“ከፊታቸው ያለውን ጨዋታ መወጣት እና መፍጨርጨር የእነሱ ፋንታ ነው” ሥዩም ከበደ

የፋሲል ከነማው አሠልጣኝ ሥዩም ከበደ ከቀናት በፊት የወልቂጤ እግርኳስ ክለብ ቡድናቸውን “ከአቅም በታች ተጫውቷል” በሚል ስለከሰሰበት ጉዳይ ሀሳብ ሰጥተዋል።

የ2013 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊው ክለብ ፋሲል ከነማ በቀጣይ ስለሚያከናውናቸው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብሮች ጋር በተያያዘ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። ከደቂቃዎች በፊት በተጠናቀቀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተነሱ ሙሉ ሀሳቦችን ከቆይታ በኋላ ይዘን የምንቀርብ ሲሆን በመግለጫው ላይ ግን ከሰሞኑ የወልቂጤ ከተማን ክስ አስመልክቶ የተሰጠውን ሀሳብ እንደሚከተለው አስፍረነዋል። በጉዳዩ ዙርያ ክለቡ ያለውን አቋም አስመልክቶ ከብዙሃን መገናኛ አባላት ለተነሳው ጥያቄ አሠልጣኝ ሥዩም ከበደ ቁጣ በተሞላው ስሜት ሀሳብ ሰጥተዋል።

“ፋሲል ከአቅም በታች ነው የተጫዋተው ብሎ ወልቂጤ ከሶናል። ይሄ እጅግ ያሳዝናል። እጅግም ያሳፍራል። በመጀመሪያ ደረጃ የእኛ ቡድን ለ19 ጨዋታዎች ሳይሸነፍ የመጣ ነው። በተዘዋዋሪ ደግሞ እነሱ ጠንካራነታችንን መስክረውልናል። ይሄም ደግሞ ትልቅ ነገር ነው። ራሱ ወልቂጤን ብትወስዱት ተከታታይ ስምንት ጨዋታ ሳያሸንፍ የመጣ ቡድን ነው። እኛ እንዴት የእነሱን ዕድል እንወስናለን። እኛ ዘንድሮ የተሻለ ሪከርድ ለመያዝ አላማ ነበረን። በቀሩት ሦስት ጨዋታዎችም ለማሸነፍ ዓላማ ነበረን። እኛ እኮ የተስፋ ቡድን ተጫዋቾች አሉን። ዋንጫ ማግኘታችንን ካረጋገጥን በኋላ እነሱን በመጠቀም መግባት እንችል ነበር። ድሬዳዋን ስንገጥም ግን 95 በመቶ ዋና ቡድኑን ነው ይዘን የገባነው። በቀሪዎቹም ጨዋታዎች እንደዚህ ነው የምናደርገው። ወጣቶቹን የምንፈትሽበት ጊዜም ሆነ እድል እናገኛለን። 

“ፋሲል ጀግና ክለብ ነው። 2011 ጀምሮ በጥሩ መንገድ የተቀረፀን፣ ያደገን እና አሳምኖ ጨዋታዎችን አሸንፎ ሻምፒዮን የሆነ ክለብ ነው። ወልቂጤዎች የራሳቸውን የውስጥ ችግር ማየት ይገባቸው ነበር። ሌላው ቀርቶ መላቀቅ በሚኖርባቸው ጨዋታዎች ላይ እኮ የስልክ ልውውጦች እና መሰል ነገሮች በደንብ ተጣርተው እና ጊዜ ተሰጥቶት ተመርምሮ ነው የሚወራው። ገና በተጫወትን ምሽት ላይ እኮ መግለጫ አይሰጥም። ከፊታቸው ያለውን ጨዋታ መወጣት እና መፍጨርጨር የእነሱ ፋንታ ነው። ድሬዳዋ ከተማ ከእነሱ የተሻለ ነው። እኛን ከመግጠሙ በፊት ያለፉትን አምስት ጨዋታ አልተሸነፈም። ሁለት አሸንፎ ሦስት አቻ ወጥቷል።  ይሄ ደግሞ ከእነሱ እንደሚሻሉ ያሳያል። 

“እኛ ስለወልቂጤም ሆነ ስለድሬዳዋ እንዲሁም ስለማንም አይመለከተንም። በሪከርድ ውድድሩን ለመጨረስ ነበር እየሰራን የነበረው። ሽንፈቱ ሊቆጨን ይችላል። ነገር ግን ከሻምፒዮናነት ማግስት ላይ እንደዚህ አይነት ነገሮች ያጋጥማሉ። በዓለም ላይም እነ ኢንተር ሚላን፣ ማንቺስተር ሲቲ እና ሊቨርፑል ሻምፒዮን ከሆኑ በኋላ ደስታቸውን አጣጥመው ሲጫወቱ ተሸንፈዋል። ፋሲልም የተለየ ክለብ አደለም። ይሄ የክሱ ነገር ግን እንደ ሀገር አይጠቅመንም። ራሳችንን የምናይበት እና ክለባችንን የምንመለከትበት ነገር ነበር መፈጠር የነበረበት። የራሳቸውን እድሜ ለማራዘም ያደረጉት ነገር እጅግ ትክክል አደለም።”

አሠልጣኝ ሥዩም ከበደ በንግግራቸው ማብቂያ ላይም በቀጣይ ክለቡ የራሱን እርምጃ እና መግለጫ እንደሚያወጣ ተናግረዋል።