ቤትኪንግ የኢትዮጰያ ፕሪምየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ቁጥሮች እና ዕውነታዎች

በቤትኪንግ የኢትዮጰያ ፕሪምየር 22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዙርያ ያሰናዳነውን ቁጥራዊ መረጃ እና ዕውነታ እነሆ።

የጎል መረጃዎች

– በዚህ ሳምንት በተደረጉት ስድስት ጨዋታዎች 6 ጎሎች ብቻ ተቆጥረዋል። በአማካይ በጨዋታ አንድ ግብ ብቻ የተስተናገደበት ይህ ሳምንት የውድድር ዘመኑ ዝቅተኛ ቁጥር ሲሆን ካለፈው ሳምንት በሰባት ጎሎች ዝቅ ያለ ቁጥር ሆኗል።

– ከስድስቱ ጎሎች መካከል አራት ጎሎች የተቆጠሩት ከዕረፍት በኋላ ሲሆን ሁለት ጎሎች ደግሞ ከዕረፍት በፊት ተቆጥረዋል።

– በዚህ ሳምንት ከተቆጠሩ ጎሎች መካከል አንዱ በፍፁም ቅጣት ምት ተቆጥሯል። የሀዋሳ ከተማው መስፍን ታፈሰ ብቸኛው ጎል አስቆጣሪ ሲሆን ሳላዲን ሰዒድ እና ሀብታሙ ሸዋለም ፍፁም ቅጣት ምት ያመከኑ የዚህ ሳምንት ተጫዋቾች ናቸው።

– አምስት ተጫዋቾች በጎል አስቆጣሪነት ስማቸውን አስመዝግበዋል። መስፍን ታፈሰ ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር ቀሪዎቹ ተጫዋቾች አንድ አንድ ጎል አስቆጥረዋል።

– በዚህ ሳምንት የተቆጠሩት ሁሉም ኳሶች ከሳጥን ውስጥ ተመትተው ወደ ጎልነት የተቀየሩ ናቸው።

የሳምንቱ ስታቶች

(ቁጥሮቹ የተገኙት ከሱፐር ስፖርት ነው)

ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ

ከፍተኛ – ሀዋሳ ከተማ ( 10)
ዝቅተኛ – ሰበታ፣ ሆሳዕና፣ ድቻ (1)

ጥፋቶች

ከፍተኛ – ሲዳማ ቡና (26)
ዝቅተኛ – ኢትዮጵያ ቡና (5)

ከጨዋታ ውጪ

ከፍተኛ – ድሬዳዋ ከተማ (6)
ዝቅተኛ – ወልቂጤ ከተማ (0)

የማዕዘን ምት

ከፍተኛ – ሀዋሳ ከተማ (6)
ዝቅተኛ – ሀዲያ ሆሳዕና (1)

የኳስ ቁጥጥር ድርሻ

ከፍተኛ – ኢትዮጵያ ቡና (72%)
ዝቅተኛ – ወላይታ ድቻ (28%)

የዲሲፕሊን ቁጥሮች

– በዚህ ሳምንት 25 የማስጠንቀቂያ ካርዶች ሲመዘዙ አንድ ቀይ ካርድ ተመዟል።

– የዚህ ሳምንት ቁጥር ካለፈው ሳምንት በ7 የቢጫ ካርድ ከፍ ያለ ነው።

– የአዳማ ከተማው ላሚን ኩማሬ (ሁለት ቢጫ) በዚህ ሳምንት ብቸኛው የቀይ ካርድ ሰለባ የሆነ ተጫዋች ሆኗል።

– አዳማ ከተማ ከተማ 5 ቢጫ ካርድ በማስተናገድ ቀዳሚ ሲሆን ሰበታ፣ ሲዳማ፣ ሀዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ እና ድቻ (1) ዝቅተኛውን ቁጥር አስመዝግበዋል።

– የፋሲሉ ከድር ኩሊባሊ እና የድቻው በረከት ወልዴ በአምስት ቢጫ ቀጣዩ ጨዋታ የሚያልፋቸው ተጫዋቾች ናቸው።

ፋሲል ከነማ

ፋሲል ከነማ በዚህ ሳምንት አራት ጨዋታ እየቀረው ቻምፒዮንነቱን ማረጋገጡ ይታወሳል። ከወልቂጤ ከተማ ባደረገው ጨዋታም የክብር ዘብ ተደርጎለት ወደ ሜዳ ገብቷል። ይህ በፕሪምየር ሊጉ ሲከሰትም ከሦስት የውድድር ዘመናት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ሆኗል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ግንቦት 11 ቀን 2009 ሁለት ጨዋታ እየቀረው ቻምፒዮን መሆኑን ማረጋገጥ የቻለ ሲሆን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ያደረገው የ30ኛ ሳምንት ጨዋታም በክብር ዘብ ወደ ሜዳ የገባበት የመጨረሻ ጨዋታ ሆኖ ተመዝግቧል።

በ2010 እና 2011 በመጨረሻ ጨዋታ ላይ አሸናፊ ቡድኖች የተለዩ ሲሆኑ ባለፈው ዓመት በኮሮና ምክንያት መሰረዙ ይታወሳል።

ወልቂጤ ከተማ

ወልቂጤ ከተማዎች በዘንድሮው የውድድር ዘመን ለመጀመርያ ጊዜ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። አምና ሊጉ እስኪቋረጥ ድረስ በስሑል ሽረ አምስት የፍፁም ቅጣት ምቶችን የመታው ሀብታሙ ሁሉንም ወደ ጎልነት የለወጠ ሲሆን ዘንድሮ ቡድኑ ያገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ሚኬል ሳማኬ እና ከድር ኩሊባሊ

እስከ 21ኛው ሳምንት ድረስ ፋሲል ከነማ ያደረጋቸውን እያንዳንዱ ደቂቃቃዎችን በሜዳ በመቆየት ያከናወኑት ተጫዋቾች ከድር ኩሊባሊ እና ሚኬል ሳማኬ ናቸው። በዚህ ሳምንት ቡድኑ የሊጉን አሸናፊነት ማረጋገጡን ተከትሎ ማሊያዊው የግብ ዘብ ሚኬል ሳማኬ ለመጀመርያ ጊዜ በተጠባባቂ ወንበር ላይ የተቀመጠ ሲሆን ይድነቃቸው ኪዳኔ ተክቶት ተጫውቷል።

ሌላው ቡድኑን በወጥነት ያገለገለው አይቮሪኮስታዊው ተከላካይ ከድር ኩሊባሊ ከወልቂጤ በተደረገው ጨዋታ ላይ የውድድር ዘመኑ አምስተኛ ቢጫ በመመልከቱ በዚህ ዓመት ለመጀመርያ ጊዜ ቀጣዩ የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ያልፈዋል።

የጎል ድርቅ

በዚህ ሳምንት በተደረጉት ስድስት ጨዋታዎች የተቆጠሩት ጎሎች ብዛት ስድስት ብቻ ነው። ይህ ቁጥር የዘንድሮ የውድድር ዘመን ዝቅተኛው የጎል መጠን ሲሆን ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት እንዲህ አይነት ድርቅ ቢከሰትም ለመጨረሻ ጊዜ ሊጉ በዚህን ያህል መጠን በጎል ድርቅ ተመትቶ የነበረው በ2010 የውድድር ዘመን 29ኛው ሳምንት ነበር። በወቅቱ በስምንት ጨዋታ አምስት ጎሎች ብቻ ተቆጥረው ነበር።

© ሶከር ኢትዮጵያ