“ይህ ዕድል ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለብዙ የሀዲያ ወጣቶች ትልቅ ተስፋ ነው” ደስታ ዋሚሾ

ትልቅ ተጫዋች ለመሆን ከልጅነቱ ጀምሮ ያደረበት የእግርኳስ ፍቅር በፕሮጀክት ጀምሮ ዛሬ የሀድያ ሆሳዕና ዋናው ቡድን እስከመጫወት አድርሶታል። ተስፈኛው አጥቂ ደስታ ዋሚሾ ተወልዶ ያደገው በሀድያ ከተማ ልዩ ስሟ ጊቤ ወረዳ በምትባል ሠፈር ነው። በእግርኳስ ፍቅር የተለከፈው ደስታ በአሰልጣኝ አብነት ስር በሠፈር በፕሮጀክት ታቅፎ እግርኳስን በእውቀት መሠልጠን ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ በ2011 በሀድያ ተስፋ ቡድን በመግባት እየሰራ ቢቆይም አቅማቸውን የሚያሳዩበት ውድድር በማጣታቸው እድገታቸውን ጠብቀው እንዳያድጉ ፈተና ሆኖባቸው ቆይታል። ሆሳዕና ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከ20 ዓመት በታች ውድድር ተሳታፊ በመሆኑ እንደ ደስታ ዋሞሻ አይነት አቅም ያላቸውን ተስፈኛ ተጫዋቾችን መመልከት ችለናል።
ደስታ ከ20 ዓመት ውድድር ሰባት ጎል በማስቆጠር ከፍተኛ ጎል አግቢነትን ከመፎካከሩም በላይ ወደፊት ተስፋ የሚጣልበት አጥቂ መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት ሶከር ኢትዮጵያ በዘገባዋ ስትጠቁም ቆይታለች። ክለቡ በአሁኑ ሰዓት ካለበት ወቅታዊ ችግር የተነሳ በአስራ አምስቱ ተጫዋቾች ምትክ አስር ተጫዋቾችን ወደ ዋናው ቡድን ሲያሳድግ ደስታ አንዱ ተጫዋች በመሆን ዛሬ ሰበታ ከተማን ሲገጥሙ ለመጀመርያ ጊዜ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ መካተት ችሏል። በአስገራሚ ሁኔታ ያገኘውን ዕድል በእንቅስቃሴም ጎልም በማስቆጠር መጠቀም የቻለው ደስታ ዋሚሾ ስለመጀመርያ ጎሉ፣ ስለመጣበት መንገድ እና ስላለው ራዕይ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጓል።

” ከቤተሰቤም ሆነ በአካባቢዬ እግርኳስን ተጫውቶ ያለፈ ሰው የለም። ግን ከልጅነቴ ጀምሮ የእግርኳስ በፍቅር በጣም እወድ ነበር። የመጫወት ከፍተኛ ፍላጎትም ነበረኝ። እንደ እርሱ ብሆን እያልኩ በዛብህ መለዮን አርዓያዬ እያደረጉ አድጌያለሁ።

“ዘንድሮ ተስፋ ቡድን መሳተፋችን ብዙ ልምድ እንድናገኝ ጠቅሞናል። በፊት ከልምምድ ውጭ ብዙ ጨዋታዎች አግኝተን አናቅም ነበር። ዘንድሮ ግን ወጥቶ ዘጠና ደቂቃ የመጫወት ልምድ አግኝተን አቅማችንን እና ክፍተቶቻችን አይተን ተመልሰናል።

” በፍጥነት ዋናው ቡድን እናድጋለን ብለን አላሰብንም ነበር። ፈጣሪ ረድቶን ይህን ትልቅ ዕድል በማግኘታችን እኔን ጨምሮ ከእኔ ጋር የመጡት በሙሉ በጣም ደስ ብሏቸዋል። ይህ ዕድል በቀላሉ የማይገኝ መሆኑን እናውቃለን። አጋጣሚ ሆኖ ይህን ዕድል ማግኘታችን ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለብዙ የሀድያ ወጣት ተጫዋቾች ትልቅ ተስፋ እና መልዕክት ነው።

” የመጀመርያ ተሰላፊ ስሆን አንድ ነገር አደርጋለሁ ብዬ አስቤ ነበር። በዛ ላይ እየደገፉኝ እየመከሩኝ የነበሩ ልጆች አሉ። ግብጠባቂው ስንታየሁ በጣም ይመክረኝ ያበረታታኝ ነበር። እንዳውም ጎል አግብተህ ወደ እኔ ትመጣለህ ብሎኝ ነበር። እንደ አጥቂነቴ ጎል አስቆጥራለው ብዬ አስቤ ነበር። ይህም ተሳክቶ ጎል በማስቆጠሬ በጣም በጣም ደስ ብሎኛል።

“ቡድናችን ያለበት ሁኔታ ይታወቃል። ይህን ጫና ተቋቁሞ ዘጠና ደቂቃ መጫወት ጎል ማስቆጠር ደስ ይላል። በጣም ከባድ ነው ፈጣሪ ረድቶን ይህን በማድረጋችን ደስተኞች ነን። ለቀጣይ በራስ መተማመናችንን ከፍ ያደርገዋል።

” ጎሉን ሳስቆጥር ጨርሶ አመቻችቶ የሰጠኝ ዳዋ ነበር። እርሱ ጋር በመሄድ ተቃቅፈን ደስታችንን ስንገልፅ ተጋጭተን አፍጫዬ ሊደማ ችሏል። ያው ወድያው ህክምና አግኝቼ ተመልሼ መጫወት ችያለው።

” ያው በመጀመርያ የዋናው ቡድን ጨዋታዬ የመጀመርያ ጎል በማስቆጠሬ በጣም ደስ ብሎኛል። ስሜቱ በጣም ከፍተኛ ነው። ፈጣሪ ይመስገን የበለጠ ከዚህ በኃላ ጠንክሬ እንድሰራ እና ክለቤንም በምችለው አቅም ለመጥቀም አስባለሁ። ከዛም ባለፈ ሀገሬን ለማገልገል ትልቅ ህልም አለኝ።

” ዛሬ ያስቆጠርኩት ጎል በተስፋ ቡድን እኛን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል እያሰለጠነ እየመከረ እዚህ ላደረሰን የተሰፋ ቡድናችን አሰልጣኝ አላምረው ካሣ አበረክታለሁ።

© ሶከር ኢትዮጵያ