ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ የጨዋታ ሳምንት የተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾችን በዚህ የፅሁፋችን ክፍል ዳሰናቸዋል።

👉 በምርጥ አቋማቸው የዘለቁት ስንታየሁ እና ቸርነት

በፕሪምየር ሊጉ በወቅታዊ ምርጥ አቋም ላይ ከሚገኙ ተጫዋቾች መካከል የወላይታ ድቻዎቹ ስንታየሁ መንግሥቱ እና ቸርነት ጉግሳ ይጠቀሳሉ። ሁለቱ ተጫዋቾች በዚህ ሳምንት ቡድኑ ከሰበታ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ በሁለት ጎል ከመመራት ተነስተው አቻ እንዲወጡ ከፍተኛውን ሚና መወጣት ችለዋል።

ሰበታ ከተማዎች በመጀመርያዎቹ ሃያ ደቂቃዎች ባስቆጠሯቸው ጎሎች 2-0 ሲመሩ ከቆዩ በኋላ ወደ እረፍት ከማምራታቸው በፊት ስንታየሁ የመጀመርያ ጨዋታውን ካደረገው ኢዙ አዙካ ያሻገረውን ኳስ በግሩም ሁኔታ በግንባር ገጭቶ ልዩነቱን ማጥበብ ሲችል በ83ኛው ደቂቃ ደግሞ ቸርነት ጉግሳ ከስንታየሁ በጭንቅላት ተገጭቶ የተመቻቸለትን ኳስ ከሳጥን ውጪ በመምታት ድንቅ ጎል አስቆጥሮ ድቻ ከጨዋታው አቻ ውጤት ይዞ እንዲወጣ ማድረግ ችሏል።

ከዚህ ጨዋታ በፊትም በቡድኑ የድሬዳዋ ቆይታ በፈተናዎች ውስጥም ቢሆን ማንፀባረቃቸውን የቀጠሉት ሁለቱ ተጫዋቾች ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው እየጎላ መጥቷል። ለግላጋው አጥቂ ስንታየሁ በአደገኛ ዞኖች ላይ ሆኖ በሚወስናቸው ውሳኔዎች እንዲሁም ቸርነት ከመስመር ወደ መሐል እያጠበበ ወደ ውስጥ በመግባት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ለድቻ ጠንካራ ጎን ለተጋጣሚዎች ደግሞ ስጋት መሆናቸው የሚቀጥል ይመስላል።

👉 ግብ አግቢው ፀጋሰው ድማሙ

በሀገራችን እግርኳስ ግብ የማስቆጠር ኃላፊነቱን በአጥቂ መስመር ተሰላፊ ተጫዋቾች ላይ የተንጠለጠለ ይመስላል። ነገርግን ይህን ጫና በሌሎች የሜዳ ክፍሎች የሚገኙ ተጫዋቾች ሊጋሩት እንደሚገባ ይታመናል።

እንደ ቡድን ብዙ ግቦችን በማያስቆጥረው የሀዲያ ሆሳዕና ስብስብ ውስጥ በቅርቡ በተከታታይ ጨዋታዎች የመሰለፍ ዕድልን እያገኘ የሚገኘው የመሀል ተከላካዩ ፀጋሰው ድማሞ ከመከላከሉ ባለፈ ግብ የማስቆጠር ኃላፊነቱን እየተጋራ ያለ ይመስላል። ቡድኑ ባደረጋቸው የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ሁለት አስደናቂ የግንባር ኳሶችን ያስቆጠረው ተጫዋቹ ያስቆጠረባቸው መንገዶች የአየር ላይ ኳሶችን አጠቃቀሙ ምን ያህል አስደናቂ ስለመሆኑ የሚመሰክሩ ናቸው።

ተጫዋቹ በተለይ የቆሙ ኳሶችን ገጭቶ በማስቆጠር ረገድ በሀገራችን ብዙዎች ያልታደሉትን ይህን ብቃት የሚያሳድግ ከሆነ በእግርኳሳችን በጉድለትነት በሚነሳው በዚህ ሒደት ተጠቃሽ ተጫዋች ሊሆን ይችላል።

👉 ብርቱው ፍሬዘር ካሣ

በውድድር ዓመት ከጨዋታ ጨዋታ በርካታ ለውጦችን በተለይ በተከላካይ መስመሩ ላይ በሚያደርገው የድሬዳዋ ከተማ ቡድን ውስጥ በወጥነት ከተለያዩ ተጫዋቾች ጋር እየተጣመረ በተቻለው መጠን ቡድኑን እያገለገለ የሚገኘው ፍሬዘር ካሣ በዚህኛውም የጨዋታ ሳምንት ከሲዳማ ቡና ወሳኝ ሦስት ነጥብ ሲወስዱ የዚህ ተጫዋች ግልጋሎት እጅግ ከፍ ያለ ነበር።

በጨዋታው በሲዳማ ቡናዎች በኩል ልዩነት ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቅ የነበረውን አጥቂያቸውን ኦኪኪ አፎላቢን እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል መልኩ መቆጣጠር የቻለው ፍሬዘር የጊዜ አጠባበቁ ፣ የአየር ላይ ኳሶችን የሚያሸንፍበት መንገድ ብቻ በጥቅሉ ለቡድኑ በጨዋታው ወቅት መስጠት የሚችለው በሙሉ ማድረግ ችሏል።

👉 በጥሩ አቋም የተመለሰው ፕሪንስ ሰቨሪንሆ

በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ የምናውቀው ቡርኪናቤው የመስመር አጥቂ ፕሪንስ ሰቨሪንሆ በጅማ አባ ጅፋር ማልያ ወደ ሊጉ ተመልሷል። ባሳለፍነው ሳምንት ከሰበታ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ ተቀይሮ የገባው የመስመር አጥቂው የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ አንዳች መልካም ነገር እንደሚጨምር በዚያ ጨዋታ ምልክት ሰጥቶ ነበር።

በ20ኛው ሳምንት ጅማ አባ ጅፋር ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረገው ጨዋታ ደግሞ ተጫዋቹ ወደ ቀዳሚው አሰላለፍ መጥቷል። የቀድሞው ክለቡን በገጠመበት በዚህ ጨዋታም ፕሪንስ ጥሩ የጨዋታ ቀን አሳልፏል። ጅማ ነጥብ እንዲጋራ ያስቻለችውን ብቸኛ ግብ ተመስገን ደረሰ ሲያስቆጥር ኳሷን ከግራ መስመር ያሻማውም ይኸው ተጫዋች ነበር። ከግቧ ውጪም የቡድኑን መልሶ ማጥቃት ስል በማድራግ በተደጋጋሚ ከግራ የቡድኑ ክፍል የሚነሱ ኳሶች ነፍስ እንዲዘሩ የፕሪንስ መኖር ወሳኝ ነበር።

በጨዋታው ዕለት ከተጨዋቹ ብቃት በላይ ጀርባው ላይ በወረቀት ተፅፎ የተለጠፈው ስሙና የማልያ ቁጥሩ አነጋጋሪነት ትኩረት ይሳብ እንጂ በእንቅስቃሴው የፈጠረው ተፅዕኖ በጉልህ የሚታይ ነበር። የተጫዋቹ በዚህ ብቃት ላይ መገኘት ውጤት አብዝቶ ለሚያስፈልገው የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ቡድን እጅግ አስፈላጊ ነው። በቀጣይ ጨዋታዎች በተመሳሳይ አደገኛ የግብ ዕድሎችን መፍጠሩን ከቀጠለ እና ወደ አስቆጣሩነቱም ከመጣ ለጅማ ያለመውረድ ፍልሚያ ተስፋ ሊሆን ይችላል።

👉 የፈጣኖቹ ግቦች ባለቤት – ተመስገን ደረሰ

በጅማ አባጅፋር ቡድን ውስጥ በግሉ ጥሩ የውድድር ጊዜያትን እያሳለፈ የሚገኘው ሁለገቡ ተመስገን ደረሰ በዚህኛው ሳምንት ለሁለተኛ ጊዜ የውድድር ዘመኑን ፈጣን ግብ ማስቆጠር ችሏል።

አባ ጅፋር ከቀናት በፊት ሀዋሳ ከተማ ጋር አንድ አቻ በተለያየበት ጨዋታ የሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ከአንድ ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ጅማን ቀዳሚ ያደረገች ግብን ማስቆጠሩ የሚታወስ ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት እንደዚሁ ቡድኑ በቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ለባዶ እየተመራ ከመልበሻ ቤት እንደተመለሰ ከሃያ ሰከንድ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ጨዋታው በአራት ንክኪዎች ቡድኑን አቻ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ታታሪው ተጫዋች በእስካሁኑ የሊጉ ጉዞ ሁለተኛ አጋማሽ ከተጀመረ ከአንድ ደቂቃ ባነሱ ሰከንዶች ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ታሪክ ሰርቷል።

👉 ራሱን በሚገባ እያሳየ የሚገኘው አብዲሳ ጀማል

እጅግ ደካማ የውድድር ዘመን እያሳለፈ በሚገኘው እና በሊጉ ግርጌ በተቀመጠው አዳማ ከተማ ውስጥ በግሉ ግን በተለየ እጅግ መልካም የሚባል የውድድር ጊዜያትን እያሳለፈ ይገኛል። ወጣቱ አጥቂ አብዲሳ ጀማል።

የከፍተኛ ሊግ ተካፋይ የሆነውን ሻሸመኔ ከተማን ለቆ በክረምቱ አዳማ ከተማን የተቀላቀለው አጥቂው በመጀመሪያ ዓመት የፕሪምየር ሊግ ቆይታው እስካሁን ሰባት ግቦችን ሲያስቆጥር በእንቅስቃሴ ደረጃ ደግሞ የተሟላ አጥቂ ለመሆን የሚያበቁ ባህሪያትን የተላበሰ ስለመሆኑ እያስመሰከረ ይገኛል።

አንድ አጥቂ ሊያሟላ የሚገባው አስደናቂ ፍጥነትን ከጥሩ የአጨራረስ ብቃት የተላበሰው ተጫዋቹ በመስመር አጥቂነት በሚጀምርባቸው ጨዋታዎች ደግሞ በመከላከሉ ወቅት በጥልቀት ወደ ኋላ እየተሳበ የመስመር ተከላካዮችን የሚያግዝበት መንገድ ልዩ ነው። ተጫዋቹ በጥሩ አሰልጣኝ የሚደገፍ ከሆነ በቀጣይ ይበልጥ ራሱን እያሻሻለ በመሄድ በቀጣይ በሀገሪቱ ከሚገኙ ጥሩ አጥቂዎች ተርታ ለመመደብ የሚያበቁ ግብአቶችን በአንድ የያዘ ተጫዋች ነው።

ነገሮች በዚሁ የሚቀጥሉ ሆነው አዳማ ከተማ ከሊጉ ከተሰናበተ አብዲሳ ጀማል የተለየ ነገር እስካልተፈጠረ ድረስ በቀጣይ ዓመት በፕሪምየር ሊጉ በትልቅ ደረጃ የምንመለከተው አጥቂ እንደሚሆን አያጠራጥርም።

👉በመጀመሪያ የኳስ ንክኪው ግብ ያስቆጠረው በላይ ዓባይነህ

በ20ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዳማ ከተማዎች ከወልቂጤ ከተማ አቻቸው ጋር ነጥብ ተጋርተው እንዲወጡ ያስቻለው በላይ ዓባይነህ በእግርኳስ ህይወቱ ከማይረሳቸው ቀናት አንዱን አሳልፏል ቢባል ማጋነን አይሆንም።

በጨዋታ ዕለት ስብስብ ውስጥ ተጠባባቂ በመሆን ጨዋታውን የጀመረው የመስመር አጥቂው በላይ ቡድኑ 1-0 እየተመራበት በነበረው ጨዋታ 90ኛው ደቂቃ ላይ ከወልቂጤ ግብ ትይዩ በሳጥን ጠርዝ አካባቢ የቅጣት ምት ባገኙበት ቅፅበት በቃሉ ገነነን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው አጥቂው በመጀመሪያው የኳስ ንክኪ የቅጣት ምቷን በግሩም ሁኔታ በመምታት ቡድኑን አቻ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ከዚህ ቀደም እንዲሁ በተመሳሳይ የሊጉ ውድድር አዲስ አበባ ላይ ሰበታ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና ባደረጉት ጨዋታ ላይ ቃልኪዳን ዘላለም ለሰበታ እንዲሁም በጅማ ዩኒቨርስቲ በተደረገው የባህርዳር ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ ላይ ሣላአምላክ ተገኘ ለባህር ዳር በመጀመርያ የኳስ ንክኪ ማስቆጠር መቻላቸው ይታወሳል።

👉 “ዮሐንስ” በርታ ተመልሷል

በ2011 የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባደገበት ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊግ በተመለሰው የደቡብ ፖሊስ ቡድን ውስጥ ባሳየው አስደናቂ ብቃት የበርካታ ክለቦች ዓይን አርፎበት የነበረው ተከላካይ አማካዩ ዮናስ በርታ ከበርካታ ውጣ ውረዶች በኋላ ዳግም ሜዳ ተመልክተነዋል።

በተሰረዘው የአምናው የውድድር ዘመን ደቡብ ፖሊስን ለቆ በርካታ የመሀል አማካዮችን ባሰባሰበው የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለው አዳማ ከተማ በቂ የመሰለፍ ዕድልን ያላገኘው ተጫዋቹ በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ወደ ወልዋሎ ቢያመራም በቂ ጨዋታዎችን ሳያደርግ የውድድር ዘመኑ መሰረዙ የሚታወስ ሲሆን የዘንድሮውንም የውድድር ዘመን እግርኳሳዊ ባልሆነ ምክንያት ሜዳ ርቆ መቆየቱ ይታወሳል።

በቅርቡ ወልቂጤ ከተማን የተቀላቀለው አማካዩ ቡድኑ ከአዳማ ከተማ ጋር አቻ በተለያየበት ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት ከረጅም ጊዜያት በኃላ በሜዳ ላይ ሲጫወት ተመልክተነዋል። በዚህ ወቅትም በአዲሱ ክለቡ በለበሰው መለያ ላይ ስሙም በስህተት “ዮሐንስ” ተብሎ መፃፉ እንዲሁ ወደ ሜዳ ከመመለሱ ባልተናነሰ ትኩረትን የሳበ ጉዳይ ነበር።

👉 ቢኒያም በላይ ዳግም በፕሪምየር ሊጉ

በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ፈጣን እምርታን ካሳዩ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ቢኒያም በላይ በጥቂት ዓመታት ከድሬዳዋ የአሸዋ ሜዳ እስከ አውሮፖ ሊጎች የደረሰበት ፈጣን ዕድገት እጅግ አስገራሚ ነው። ከጀርመን የእግርኳስ ፌደሬሽን ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን የቴክኒካዊ ድጋፍ አካል በነበሩት ጀርመናዊዉ ዩሀኪን ፊከርት ድጋፍ ከዕድሜው የፈጠነ ዕድገት ያሳየው ተጫዋቹ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመለሰውን ዝውውር ከሳምንታት በፊት መፈፀሙ ይታወሳል።

በ20ዐ9 የኢትዮጵያ ፕሪምየር በመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ተረቶ ከፕሪምየር ሊጉም ከኢትዮጵያ እግርኳስም ላይ ከጠፋበት የመጨረሻ ጨዋታ በኋላ ሲዳማ ቡና ድሬዳዋ ከተማን በገጠመበት ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ የሲዳማ ቡናን መለያ ለብሶ በፕሪምየር ሊጉ ተመልክተነዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ