ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ17ኛ ሳምንት ምርጥ 11

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በድሬዳዋ ስታድየም ሲቀጥል የ17ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን መሰረት በማድረግ የሳምንቱን ምርጥ ቡድን እንዲህ አሰናድተናል።

አሰላለፍ 4-3-3

ግብ ጠባቂ

ፋቢያን ፌርኖሌ – ሲዳማ ቡና

በግብ ጠባቂዎች ስህተት ግቦችን ሲያስተናግድ የቆየው ሲዳማ ቡና መፍትሄ ይሆነኛል ብሎ ያመጣው ቤኒናዊው ግብ ጠባቂ በመጀመሪያ ጨዋታው ለቡድኑ ጥያቄ መልስ መስጠት ችሏል። ግዙፉ የግብ ዘብ ከቡድን አጋሮቹ ጋር ካሁኑ ጥሩ መናበብን ማሳየት ሲችል የአብዲሳ ጀማልን ያለቀለት የግብ ሙከራ ያዳነበት መንገድም ድንቅ ነበር።

ተከላካዮች

እንየው ካሣሁን – ፋሲል ከነማ

እንየው በፋሲል ቤት የቀኝ መስመር የተላካይነቱን ሚና ከተረከበ ጀምሮ በወጥ አቋም መዝለቁን ተያይዞታል። በወላይታ ድቻው ጨዋታም እንደተለመደው ከፍ ያለ ያማጥቃት ተሳትፎ ሲያደርግ የዋለው መስመር ተከላካዩ ሙጂብ ቃሲም ሁለተኛውን ግብ እንዲያስቆጥር በልኩ የተመጠነ ኳስ በማሻገር የቡድኑን ድል ዕውን ያረገችው ጎል እንድትገኝ አስተዋፅዖ አድርጓል። ተጫዋቹ በተሻጋሪ ኳስ ለሙጂብ ጎል መንስኤ ሲሆን ይህ ሁለተኛው ነው።

ያሬድ ባየህ – ፋሲል ከነማ

ከብሔራዊ ቡድን ግዳጅ መልስ የወትሮው እርጋታ የተላበሰ እንቅስቃሴውን ማሳየት የቻለው ያሬድ ባየህ የመልሶ ማጥቃት ፈተና የነበረበት የአፄዎቹን የኋላ ክፍል በአግባቡ መምራት ችሏል። ከዚህ ባለፈ ከኳስ ጋር ሲሆን ነፃነት የሚታይበት ተከላካዩ የድቻዎች የፊት መስመር ጫና በቀነሰበት ወቅት በራስ መተማመኑን በሚያሳይ መልኩ መሀል ሜዳ ድረስ በመጠጋት ክፍተቶችን ሲፈልግ ለነበረው ቡድኑ የኳስ ፍሰት መነሻ ሆኖ አገልግሏል።

ምኞት ደበበ – ሀዋሳ ከተማ

ሀዋሳ ከተማ እንደቡድን እጅግ ጠጣር ሆኖ በቀረበበት ጨዋታ ኢትዬጵያ ቡናን አላፈናፍን ብሎ እንዲያመሽ ከተጉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ምኞት ደበበ ነው። ከላውረንስ ላርቴ ጋር በነበራቸው ጥምረት ከስህተት በፀዳ እና እስከፍፃሜው ባልተዛነፈ ትኩረት የቡናን አጥቂዎች በአግባቡ መቆጣጠር ሲችሉ ሀዋሳን ባለድል ያደረገችውን ግብ በማስቆጠሩም ምኞት የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ መሆን ችሏል።

መሐሪ መና – ሲዳማ ቡና

ክለቡን ከተቀላቀለ ጀምሮ ሦስተኛ ተከታታይ ጨዋታውን ያደራገው መሀሪ መና በሳምንቱ ከታዩ የግራ መስመር ተከላካዮች ጋር ሲነፃፀር የተሻለው ተመራጭ ሆኗል። ተጫዋቹ በመከላከሉ ረገድ በየጨዋታው ግብ የሚቆጠርበትን ቡድን በመስመሩ በኩል እንዳይከፈት በትጋት የተጫወተ ሲሆን ወደ ፊት ኳሶችን በማሻገር ማጥቃቱን ለማገዝም ጥሯል።

አማካዮች

ዳዊት እስጢፋኖስ – ሰበታ ከተማ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚው ሰበታን በራሱ ሜዳ ላይ ለማስቀረት ከፍ ባለ ጫና ለማፈን በሞከተበት ጨዋታ ሰበታ በተረጋጋ ሁኔታ ኳስ ይዞ መሀል ሜዳውን እንዲያልፍ የሚረዳው ተጫዋች ያስፈልገው ነበር። በዚህም ከተከላካዮች ፊት ያለው ቦታ ላይ መሰለፍ ምቾት እየሰጠው የሚገኘው ዳዊት ቅብብሎችን በመከወን ቡድኑ ከራሱ ሜዳ ለመውጣት የነበረበትን ፈተና ሲያቃልል ተስተውሏል።

ዳንኤል ኃይሉ – ድሬዳዋ ከተማ

በውድድሩ አጋማሽ ከሰበታ ወደ ድሬዳዋ ያመራው ዳንኤል ድሬዳዋ መሀል ሜዳ ላይ ላጣቸው ነገሮች መፍትሄ እንደሚሆን ፍንጭ የሰጠበትን ጨዋታ አድርጓል። በፍፁም ቅጣት ምት ብቸኛዋን ግብ ማስቆጠሩ እንዳለ ሆኖ ከሞክሼው ዳንኤል ደምሴ ጋር የነባር ተጫዋች ያህል ጥሩ ጥምረት በመፍጠር የቡድኑን የማጥቃት ሂደት ከጥልቅ ቦታዎች ላይ መምራት ሲችል ከቆሙ ኳሶችም ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችሎ ነበር።

ሳምሶን ጥላሁን – ባህር ዳር ከተማ

ከወትሮው በተለየ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ተጠግቶ የተጫወተው ሳምሶን ከኳስ ጋር በተገናኘባቸው ቅፅበቶች ቀለል ባለ አኳኋን ቅብብሎችን በማድረግ በቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ላይ ሁሉ ተሳታፊ ነበር ማለት ይቻላል። በሁለት አጋጣሚዎች የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን ፈጥሮ የነበረው ተጫዋቹ ለባዬ ገዛኸኝ ግብም አመቻችቶ በማቀበል ለቡድኑ ድል ወሳኝ ሚና ተወጥቷል።

አጥቂዎች

ኦኪኪ አፎላቢ – ሲዳማ ቡና

ከአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጋር በሦስተኛ ክለቡ የተጣመረው ናይጄሪያዊው አጥቅ ስለምን አሰልጣኙ ዕምነት እንደሚጥሉበት አሳይቷል። በድንቅ የቅጣት ምት ሙከራ በጀመረው የአዳማው ጨዋታ ጨራሽ መሆኑን ባሳየበት አጋጣሚ ሲዳማን ቀዳሚ ያደራገች ግብ ሲያስቆጥር ከመስመር እየተነሳ ያደርገው የነበረው እንቅስቃሴ የቡድኑን የማጥቃት ሂደት አስፈሪ አድርጎት አምሽቷል።

ባዬ ገዛኸኝ – ባህር ዳር ከተማ

በሙሉ ትኩረት እና አካል ብቃት ላይ ሲገኝ እጅግ አስፈሪ የሆነው ባዬ ገዛኸኝ ይህንን የሜዳ ላይ ባህሪውን ያሳየበትን ጨዋታ አከናውኗል። ከሳምሶን ጥላሁን የደረሰውን ኳስ በአስደናቂ አጨራረስ አስቆጥሮ ቡድኑ ጨዋታውን እንዲመራ ማድረግ ሲችል በሌላ አጋጣሚ በግቡ አግዳሚ ተመለሰበት እንጂ የግብ ብዛቱን ሁለት ለማድረስም ተቃርቦ ነበር።

ሙጂብ ቃሲም – ፋሲል ከነማ

ሦስተኛ ተከታታይ ጨዋታው ላይ ግብ ማስቆጠር የቻለው ሙጂብ በሁለቱ ጨዋታዎች ደግሞ ሁለት ሁለት ግቦችን ከመረብ አገናኝቷል። ፋሲል በተፈተነበት የድቻው ጨዋታ ሙጂብ ፊት ላይ በከፍተኛ በራስ መተማመን ሲያደባ ቆይቶ ያገኛቸውን አጋጣሚዎች በድንቅ አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሯቸዋል። ተጫዋቹ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ፉክክሩ ላይም ፍጥነቱን ጨምሮ ከአቡበከር ናስር ጋር የነበረውን ልዩነት ወደ ሦስት ዝቅ ማድረግ ችሏል።

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀዋሳ ከተማ

ከአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጋር ለሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኝነት የተፎካከረው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ካደረገው ጨዋታ ክብደት አንፃር ተመራጭ ሆኗል። የዋንጫ ተፎካካሪ የሆነው ኢትዮጵያ ቡናን የገጠመው ሀዋሳ ከተማ ለሰባት ጨዋታዎች ከድል ቢርቅም በመልካም የሥነ ልቦና ጥንካሬ ላይ ሆኖ ነበር ጨዋታውን ያደረገው። የተጋጣሚን አጨዋወት መቆጣጠር እና የተጫዋቾችን ትኩረት እስከመጨረሻው እንዲቀጥል በማድረግ ላይ ያተኮረው የአሰልጣኙ ዕቅድ ሰምሮም ሀዋሳ ከስምንተኛው ሳምንት በኋላ ወደ ድል ተመልሷል።

ተጠባባቂዎች

ባሕሩ ነጋሽ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ላውረንስ ላርቴ – ሀዋሳ ከተማ
ውብሸት ዓለማየሁ – ጅማ አባ ጅፋር
ብርሀኑ አሻሞ – ሲዳማ ቡና
ኦሴይ ማዊሊ – ሰበታ ከተማ
ግርማ ዲሳሳ – ባህር ዳር ከተማ
ጁኒያስ ናንጄቦ – ድሬዳዋ ከተማ


© ሶከር ኢትዮጵያ