ወደ ከፍተኛ ሊግ የሚያድጉ አራት ቡድኖች ተለይተው ታውቀዋል

በአዳማ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የአንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ዳሞት ከተማ፣ ቡራዩ ከተማ፣ እንጅባራ ከተማ እና አምቦ ከተማ ወደ ከፍተኛ ሊግ ማደጋቸውን አረጋግጠዋል።

ከረፋድ ጀምሮ በአዳማ አበበ በቂላ ስቴዲየም ሲካሄድ በዋለው የአንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች በመጀመርያ ያገናኘው አምቦ ከተማ እና የአዲስ ከተማን ነበር። በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አልፎ አልፎ ከቆሙ ኳሶች በሚፈጠሩ የግብ ዕድሎች ከተመለከትነው ውጭ ብዙም ግልፅ የግብ ዕድል ሳንመለከት ቀርተናል። በጨዋታው ከዳኝነት ጋር በተያያዘ በሚፈጠሩ ስህተቶች በተጫዋቾችም ሆነ ከቡድኑ አባላት በሚያስተጋቡ ጩኸቶች ከመስማት በቀር የረባ ነገር ሳንመለከት ወደ ከፍተኛ ሊግ የሚያድገውን ቡድን ለመለየት በተሰጠው መለያ ምት አምቦ ከተማ 4-3 በማሸነፍ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ከፍተኛ ሊጉን መቀላቀል ችሏል።

በዛሬው የአምቦ ከተማ ውጤታማ ጉዞ ውስጥ የስድስት ቁጥር ለባሹ ግዛቸው ኃይሉ ሚና የጎላ ቢሆንም በመለያ ምቱ ወቅት ሁለት ምቶችን በግሩም ሁኔታ በማዳን ትልቅ አስተዋፆኦ የነበረው ግብጠባቂው አረፋት መሐመድ በግሉ ጥሩ ቀን አሳልፏል።

በቀጣይ አምስት ሰዓት በቀጠለው ሁለተኛ ጨዋታ ጉለሌን ከ እንጅባራ አገናኝቶ ቀድሞ ከተካሄደው ጨዋታ ጋር በሁሉም መልኩ ተመሳሳይ ሆኖ በመደበኛ ክፍለ ጊዜ ያለ ጎል መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ መለያ ምት አምርተው እንጅባራዎች 4-2 አሸናፊ ሆነዋል። የጨዋታውን የመጀመርያ አስራ አምስት ደቂቃ ጉለሌዎች እንደወሰዱት ብልጫ እና ሳይጠቀሙበት እንደቀረው ግልፅ የጎል አጋጣሚ ጨዋታውን ተቆጣጥረው ይወጣሉ ቢባልም መጨረሻው የተገላቢጦሽ ነው የሆነው።

እንጅባራዎች በተዘናጉበት አስራ አምስት ደቂቃዎች ጎል አለማስተናገዳቸው እድለኞች ቢያደርጋቸውም የጨዋታው ደቂቃ በገፋ ቁጥር ወደ እንቅስቃሴ ገብተው የተደረጀ አጨዋወት አድርገዋል። ይህም ቢሆን ግልፅ የጎል እድል መፍጠር አልቻሉም። ጉለሌዎች የአጥቂዎቻቸው የሚያገኙትን አጋጣሚ አለመጠቀም ዋጋ አስከፍሏቸው የጨዋታው መደበኛ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተሰጠው መለያ ምት እንጅባራ ከተማ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ በግብጠባቂው ቅዱስ ዳኘው ብቃት ታግዞ 4-2 በማሸነፍ ከፍተኛ ሊጉን ተቀላቅሏል።

በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ያለጎል እንደተጠናቀቁት ሁሉ የስምንት ሰዓቱ የቡራዩ ከተማ እና የሰንዳፋ በኬ ጨዋታም በተመሳሳይ ወደ መለያ ምት ዓምርቶ ቡራዩ ከተማ 5-3 በማሸነፍ ከሁለት ዓመት በኃላ ዳግም ወደ ከፍተኛ ሊጉ መመለሱን አረግጧል። ጥሩ የኳስ ፍሰት ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ ያስመለከተን የሁለቱ ጨዋታ ጥቂት የማይባሉ የጎል ዕድሎችን አስመልክተውናል። በተለይ ሰንዳፋ በኬዎች ከመሀል ሜዳ ከተከላካዮች ጀርባ የተጣለለትን ቅዱስ ተስፋዬ አግኝቶ ወደ ጎልነት ቀየረው ሲባል ቀድሞ በኢትዮጵያ ቡና እና በወላይታ ድቻ ከዋንጫ ጋር የታገዘ ታሪክ መፃፍ የቻለው ወንድወሰን ገረመው በጥሩ ሁኔታ ያዳናት ኳስ ለሰንዳፋዎች የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። 

በቀድሞ የጅማ አባ ቡና እና ፊንጫ ስኳር አሰልጣኝ መኮንን ማሞ የሚመሩት ቡራዩዎችም ሆኑ ሰንዳፋዎች ጥሩ እንቅስቃሴ ቢያሳዩም በጎል ያልታጀበ በመሆኑ ጨዋታው ወደ መለያ ምት አምርቶ ወላይታ ድቻን በ2009 በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የኢትዮጵያ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ እንዲያነሳ መለያ ምቶችን በማዳን አስተዋፅኦ ያበረከተው የአሁኑ የቡራዩ ከተማ ግብጠባቂ ወንደሰን ገረመው ዛሬም በድንቅ ብቃቱ ቡራዩ ከተማ 5-3 አሸንፎ ከሁለት ዓመት በኋላ ዳግም ወደ ከፍተኛ ሊግ መመለስ ችሏል።

የዕለቱ የመጨረሻ የሆነው የዳሞት ከተማ እና የጎፋ ባሬንቼ ጨዋታ ጎሎች የተስተናገዱበት እና ድራማዊ ክስተቶችን ያስመለከተ ሆኖ በዳሞት ከተማ 3-2 አሸነፊነት ተጠናቋል።
በቀድሞ ተጫዋቾች በአሁኖቹ አሰልጣኞች የሚመሩት ሁለቱም ቡድኖች ለወደፊት በትልቅ ደረጃ መጫወት የሚችሉ ወጣት ተጫዋቾችን አስመልክተውናል። በውድድሩ ጅማሮ ሽንፈት በማስተናገድ ቢጀምሩም በኋላ ላይ ተከታታይ ድል በማስመዝገብ ለዛሬው ጨዋታ የደረሱት በአሰልጣኝ መኮንን ገላነህ (ዊሀ) የሚመሩት ጎፋ ባሬንቺዎች በየትኛውም መንገድ ወደ ጎል በመድረስ የመጀርያዎቹ ደቂቃዎች አደጋ ለመፍጠር ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። 

በቀድሞ ድንቅ ተጫዋች ፍቃዱ ተካ (ዶቃ) የሚሰጠጥኑት ዳሞት ከተማዎች ከተወሰደባቸው ብልጫ ቀስበቀስ ጨዋታውን እየተቆጣጠሩ ይፈጥሩት የነበረው አደጋ ተሳክቶ በ40ኛው ደቂቃ ከተከላካዩ እና ከግብጠባቂው መሀል ሾልኮ በመግባት በግንባሩ የመጀመርያውን ጎል ሙሉጌታ ካሣሁን ማስቆጠር ችሏል።

ከዕረፍት መልስ ዳሞቶች ጥንቃቄ መርጠው መከላከል አመዝነው ሲጫወቱ ጎፋዎች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ፍለጋ ጥረት ቢያደርጉም ጨዋታው የተለየ ነገር ሳያስመለክተን 80ኛው ደቂቃ መዝለቅ ችሎ ነበር። ሆኖም በመጨረሻው አስር ደቂቃ ድራማዊ ትዕይንት ሊያስመለክተን ችሏል። በመልሶ ማጥቃት ወደ ጎፋ ባሬንቺ ሜዳ የደረሱት ዳሞቶች በደረጄ ነጋሽ ሁለተኛ ጎል አስቆጥረው ብዙም ሳይቆይ የመጀምርያውን ጎል ለዳሞት ያስቆጠረው ሙሉጌታ ካሣሁን ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል በማስቆጠር ቡድኑን እፎይ ማድግ ችሎ ነበር። ሆኖም ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሦስት ደቂቃ በሚቀርበት ቅፅበት ዳሞችን ከመረጋጋት ወደ ጭንቀት የቀየረች ሁለት ተከታታይ ፈጣን ጎሎች ጎፋ ባሬንቺዎች በኃይሉ ተስፋዬ እና ቴዎድሮስ አበበ አማካኝነት ቢያስቆጥሩም የጨዋታው መጠናቀቅ መሰማቱን ተከትሎ በአሳዛኝ ሁኔታ ለመሸነፍ ተገደዋል። ዳሞት ከተማም ውጤቱን ተከትሎ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግን መቀላቀል ችሏል።

ዛሬ ያሸነፉት አራት ቡድኖች ወደ ከፍተኛ ሊጉ ማደጋቸውን ተከትሎ በቀጣይ ሁለት ሌሎች አዳጊ ቡድኖችን ለመለየት በዛሬዎቹ ተሸናፊዎች መካከል የመለያ ጨዋታዎች ቅዳሜ ይደረጋሉ። አዲስ ከተማ ከሰንዳፋ በኬ እንዲሁም ጉለሌ ከጎፋ ባሬንቼ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች አሸናፊዎቹ ቡድኖች ከፍተኛ ሊጉን የሚቀላቀሉ ይሆናል።