ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

በ18ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተመለከትናቸው ዓበይት ተጫዋች ነክ ጉዳዮች በዚህ ፅሁፍ ለመዳሰስ ሞክረናል።

👉 ዓይኖች የበዙበት አቡበከር ናስር

አቡበከር ናስር የሚለው ስም ከእግርኳስ ቤተሰቡ አልፎ ለእግርኳሱ ሩቅ በሆኑ ግለሰቦች ዘንድም መታወቅ እየጀመረ መጥቷል። ይህ ወጣት አጥቂ በተለይ ብሔራዊ ቡድናችን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ካለፈ ወዲህ ትኩረቶች ሁሉ ወደ እርሱ ሆነዋል።

እርግጥ ሁኔታው ጥሩ ጎኖች ቢኖሩትም በተለይ እንደ አቡበከር ናስር ላሉ አፍላ ወጣቶች ግን ይዞባቸው የሚመጣ በቀላሉ የማይታይ ጫና መኖሩ አያጠያይቅም። ተጫዋቾች በእግርኳሳዊ ህይወታቸው ብቅ ብቅ ማለት በጀመሩበት በዚህ ወቅት ከሜዳ ውጪ ባሉ ሁነቶች ትኩረታቸው ሳይሰርቅ ሜዳ ላይ ያለው ብቃታቸውን ለማሳደግ መጣራቸውን ካልቀጠሉ ብዙዎች በዚህ ያለጊዜው በሚመጣ የዝና ማዕበል ተወስደው የእግርኳስ ህይወታቸው በአጭሩ ሲቀጭ አስተውለናል።

አቡበከር ናስር ግን ይህን ፈተና በብቃት እየተወጣ ያለ ይመስላል። ተጫዋቹ አሁንም ሜዳ ላይ ያለውን ብቃት በማሻሻል ወደ ታላቅነት ለመገስገስ ጥረቱ ተዛንፎ አልታየም።

በ18ኛ ሳምንት ቡድኑ ሰበታ ከተማን ሲረታ ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች የተጫዋቹን እያደር እያደገ መምጣት ማሳያ ናቸው። አቡበከር ሁለቱም ያስቆጠራቸው ግቦች የአጨራረስ ክህሎቱ ስለመሻሻሉ በራሳቸው ምስክር ናቸው።

ግቦቹ የተቆጠሩበት መንገድ ተጫዋቹ ከግብ በፊት ባሉት እነዛ የመጨረሻ ጥቂት ሰከንዶች ላይ ብዙ አጥቂዎች በልምድ የሚያመጡትን እርጋታ ገና ከወዲሁ ያገኘው ይመስላል። በጨዋታው ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦችም ሆኑ የግቡ ቋሚ የመለሰችበት ኳስ ጭምር አጥቂው ዓይኖች ሁሉ እሱ ላይ በሆኑበት እና ቡድኑ ከሽንፈት ለመመለስ በሚያደርገው ጨዋታ መሆኑ እርጋታውን ሳይነጥቀው ደግም ኃላፊነቱን መወጣቱ አጠቃላይ የልጁን የአዕምሮ ዝግጅትም ሆነ ወደ ታላቅ አጥቂነት እየተሸጋገረ ለመምጣቱ ምስክሮች ናቸው።

👉 ስታድየሙን የሚያሞቁት የውጪ ግብ ጠባቂዎች

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮው ውድድር ላይ በተለይ የደጋፊዎች አለመኖርን ተከትሎ በየስታድየሞቹ ያለው ድባብ እጅግ የተቀዛቀዘ ነው። በተለይም በድሬዳዋው ውድድር በቁጥር ውስን የሆኑት እና ፍቃድ ተሰጥቷቸው የነበሩ የተጋጣሚ ክለብ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ መግባት መከልከልን ተከትሎ በድሬዳዋ ስታዲየም ያለው ድባብ እጅጉን ከመቀዝቀዙ ጋር በተያያዘ እያንዳንዱ ሜዳ ላይ ያሉ ድምፆች ኩልል ብለው መሰማት ጀምረዋል።

ታድያ በዚህ እያንዳንዱ ድምፆች በቴሌቪዥን ስርጭት በሚሰሙበት ወቅት የውጪ ሀገራት ግብ ጠባቂዎች በሜዳ ላይ በሚኖሩበት ወቅት የሚያወጡት ድምፅ ከሌሎች ተጫዋቾች ጎልቶ እየተደመጠ ይገኛል።

እነዚሁ የውጭ ሀገራት ዜግነት ያላቸው ግብ ጠባቂዎች ከኋላ በመሆን የቡድን አጋሮቻቸውን በማንቃት፣ በማነሳሳት ብሎም በመምራት ረገድ የሚወጡት ሚና ከፍ ያለ መሆኑ ቢታወቅም በዚህ ሂደት የሚያወጡት ድምፅ ግን ከሌሎች ተጫዋቾች በተሻለ በቀጥታ ስርጭት ወቅት ሆነ በስታዲየም ተለይቶ የሚሰማ መሆኑ ትኩረት ይስብ ነበር። ይህን ሒደት በአዎንታዊ መልኩ ከወሰድነውም ቡድን በመምራት ረገድ የሀገራችን ግብ ጠባቂዎች ሊማሩበት ይገባል።

👉 ታታሪው ተመስገን ደረሰ

እንደ ቡድን አሁን አሁን ከአሰልጣኝ ለውጥ ጋር በተያያዘ ለውጦችን ማሳየት ጀመሩ እንጂ እጅግ ደካማ የውድድር ዘመን እያሳለፈ በሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር ውስጥ በግላቸው ጥሩ የሚባል የውድድር ጊዜን እያሳለፉ ከሚገኙ ተጫዋቾች አንዱ ሁለገቡ ተመስገን ደረሰ ነው።

በመስመር ተከላካይነት ፤ በመስመር አጥቂነት ሆነ በፊት አጥቂነት በተለያዩ ጊዜዎች የሚሰጡትን ሚናዎች በሚገባ የሚወጣው ተጫዋቹ በተሰጠው ሚና ውስጥ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያሳየው መታታተር አስደማሚ ነው።

በ18ኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ከሀዋሳ ከተማ አንድ አቻ ሲለያይ በመስመር አጥቂነት ጨዋታውን የጀመረው ተጫዋቹ በጨዋታው እጅግ አስደናቂ የሆነ ታታሪነቱን አስመልክቶናል። ተመስገን በጥንቃቄ እየተከላከለ በተወሰኑ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ መጫወትን ምርጫው አድርጎ ወደ ሜዳ በገባው የጅማ አባ ጅፋር ቡድን ውስጥ በመከላከሉ ወቅት የነበረው ሚና ብሎም በመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶች ወቅት ከፍ ያለ ተሳትፎን ከማድረግ አልፎ ቡድኑን ለረጅም ደቂቃ መሪ ያደረገችውን ግብ ማስቆጠር ችሏል።

👉 ለተከላካዮች የራስ መተማመንን የመለሰው ፋቢያን ፋርኖሌ

ሲዳማ ቡና በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ያስፈረማቸው ተጫዋቾች በተለይ በድሬዳዋዉ ውድድር ለቡድናቸው እጅግ ወሳኝ ሚናን እየተወጡ ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ በተለይ በግብጠባቂ ስፍራ ላይ ያስፈረሙት አንጋፋው ቤኒናዊው የግብ ዘብ ፋቢያን ፋርኖሌ ድርሻ የላቀ ነው።

እስካሁን ሁለት ጨዋታዎች ያደረገው ፋፍኖሌ ምንም ግቦችን አላስተናገደም። በዚህ ሒደት ውስጥ ግብ ጠባቂው በተለይ በወልቂጤ ከተማው ጨዋታ አደገኛ ሙከራዎችን ከማዳኑ ባለፈ ከፊቱ ለተሰለፉ የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎች የራስ መተማመናቸውን የመለሰላቸው ይመስላል።

በሊጉ እጅግ ደካማ የተከላካይ መስመር ከነበራቸው እና ግቦችን በቀላሉ ያስተናግዱ ከነበሩ ክለቦች አንዱ የነበረው ሲዳማ ቡና ቀስ በቀስ እንደቡድን እያሳየ ከሚገኘው መሻሻል ትይዩ የቡድን የመከላከል አወቃቀር ላይ መሻሻሎች መታየት ጀምረዋል። ለዚህም ቤኒናዊው ግብጠባቂ ፋቢያን ፋርኖሌ ተጠቃሽ ነው።

በሊጉ የ18 የጨዋታ ሳምንታት ጉዞ ከአዳማ ከተማ ቀጥሎ በበርካታ የግብ ጠባቂ ስህተቶች ግቦችን ያስተናግድ የነበረው ሲዳማ ቡና አሁን ላይ ቡድኑ ዕምነቱን የሚጥልበት ጠንቃቃው ቤኒናዊ ግብ ጠባቂ መምጣቱን ተከትሎ የቡድኑ ተጫዋቾች በተለይም ተከላካዮች ከኃላቸው የሚተማመኑበት ጠንካራ ግብ ጠባቂ በመኖሩ ከፍ ባለ የራስ መተማመን እየተጫወቱ እንደሚገኙ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች መመልከት ይቻላል።

👉 ቀኑ ያልነበረው ቶማስ ስምረቱ

እንደቡድን ሰሞኑን በርከት ያሉ ግለሰባዊ ስህተቶች በበዙበት የወልቂጤ ከተማ የተከላካይ መስመር ውስጥ ከመሐም ሻፊ ጋር የተጣመረው ቶማስ ስምረቱ በዚህ ሳምንት የመነጋገርያ ርዕስ ሆኗል። ቡድኑ በጨዋታው ላስተናገዳት ብቸኛ ግብ ምክንያት ለሆነችው የፍፁም ቅጣት ምት መሰጠት ምክንያት የሆነው ቶማስ በዚህ ወቅት የቢጫ ካርድ ሰለባ የሆነ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ በአንድ የጨዋታ ቅፅበት ወልቂጤዎች የማዕዘን ምት ለማሻማት ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት በድጋሚ የቪድዮ ምልሰት የነበረው ሁኔታ በግልፅ ባይስተዋልም ከሲዳማ ቡናው የመሀል ተከላካይ ከሆነው ጊት ጋትኮች ጋር በነበረው ፍትጊያ ብዙም ግልፅ ባልሆነ ውሳኔ ሁለተኛ ቢጫ ካርድ ተመልክቷል። የጨዋታው የመሐል ዳኛ ብርሃኑ መኩርያ ቢጫ ካርዱ ሁለተኛ መሆኑን ባለማስተዋላቸው የተነሳ ለተወሰኑ ተጨማሪ ደቂቃዎች በሜዳ ላይ መቆየት ቢችልም በአራተኛ ዳኛው አማኑኤል ኃይለስላሴ አስታዋሽነት በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ ሊወገድ ችሏል።

በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ከመውጣቱ ባሻገር እንደ ቡድን በተለይ የመከላከል መስመሩ ላይ ጥያቄዎች እየተነሱበት የሚገኘው ቡድኑ በቀጣይ የእሱን ግልጋሎት ማግኘት አለመቻሉ በቡድኑ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ በራሱ ለቡድኑ ከፍተኛ ጉዳት ይኖረዋል።

👉 ደምቆ ያመሸው ኤልያስ ማሞ

በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማን ለቆ ላለመውረድ እየታገለ የሚገኙት አዳማ ከተማዎችን የተቀላቀለው የአጥቂ አማካዩ ኤልያስ ማሞ በአዲሱ ክለብ መለያ እስካሁን የገጎላ ተፅእኖ መፍጠር ባይችልም በ18ኛ ሳምንት ቡድኑ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር 1-1 በተለያየበት ጨዋታ ላይ እጅግ አስደናቂ ብቃቱን ያሳየበት ምሽት ነበር።

በሁለቱም አጋማሾች ከወትሮው የተሻሻለ አዳማ ከተማን በተመለከትንበት የሆሳዕናው ጨዋታ ኤልያስ ማሞ አብዲሳ ጀማል ያስቆጠራትን ኳስ አመቻችቶ ከማቀበል ባለፈ በአጥቂዎች ደካማ ውሳኔ ግብ መሆን ሳይችሉ የቀሩ ሦስት እጅግ አደገኛ የነበሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችሏል።

ገና ክለቡን እደተቀላቀለ የአምበልነት ኃላፊነቱን የተረከበው ተጫዋቹ ቡድኑ በሊጉ ለመቆየት በሚያደርገው ጥረት በተለይ ዕድሎችን እየፈጠረ ከጨዋታዎች አዎንታዊ ውጤትን ይዘው ለመውጣት የኤልያስ ማሞን መሰል ከፍ ያሉ ብቃቶችን በተደጋጋሚ የሚሹ ይሆናል።

👉 4 የውጭ ተጫዋቾችን በመጀመሪያ ተሰላፊነት

ላለመውረድ እየታገለ የሚገኘው አዳማ ከተማ በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ያስፈረማቸውን አራት የውጪ ሀገራት ተጫዋቾችን ለመጀመሪያ ጊዜ በጋራ ከሀዲያ ሆሳዕናን በገጠሙበት ጨዋታ ተጠቅሟል።

ላለመውረድ እጁ ላይ ያሉትን ካርዶች በሙሉ እየጣለ የሚገኘው አዳማ ከተማ ሳኩራ ካማራ (ግብጠባቂ) ፣ ኦቢሳ ጆናታን(የመሀል ተከላካይ) ፣ ላሚን ኩማር(ተከላካይ አማካይ) ፣ ማማዱ ኩሊባሊ(አጥቂ) በጋራ ባሳለፈበት ጨዋታ እንደቡድን በተወሰነ መልኩ የተሻሻለውን አዳማን ተመልክተናል።

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ተፅዕኗቸው እየቀነሰ የመጡት የውጭ ሀገራት ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾችን ከሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ አራት የውጭ ተጫዋቾች በጋራ በመጠቀም በሊጉ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ።

👉ራሱን በድቻ ቤት ፈልጎ እያገኘ የሚገኘው ስንታየሁ መንግሥቱ

ከሁለት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በአርባምንጭ ከተማ ቤት እጅግ ድንቅ እንቅስቃሴን በማሳየት የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ያጠናቀቀው ስንታየሁ መንግሥቱ በተሰረዘው የውድድር ዘመን ወደ ባህር ዳር ከተማ ቢያመራም በቂ የመሰለፍ ዕድል ማግኘት ባለመቻሉ የሚጠበቀውን ያህል ግልጋሎት ሳይሰጥ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ወደ ወላይታ ድቻ ማምራቱ ይታወቃል።

ተጫዋቹ በወላይታ ድቻ ቤት በጎሎች የታጀበ መልካም አጀማመር ቢያደርግም በጉዳት በርካታ ሳምንታትን ከሜዳ ለመራቅ ተገዷል። ከጥቂት ሣምንታት በፊት ከወልቂጤ ከተማ ጋር በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታድየም ባደረጉት ጨዋታ ወደ ሜዳ በተመለሰበት ጨዋታ ግሩም ግብን ማስቆጠሩ ይታወሳል።

ቡድኑ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ድሬዳዋ ከተማን ሲረታ ተጫዋቹ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። በዚህም ዕምነት አሳድረው የመሰለፍ ዕድልን እየሰጡት ለሚገኙት ወላይታ ድቻዎች በቂ ምላሽ እየሰጠ መሆኑ ታይቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ