ቤትኪንግ የኢትዮጰያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ቁጥሮች እና ዕውነታዎች

በአስራ ዘጠነኛው ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጰያ ፕሪምየር ዙርያ ቁጥራዊ መረጃዎች እና ዕውነታዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።

የጎል መረጃዎች

– በዚህ ሳምንት በተደረጉት ስድስት ጨዋታዎች 16 ጎሎች ተቆጥረዋል። ካለፈው ሳምንት በአራት ከፍ ያለ የጎል ቁጥርም ተመዝግቧል።

– ከአስራ ስድስቱ ጎሎች መካከል ዘጠኝ ጎሎች የተቆጠሩት ከዕረፍት በፊት ሲሆን ሰባት ጎሎች ደግሞ ከዕረፍት በኋላ ተቆጥረዋል።

– በዚህ ሳምንት ከተቆጠሩ ጎሎች አንዱም በፍፁም ቅጣት ምት አልተቆጠረም።

– የድሬዳዋ ከተማው ዳንኤል ኃይሉ በዚህ ሳምንት የተገኘውን አንድ የፍፁም ቅጣት ምት መትቶ በባህር ዳር ከተማው ፅዮን መርዕድ ተመልሶበታል።

– ይህ ሳምንት በርካታ ጎሎች ከቆሙ ኳሶች መነሻነት የተቆጠሩበት ሆኖ አልፏል። ሱራፌል ዐወል፣ ሄኖክ ኢሳይያስ እና ፍፁም ዓለሙ በቀጥታ ቅጣት ምት ግሩም ጎሎች ሲያስቆጥሩ ፀጋሰው ድማሙ በግንባሩ ገጭቶ ያስቆጠረውም ከቅጣት ምት የተሻማ ነበር። አስቻለው ታመነ እና ፍቃዱ ዓለሙ ያስቆጠሯቸው የማሸነፍያ ጎሎች በቀጥታ ከማዕዘን የተሻሙ ኳሶችን በግባራቸው ገጭተው ሲሆን ኦኪኪ አፎላቢ እና ሙጂብ ቃሲም ያስቆጠሯቸው ጎሎችም ከመጨረሻ ምት በፊት ንክኪዎች ቢኖራቸውም መነሻቸው ከማዕዘን ምት ነበር።

– ሄኖክ ኢሳይያስ እና ፍፁም ዓለሙ በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ በቅጣት ምት ጎል ማስቆጠር ችለዋል። ከዚህ ቀደም ዳዋ ሆቴሳ ሁለት የቅጣት ምት ጎሎች ማስቆጠሩ ይታወሳል።

– በዚህ ሳምንት ስድስት ኳሶች ከሳጥን ውጪ ተመትተው ወደ ጎልነት ተቀይረዋል።

– 15 ተጫዋቾች በጎል አስቆጣሪነት ስማቸውን አስመዝግበዋል። ጋናዊው የሰበታ ከተማ አጥቂ ኦሴይ ማውሊ በሁለት ጎል ከፍተኛው አስቆጣሪ ነው።

– አስቻለው ታመነ፣ ፍቃዱ ዓለሙ፣ ፀጋሰው ድማሙ፣ ኦሴይ ማውሊ፣ ቸርነት አውሽ፣ ደስታ ዮሐንስ እና ዘላለም ኢሳይያስ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ጎላቸውን አስቆጥረዋል።

የሳምንቱ ስታቶች

(ቁጥሮቹ የተገኙት ከሱፐር ስፖርት ነው)

ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ

ከፍተኛ – ሀዋሳ ከተማ (8)
ዝቅተኛ – ድሬዳዋ ከተማ (2)

ጥፋቶች

ከፍተኛ – ጅማ አባ ጅፋር (23)
ዝቅተኛ – ሀዋሳ ከተማ (9)

ከጨዋታ ውጪ

ከፍተኛ – ወልቂጤ እና ሰበታ (7)
ዝቅተኛ – ቡና እና ሲዳማ (0)

የማዕዘን ምት

ከፍተኛ – ባህር ዳር ከተማ (9)
ዝቅተኛ – ወልቂጤ ከተማ (0)

የኳስ ቁጥጥር ድርሻ

ከፍተኛ – ኢትዮጵያ ቡና (63%)
ዝቅተኛ – ቅዱስ ጊዮርጊስ (37%)

የዲሲፕሊን ቁጥሮች

– በዚህ ሳምንት 24 የማስጠንቀቂያ ካርዶች ሲመዘዙ አንድ ቀይ ካርድ ተመዟል።

– የዚህ ሳምንት ቁጥር ካለፈው ሳምንት በ3 የቢጫ እና አንድ ቀይ ካርድ ያነሰ ሆኖ ተመዝግቧል።

– የኢትዮጵያ ቡናው ታፈሰ ሰለሞን (ሁለት ቢጫ) በዚህ ሳምንት ብቸኛው ተጫዋች ሆኗል።

-ባህርዳር ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ እንዲሁም ሲዳማ ቡና ከ ፋሲል ከነማ እያንዳንዳቸው 6 ቢጫ ካርድ በማስተናገድ ቀዳሚዎች ናቸው።

– ሲዳማ ቡና (4) ከፍተኛውን የካርድ ቁጥር ያስመዘገበ ቡድን ሲሆን ሀዋሳ ከተማ (0) ዝቅተኛውን ቁጥር አስመዝግቧል።

ጎል አስቆጣሪው አማካይ – ፍፁም ዓለሙ

የባህር ዳር ከተማው አማካይ አስደናቂ የጎል ማስቆጠር ጉዞ ቀጥሏል። በዚህ ሳምንት ጎል ያስቆጠረው ፍፁም የውድድር ዓመት የጎል ድምሩን ከወዲሁ ዘጠኝ ማድረስ የቻለ ሲሆን ይህም ከሌሎች አማካዮች በእጅጉ ልቆ እንዲቀመጥ አስችሎታል። ባለፉት አምስት የውድድር ዘመናት(ከ2007 ወዲህ) ከአማካይ ቦታ ተነስቶ በርካታ ጎል በማስቆጠር ፍፁም ዓለሙ የሚበለጠው በ2009 የውድድር ዓመት 10 ጎሎች ባስቆጠረው ፍሬው ሰለሞን (ሀዋሳ ከተማ) ብቻ ነው።

ሱራፌል ዳኛቸው እና ቢጫ ካርድ

የፋሲል ከነማው አማካይ ሱራፌል ዳኛቸው ከሲዳማ ቡና ጋር በተደረገው ጨዋታ የውድድር ዘመኑን አስረኛ የማስጠንቀቂያ ካርድ ተመልክቷል። ይህም ከሁሉም ተጫዋቾች ቀዳሚው የሚያደርገው ሲሆን ለሁለተኛ ጊዜ አምስት ቢጫ በመመልከቱ ምክንያት ቀጣይ 2 ጨዋታዎች የሚያልፉት ይሆናል።

ከቢጫ ካርድ ጋር በተያያዘ የሲዳማ ቡናው ብርሀኑ አሻሞ፣ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቤል ያለው እና የድሬዳዋ ከተማው ምንያምር ጵጥሮስ አምስተኛ ቢጫ ካርዳቸውን በመመልከታቸው ቀጣይ ጨዋታ ያልፋቸዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ