር ስፖርት ማስተዋሻነቱን በሞት ላጧቸው አያታቸው መታሰቢያ ያውሉ እንደሆን የተጠየቁት አሰልጣኙ “እንደ ጥሩ መታሰቢያ የሚወሰድ ከሆነ ቢሆን ደስ ይለኛል።” ሲሉም ተደምጠዋል።

👉የአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ቀጣይ ፈተና

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ብዙም ሳይወራላቸው በዝምታ ውስጥ ለጠያቂዎቻቸው ምላሽ በመስጠት ቡድናቸውን በተደላደለ መልኩ በሰንጠረዡ አናት ማስቀመጥ ችለዋል። ይህ ከዓመት ዓመት ይበልጥ እየተብላላ እና እየተዋሀደ የሚገኘው ቡድን ሊጉን ከተከታዮቹ በሰፊ ልዩነት በዚህ ወቅት መምራት መጀመሩ የሚደነቅ ነው።

የአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ዋነኛ ፈተና የሚጀምረውም አሁን ይመስላል። ተከታታይ ድሎችን አስመዝግቦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ኢትዮጵያ ቡና በ8 ነጥብ እየራቀ ቀሪ አስር ጨዋታዎች የሚጠብቀው ቡድን በእነዚህ ጨዋታዎች የሚያስመዝግባቸው ውጤቶች በጣሙን ይጠበቃሉ።

መሪ መሆን በራሱ የሚፈጥረው ጫና እንዳለ ሆኖ፤ አሰልጣኝ ሥዩም ተጫዋቾቻቸው የስምንት ነጥብ ልዩነት በመፈጠሩ ሳይዘነጉ ከዚህ ቀደም በነበረው የድል ረሀብ እንዲቀጥሉ ማስቻል በራሱ ትልቅ ፈተናቸው ነው።

ሌላኛው የቡድኑ ፈተና ምንም እንኳን በሁለተኛው ዙር ሁሉም ከወገብ በላይ የሚገኙ ቡድኖች የሚያጋጥም ቢሆንም ከዚህ ቀደሞ ከነበሩት ዓመታት ልምድ አንፃር አለመሸነፍን ቅድሚያ የሰጡ የጨዋታ አቀራረቦች በተለይ በሁለተኛ ዙር በቡድኖች ይበልጥ የሚጨምሩ መሆኑ ነው። በመሆኑም እንደፋሲል ያሉ አጨዋወታቸው ክፍተቶችን ከማግኘት አንፃር ትዕግስት የተካለበት ቡድኖች በጨዋታ ወቅቶች ተጋጣሚዎች አማራጭ በማሳጣት ሲፈትኗቸው በተሻለ መልኩ መፍትሄ ፈጣሪ ሆነው መገኘት የግድ ይላቸዋል።

ቡድኑ እስካሁን ከሰበሰበው 35 ነጥብ ያልተናነሳ 30 ነጥብ ሊያግኝባቸው የሚችሉ ጨዋታዎች ከፊቱ ይጠብቁታልና አሰልጣኙ ይህ ላለፉት ሦስት የውድድር ዘመናት እየጎለበተ እና ይበልጥ እየጠነከረ የሚገኘውን ስብስብ በያዘው አስደናቂ ጉዞ አስቀጥሎ ለውጤት የማብቃት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እነዚህን እና ሌሎች ያልጠቃቀስናቸውን ተግዳሮቶች መሻገር የግድ ይላቸዋል።

ዓበይት አስተያየቶች

👉 ካሣዬ አራጌ ስለዋንጫ ፉክክሩ

“ገና እንግዲህ ሁለተኛው ዙር መጀመሩ ነው። ይሄ ሁለተኛ ጨዋታችን ነው። ስለዚህ ከዚህ በኋላ ብዙ ጨዋታዎች አሉ። አሁንም ቢሆን ለቻምፒዮንነት ለመጫወት ዕድሉ አለን።”

👉ሥዩም ከበደ ስለቻምፒዮንነት ማሰብ ስለመጀመራቸው

“አዎ ማለት እችላለሁ። ምክንያቱም ከእኛ ጋር እኩል የሚወዳደሩትን በዚህ ነጥብ ርቀት 8 ፣ 9 እና 10 መራቅ ቀላል ነገር አይደለም። በቡድኑ ሥነ-ልቦና ላይ የሚፈጥረው ጥንካሬ ትልቅ ነው። ከሁሉም በላይ ሁለተኛውን ዙር ስንጀምር ከጠንካራዎቹ ነው የጀመርነው ፤ ከቅዱስ ጊዮርጊስም ከኢትዮጵያ ቡናም ጋር። እነዚህን ተፎካካሪዎችን አሸንፈን መውጣቱ ከሁለቱም ስድስት ነጥብ ማግኘት አጠቃላይ የቡድናችንን ጥንካሬ እና የሥነ-ልቦና ከፍታን ያሳያል እና በጣም ጥሩ ቀን ነው ብዬ አስባለሁ።”

👉ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ቡድኑ ጥሩ ጥሩ ግልፅ የግብ ማግባት ዕድሎችን ፋጥሮ ጎል ስላለማስቆጠሩ?

ይህንን ችግር እንደ ቡድን ነው የምንወስደው። እንዳልኩት ከባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ቡድናችን ተሻሽሎ ነው የመጣው። ተጫዋቾቻችን ያላቸው አቅም እና ቡድኑ ያለበት ደረጃ የሚመጣጠን እንዳልሆነ ነው ዛሬ ያየሁት። በደንብ ጫና አሳድረን ተጫውተናል። ግን ብልጫ ወስደን ተጫውተን ሦስት ነጥብ አለማግኘታችን በቀጣይ ሥራ እንደሚጠብቀን የሚያሳይ ነው። እንደተባለው ብዙ ዕድሎችን ብንፈጥርም መጠቀም አልቻልንም። በቀጣዩ የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ችግራችንን አስተካክለን እንቀርባለን።

👉አብርሃም መብራቱ ስለዳዊት እስጢፋኖስ እና አዲሱ የተከላካይ አማካይነት ሚናው ?

“ዳዊት ያው ያለው ልምድ የሚታወቅ ነው ፤ ያለው የኳስ ክህሎት ጥሩ ነው ምንም እንኳን እዛ ቦታ ላይ ለረጅም ጊዜ ባይጫወትም ያለው ልምድ ግን እዛ ቦታ ላይ ኳስን ተቆጣጥሮ የእኛን ተከላካዮችን ኳስ እያስነካ እንዲወጣና ጨዋታውን አንብቦ እንዲጫወት ነው የምንፈልገው። ከዛም በላይ ደግሞ ወጣት የሆኑት ከፊት ያሉትን ተጫዋቾች እንዲመራልን ብለን ነው ፤ ከዚህ አንፃር በቦታው ላይ ዳዊት ትልቅ ጥቅም እየሰጠን ነው።”

👉 ፀጋዬ ኪዳነማርያም ስለአቡበከር ኑሪ ጥሩ ውሎ

“አቡበከር እንግዲህ ወጣት ልጅ ነው። ለጅማ አባ ጅፋር ብቻ ሳይሆን ለብሔራዊ ቡድን እና ለውጪ ዕድል የሚደርስ ግብ ጠባቂ ነው። በጣም ጥቃቅን ስህተቶች ካልሆነ በቀር በዚህ ውስን ልምዱ እያሳየ ያለው ብቃት በጣም ጥሩ ነው። በእግር ሲጫወት ጥሩ ነው ፣ የዓየር ላይ ኳስ የማዳን ብቃቱ ጥሩ ነው ፣ ከተከላካዩ ጋር ለመጫወት የሚሞክረው ነገርም ጥሩ ነው ። ለወደፊቱ ለብሔራዉ ቡድን ጥሩ ተተኪ ተጨዋች ነው ብዬ አስባለሁ።”

👉 ፋሲል ተካልኝ በደረጃ ከፍ ስለማለታቸው

“ወደ ፉክክር መመለሳችን እና ደረጃ ውስጥ ወዳሉት ቡድኖች መጠጋታችን ለእኛ ኃላፊነት ነው። የበለጠ ደግሞ ጠንክረን እንድንሰራ እንዲሁም ተጨዋቾቻችን በሥነ-ልቦናው ረገድ የተሻለ እንዲሆኑ ይረዳናል። ዞሮ ዞሮ ወደ ዋንጫ መጠጋት እና ደረጃ ውስጥ ማጠናቀቅ ነው ህልማችን። እዛ ለመድረስ ሜዳ ላይ የምንሰራቸውን ስህተቶች እየቀነስን መምጣት ይጠበቅብናል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ