“የትናንትናው ጨዋታ ለመካስ የገባሁበት ነበር” አስቻለው ታመነ

በሸገር ደርቢ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለ ድል ያደረገችውን ጎል ያስቆጠረው አስቻለው ታመነ በተለያዩ ጉዳዩች ዙርያ አስተያየቱን አጋርቶናል።

በደደቢት ባሳየው እንቅስቃሴ የእግርኳስ ቤተሰቡ ዓይን ውስጥ የገባውና በማስከተል ፈረሰኞቹን የተቀላቀለው የኃላ ደጀኑ አስቻለው ታመነ በየዓመቱ በሚያሳየው ወጥ አቋም ከክለቡ አልፎ የብሔራዊ ቡድን ወሳኝ ተከላካይ ሆኖ ዘልቋል። በዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ሳምንታቶች አካባቢ ከዚህ ቀደም በሚታወቅበት አቋሙ አለመገኘቱን ተከትሎ በብዙዎች ዘንድ ግርታን ፈጥሮ መቆየቱ ይታወቃል። ሆኖም በተለይ በብሔራዊ ቡድን እና የቅዱስ ጊዮርጊስ የቅርብ ጨዋታዎች አንስቶ ወደ ቀድሞ አቋሙ እየተመለሰ የመምጣቱ ማሳያ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን አስመልክቶናል። በትናንቱ የሸገር ደርቢ ወሳኝ ጨዋታ የጊዜው ወሳኝ አጥቂ አቡበከርን ከመቆጣጠር በተጓዳኝ ቡድኑን ወደ አሸናፊነት እንዲመለስ ያስቻለች ወሳኝ ጎል በግንባር በመግጨት አስቆጥሯል። ይህች ጎልን ለአስቻለውም በሸገር ደርቢ ያስቆጠራት የመጀመርያ ጎሉም ሆና ተመዝግባለች።

ሶከር ኢትዮጵያ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የተለያዩ ጥያቄዎች ለአስቻለው ታመነ በማቅረብ ምላሹን እንዲህ አቅርባዋለች።

በአንዳንድ ጨዋታዎች ላይ ባለፉት ዓመታት በነበረው አቋምህ ላይ ያልነበርክበት ምክንያት ምንድነው ?

አዎ የጤናዬ ሁኔታ ጥሩ አልነበረም። ረዥም ጊዜ ከዕረፍት ስለመጣሁ ስመለስ በተለይ አንደኛው ዙር ላይ ከቡና ጋር ስንጫወት ምንም ጤነኛ አልነበርኩም። በአሰልጣኞቹ ግፊት መርፌ ተወግቼ ነበር የተጫወትኩት፤ ብሽሽቴን በጣም ያመኝ ነበር። ትንሽ ሰውነቴም ጨምሮ ነበር። በደጋፊ ፊት መጫወት ከመልመዴ አንፃር ይህን ማጣቱ እና ሌሎች ነገሮች ተደራርበው ትንሽ ወደ ራሴ ትክክለኛ አቋም ለመመለስ አስቸግሮኝ ነበር። አሁንም ቢሆን ጥሩ ነኝ ብዬ መናገር አልችልም። ያው ከባህር ዳር ጀምሮ የተሻሻሻለ ነገር እያሳየው እገኛለሁ። የጤናዬም ሁኔታ አሁን ሙሉ ለሙሉ እየተመለሰ ነው። ከዚህ በኃላ ባሉት ቀሪ ጨዋታዎች ወደ ትክክለኛው አቋም እገባለሁ። ለኔ ይታወቀኛል፤ ሰው ስላወራ አይደለም። የተወሰነ መቀዛቀዝ ነበረብኝ። ከባህር ዳር ጀምሮ ለኔ ይታወቀኛል በሒደት ጥሩ ለወጥ እያመጣሁ እንደምገኝ።

አሁን ቀድሞ የምናውቀው አስቻለው እየተመለሰ ነው ?

ትክክለኛው አስቻለው ሙሉ ለሙሉ አልተመለሰም። በሚገባ ለመመለስ በቀሪው የሊግ ውድድር በሚገባ ራሴን አሳያለሁ። ማለት ሰው ወደሚጠብቀኝ አቋም እገባለሁ። ምክንያቱም ትልቅ ተጫዋች እንደመሆኔ መጠን ህዝቡ ከእኔ ብዙ ነገር ይጠብቃል። እና ያንን ስላላገኙ ነው ብዙ ጊዜ አስተያየቶች ይስጡ የነበሩት። ከዚህ በኃላ ከእኔ የሚጠበቀውን በተሻለ ለማሳየት እሞክራለሁ። አሁን ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም 80% ራሴን አግኝቸዋለው።

የትናንቱ ድል ትርጉሙ ምንያህል ነው ?

የሸገር ደርቢ ጨዋታ ከአዲስ አበባ ውጭ መካሄዱ አንድ ታሪክ ነው። ይህንን አጋጣሚ ቡድናችን በድል መወጣታችን በራሱ አንድ ታሪክ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በኔ ጎል ማሸነፋችን እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል። አንደኛ ካስወቀሱኝ ነገሮች አንዱ በአንደኛው ዙር ላይ የነበረኝ አቋም ነው። በተለይ ከቡና ጋር በነበረው ጨዋታ ደጋፊው ብዙ ነገር ይጠብቅ ነበር። ያኔ በሙሉ ጤናዬ ስላልተጫወትኩ የትናንትናው ጨዋታ ያንን ለመካስ የገባሁበት ነበር። እውነት ለመናገር ከጨዋታው በፊት እንደምናሸንፍ በእርግጠኝነት ተናግሬ ነበር። ስለዚህ ራሴን ለማግኘት የተጫወትኩበት ስለሆነ ውጤቱ ትርጉሙ ከፍተኛ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ቡድኔ ወደ አሸናፊነት የተመለሰበት እና ለቀጣይ ጨዋታ ለምናደርገው ጉዞ ተነሳሽነትን የሚጨምር ነው።

ውጤቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለአፍሪካ መድረክ የሚያበቃውን ደረጃ ለማግኘት ለሚያደርገው ፉክክር ምን አስተዋፆ አለው ?

በመጀመርያ ወደ ሙድ የምትመጣበት ነው። አንዳንዴ ከሙድ ስትወጣ ከውጤት ትርቃለህ። አሁን ያለፉትን አራት ዓመት ተቸግረናል። በተለያዩ አሳማኝ ባልሆኑ ምክንያቶች ከዋንጫ ርቀናል። ደጋፊዎቻችን በአፍሪካ መድረክ ላይ ቡድናቸውን ማየት ይፈልጋሉ። ስለዚህ ዘንድሮ ያለን አማራጭ ሁለተኛ ሆኖ መጨረስ ዕድል ያለው በመሆኑ ይህን ዕድል ለማሳካት ቆርጠን ተነስተናል። በቀሪ ጨዋታዎች ትኩረታችንን በማድረግ እንሳተፋለን ብዬ አስባለው።

የመጀመርያ የሸገር ደርቢ ጎሉ በማስቆጠርህ ምን ተሰማህ ?

ሸገር ድርቢ ላይ ጎል ማስቆጠር በጣም የተለየ ስሜት ነው ያለው። በሌሎች ጨዋታዎች ጎል ስታስቆጠር ትደሰታለህ። በደርቢ ላይ ግን ስታስቆጥር የተለየ ስሜት አለው። በተጠባቂው ጨዋታ ላይ የመጀመርያ ጎሌን በማስቆጠሬ እጅግ በጣም የተለየ ስሜት ፈጥሮብኛል።

ጌታነህ ከበደ ተቀይሮ ሲወጣ አንበልነትን ተረክበህ ነበር…

ለቅዱስ ጊዮርጊስ ከጌታነህ ከበደ ቀጥሎ ሁለተኛ አንበል ነኝ። ይህን ትልቅ ቡድን በአንበልነት መምራት ቀላል አይደለም። ጊዮርጊስ ትልቅ ክለብ ነው። ትላልቅ ተጫዋቾች የወጡበት ነው። ይህን ቡድን እነ አዳነ ግርማ፣ ደጉ ደበበ ሳምሶን ሙሉጌታ እና ሌሎችም ትልልቅ ተጫዋቾች በአንበልነት መርተውታል። ስለዚህ የኃላፊነት ጫና አለው። ኃላፊነቱ ከባድ ቢሆንም ይህን ኃላፊነት ለመወጣት ከቡድን አጋሮቼ ጋር በመሆን ጠንክረን እንሰራለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ