ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | 22ኛ ሳምንት ምርጥ 11

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ ምርጥ አቋማቸውን ያሳዩ ተጫዋቾችን እንዲህ መርጠናል።

አሰላለፍ 4-3-3

ግብ ጠባቂ

ይድነቃቸው ኪዳኔ – ፋሲል ከነማ

ፋሲል ከነማ የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱን ካረጋገጠ በኋላ ባደረገው የዚህ ሳምንት ቀዳሚ ጨዋታው ይድነቃቸው የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ የመሰለፍ ዕድል አግኝቷል። በጨዋታው የቡድኑን እንቅስቃሴ በእግሩ ቅብብሎችን በመከወን ከማገዙ እና ወደ ግብ የተላኩ ኳሶችን ከማምከን ባለፈ የሀብታሙ ሸዋለምን ፍፁም ቅጣት ምት በማዳን ልዩነት መፍጠር ችሏል።

ተከላካዮች

አብዱልከሪም መሐመድ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በግራ መስመር ተከላካይነት ጨዋታውን ያደረገው አብዱልከሪምን በሁለቱም መስመሮች መጫወት መቻሉን ከግምት በማስገባት በቀኝ መስመር ተከላካይነት ተጠቅመነዋል። ተጫዋቹ በባህር ዳሩ ጨዋታ ከፍ ያለ የማጥቃት ተሳትፎ በማድረግ ሳጥኑ ደረስ ይሄድ የነበረ ሲሆን የከነዓን ጎል እንዲቆጠር መነሻ መሆን ሲችል የቡድኑን ድል ያረጋገጠውን ሁለተኛውን ግብ ደግሞ ራሱ አስቆጥሯል።

ያሬድ ባየህ – ፋሲል ከነማ

የተረጋጋው የመሀል ተከላካይ ሌላ ጥሩ በቃት ያሳየበትን ዘጠና ደቂቃ አሳልፏል። እንደሁል ጊዜው እንደመሀል ተከላካይ እና አምበል ጥሩ አመራር ሲሰጥ የነበረው ያሬድ የቆሙ ኳሶችን በመከላከል ፣ የቡድኑን የኳስ ፍሰት ከኋላ በማስጀመር እና እንደ እስራኤል እሸቱ ያሉ የተጋጣሚውን አጥቂዎች በመቆጣጠር ቡድኑ ግብ እንዳያስተናግድ ውጤታማ ጥረት አድርጓል።

ደስታ ደሙ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በተከታታይ ጨዋታዎች የቡድኑ የመከላከል መስመር ላይ የመሰለፍ ዕድል ያገኘው ደስታ ደሙ በዚህ ሳምንት ጥሩ አበርክቶት ነበረው። አደጋ ሊጥሉ የሚችሉ እንቅስቃሴዎችን ከቦታው ወጣ እያለ ከመራቅ ባለፈ የባህር ዳር አጥቂዎች ልዩነት እንዳይፈጥሩ በሙሉ ጨዋታው ቦታው በሚጠይቀው ትኩረት ላይ በመገኘት ሊቆጣጠሯቸው ችሏል።

መሐሪ መና – ሲዳማ ቡና

ብዙ ጎሎች ባልተቆጠሩበት በዚህ ሳምንት ደካማ እንቅስቃሴ ከተደረገባቸው ጨዋታዎች መሀከል የሲዳማ ቡና እና የሰበታ ከተማ ጨዋታ አንዱ ነው። ይሁን እንጂ የሲዳማው የግራ መስመር ተከላካይ መሀሪ ቡድኑ ወደ ፊት ሄዶ አደጋ ለመጣል በሞከረባቸው አጋጣሚዎች ወደ ፊት ገፍቶ በመሄድ ያደርግ የነበረው ጥረት በቦታው ካሉ የሌሎች ቡድኖች ተሰላፊዎች መሀል ተመራጭ አድርጎታል።

አማካዮች
ናትናኤል ዘለቀ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ዳግም ወደ አሰላለፍ የተመለሰው ናትናኤል በሳምንቱ በተከላካይ አማካይነት ከተሰየሙ ተጫዎች ጋር ሲነፃፀር የተሻለውን እንቅስቃሴ አድርጓል። ተጋጣሚው ባህር ዳር ከተማ አደገኛ በሆነበት እና የፍፁም ዓለሙ ተፅዕኖ በሚጎላበት ከተከላካይ መስመር ፊት ባለው ቦታ ላይ ወሳኝ ተጫዋቾችን በመቆጣጠር እና ቡድኑ በእርጋታ ማጥቃቱን እንዲጀምር በማድረግ የበኩሉን አድርጓል።

ወንድማገኝ ኃይሉ – ሀዋሳ ከተማ

ወጣቱ አማካይ አሁንም ድንቅ ብቃቱን በማሳየቱ ገፍቶበታል። እንደተለመደው ከሰጥን ሳጥን በታታሪነት በተንቀሳቀሰበት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እና የሀዲያን ተጫዋቾች መከላከል ለማስከፈት ያደረገው ጥረት ሰምሮለትም በሦስት ተጫዋቾች መሀል ሆኖ በልዩ ክህሎት ሳጥን ውስጥ ገብቶ መስፍን ታደሰ ያስቆጠረውን ኳስ ማመቻቸትም ችሏል።

ከነዓን ማርክነህ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከአሰልጣኝ ፍራንክ ናታል መምጣት በኋላ ተደጋጋሚ የመሰለፍ ዕድል እያገኛ ያለው ከነዓን ዳግም ራሱን ለማግኘት ጉዞ የጀመረ ይመስላል። ጎልቶ በታየበት የባህር ዳሩ ጨዋታ የቡድኑን የማጥቃት ዑደት በዋነኝነት የመራ ሲሆን በሁለት አጋጣሚዎች ከባድ ሙከራ አድርጎ ባይሳካለትም በመጨረሻ ቡድኑን መሪ ያደረገች ወሳኝ ግብ አስቆጥሯል።

አጥቂዎች

ኤፍሬም አሻሞ – ሀዋሳ ከተማ

በሀዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ ኤፍሬም ለሀዋሳ የሁል ጊዜ የመስመር እንቅስቃሴ ብልጫ እና ለጨዋታውም ድል ወሳኝ ሚና ነበረው። በሁለት አጋጣሚዎች ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ሲያደርግ የመስፍን ታፈሰ ጎል እንዲቆጠርም ከፍ ያለ አስተዋፅዖ አድርጓል። በመጨረሻም የቡድኑን የማሳረጊያ ጎል ከመረብ አገናኝቷል።

ሽመክት ጉግሳ – ፋሲል ከነማ

የሽመክት ጉግሳ የውድድር ዓመቱ ያልተዛነፈ ታታሪነት አሁንም እንደቀጠለ ነው። በወልቂጤው ጨዋታ እንደወትሮው ከመስመር በመነሳት የፋሲል ከነማ ዋነኛ የጥቃት አማራጭ ሆኖ ሲያገለግል ተጋጣሚው ጥሩ የሆነበትን የግራ መስመር ጥቃት በማፈኑም ድርሻ ነበረው። ከዚህ በተጨማሪ አሸናፊ ያደረገቻቸውን ግብ ትክክለኛው ቦታ ላይ ተገኝቶ በማስቆጠር ቻምፒዮንነታቸውን በሌላ ድል እንዲያደምቁ መድረግ ችሏል።

መስፍን ታፈሰ – ሀዋሳ ከተማ

ከሜዳም ከግብ አስቆጣሪነትም ርቆ የቆየው መስፍን በ20ኛው ሳምንት ሀዲያ ሆስዕና ላይ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። የነበረውን ተፅዕኖ ሙሉዕ እንዲሆንም ሦስተኛውን የኤፍሬም አሻሞ ጎል ከቀኝ መስመር በመነሳት ማቀበል ችሏል። መስፍን ለሁሉም ግቦች መነሻ መሆን በመቻሉም በምርጫችን ሊካተት ችሏል።

አሰልጣኝ 

ፍራንክ ናታል – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከቡድን ውጤት መጥፋት እንዲሁም ከተጫዋቾች የሜዳ ላይ ብቃት እና የሜዳ ውጪ ጉዳዮች መሀል ጥሩ ጊዜ ላይ ያልነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህ ሳምንት ከጨዋታ ብልጫ ጋር ወሳኝ ሦስት ነጥቦችን ማሳካት ችሏል። ከዚህ ስኬት ጀርባ የነበሩት ስኮትላንዳዊው አሰልጣኝም የተጋጣሚያቸውን ጠንካራ ጎኖች ከማክሰም እና የተሻለ ቅርፅ ያለው ቡድን ከመቅረባቸው አንፃር የሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኝ አድርገን መርጠናቸወዋል።

ተጠባባቂዎች

አቤል ማሞ (ኢትዮጵያ ቡና)
በረከት ሳሙኤል (ድሬዳዋ ከተማ)
ብርሀኑ በቀለ (ሀዋሳ ከተማ)
ጋቶች ፓኖም (ወላይታ ድቻ)
ሱራፌል ዳኛቸው (ፋሲል ከነማ)
አቤል ያለው (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
አቡበከር ናስር (ኢትዮጵያ ቡና)

© ሶከር ኢትዮጵያ