የኢትዮጵያ የሴት የዕድሜ እርከን ቡድኖች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ተጋጣሚያቸውን አውቀዋል

የኢትዮጵያ ከ20 እና 17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖች የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ተጋጣሚዎቻቸውን በዛሬው ዕለት አውቀዋል።

ዛሬ ከሰዓት በግብፅ ርዕሰ መዲና የዋናው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ድልድሎችን ያወጣው ካፍ በ2022 በሚደረጉ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ አፍሪካን የሚወክሉ ቡድኖች የሚለዩበት የማጣሪያ ጨዋታ ድልድሎችን አውጥቷል። ባሳለፍነው ዓመት በተደረጉ የማጣሪያ ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የብሩንዲ አቻውን በድምር ውጤት 7-1 አሸንፎ የነበረ ሲሆን ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ ደግሞ በዩጋንዳ አቻው በድምሩ 5-1 ተሸንፎ እንደነበር ይታወሳል። ይሁን እና የውድድሩ የበላይ ካፍ በኮቪድ-19 ምክንያት የተደረጉት የማጣሪያ ጨዋታዎች ሙሉ ለሙሉ እንዲሰረዙ ወስኗል።

ይህንን ውሳኔ ተከትሎም ካፍ ከደቂቃዎች በፊት በኮስታሪካ (ከ20 ዓመት በታች) እና ህንድ (ከ17 ዓመት በታች) የሚደረጉት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ የሚሳተፉ የአህጉሪቱ ቡድኖች የሚለዩበትን የማጣሪያ ድልድል እንደ አዲስ አውጥቷል። በወጣው ድልድል መሠረትም በአሠልጣኝ ፍሬው ወልደገብርኤል የሚመራው ከ20 ዓመት በታች ቡድን ከደቡብ ሱዳን እና ሩዋንዳ አሸናፊ ጋር የሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታውን ያከናውናል። በቅርቡ አሠልጣኝ እንደሚያገኝ የሚጠበቀው ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ደግሞ በድጋሜ ከዩጋንዳ አቻው ጋር የመጀመሪያ ዙር የማጣሪያ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።

© ሶከር ኢትዮጵያ