ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ24ኛ ሳምንት ምርጥ 11


በሃያ አራተኛ ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ በመመርኮዝ የሳምንቱን ምርጦች በዚህ መልኩ አሰናድተናል።

አሰላለፍ: 3-4-3

ግብ ጠባቂ

ሴኩምባ ካማራ (አዳማ ከተማ)

ምንም እንኳን ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት አዳማ ከተማ በሰበታ ከተማ ቢረታም ጊኒያዊው የግብ ዘብ ሴኩምባ ካማራ ያሳየው ብቃት መልካም ነበር። በተለይ ተጫዋቹ ቅልጥፍና፣ ጊዜ አጠባበቅ እና ጨዋታን ማንበብ በሚጠይቁ ቅፅበቶች ላይ የነበረው የአዕምሮ እና የአካል ፍጥነት ጥሩ ነበር። በዚህም ሒደት ወደ ግብ ተቀይረው ቡድኑ የተሸነፈበትን የግብ ልዩነት ሊያሰፉ የሚችሉ ኳሶችን ሲመልስ ታይቷል። ከዚህም መነሻነት ካማራ የሳምንቱ ምርጥ ቡድናችን የግብ ጠባቂን ቦታ ይዟል።

ተከላካዮች

በረከት ሳሙኤል (ድሬዳዋ ከተማ)

የመሐል ተከላካዩ በረከት ሳሙኤል እንዳለፉት ሳምንታት ሁሉ በዚህም የጨዋታ ሳምንት ጥሩ ብቃቱ ላይ ነበር። ከምንም በላይ ተጫዋቹ በሊጉ ከሚገኙ ምርጥ የአጥቂ መስመር ተጫዋቾች ጋር ለመፋለም የነበረው ድፍረት፣ ኳስ የመመለስ እና የማምከን ችሎታ እንዲሁም አጠቃላይ የመሪነት ብቃቱ ድንቅ ነበር። ዋና ሦራው ከሆነው የመከላከል አጨዋወት ባለፈም በቆሙ ኳሶች ቡድኑ የግብ ማስቆጠሪያ አማራጭ እንዲያገኝ ሲጥርበት የነበረው መንገድ አድናቆት የሚያስችረው ነበር።

ፀጋሰው ድማሙ (ሀዲያ ሆሳዕና)

በዚህ የጨዋታ ሳምንት ከታዩ ምርጥ ተጫዋቾች መካከል ግንባር ቀደሙ ፀጋሰው ድማሙ ነው። ይህ የመሐል ተከላካይ በጊዮርጊሱ ጨዋታ ቡድኑ ግብ እንዳያስተናግድ የነበረው የጨዋታ ፍላጎት ልዩ ነበር። በዚህም የአየር ላይ ኳሶችን ሲመክት፣ የተሳኩ ሸርተቴዎችን ሲወርድ እንዲሁም በአጠቃላይ የአንድ ለአንድ ግንኙነቶችን በተሳካ ሁኔታ ሲያሸንፍ ውሏል። ይሄንንም ተከትሎ በሦስት ተከላካዮች ያዋቀርነው የሳምንቱ ምርጥ ቡድናችንን የኋላ መስመር ከመሐል ሆኖ እንዲመራ አድርገነዋል።

ሄኖክ አርፊጮ (ሀዲያ ሆሳዕና)

ሌላ ድንቅ የጨዋታ ሳምንት ያሳለፈው ተጫዋች ሄኖክ አርፊጮ ነው። ሄኖክ ቡድኑን አሸናፊ ያደረገ የፍፁም ቅጣት ምት በጥሩ አፈፃፀም ወደ ጎል ከመቀየሩ በተጨማሪ እንደ አምበልነቱ ቡድኑን ሲመራ የነበረበት መንገድ እጅግ መልካም ነበር። በጨዋታውም ቡድኑ አብዛኛውን ክፍለ ጊዜ በመከላከሉ ላይ ተጠምዶ በማሳለፉ ሄኖክ ከማጥቃት ይልቅ ወደ ኋላ በማዘንበል እንደ ሦስተኛ የመሐል ተከላካይ የጊዮርጊስን የመስመር ጥቃት ሲመክት ነበር። እኛም ወደ ግራ ያዘነበለ ሦስተኛ የመሐል ተከላካይ ያደረግነውም በጨዋታው በነበረው በዚህ የመከላከል ብቃት መነሻነት ነው።

አማካዮች

ዱላ ሙላቱ (ሀዲያ ሆሳዕና)

በቀኝ መስመር በኩል ተሰልፎ የተጫወተው ፈጣኑ ዱላ ሙላቱ ለጊዮርጊሶች የሚቀመስ አልነበረም። በዋናነትም ተጫዋቹ ወደ መከላከሉ አዘንብሎ ክፍተቶችን ለመዝጋት ከመጣሩ በተጨማሪ ስል የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎችን በተሰለፈበት መስመር በማሳለጥ ተጋጣሚን ሲያስጨንቅ ነበር። ወደ ግብ ለተቀየረው የፍፁም ቅጣት ምትም መገኘት እሱ ያሻገረው ኳስ አስፈላጊ ነበር። በአጠቃላይ ተጫዋቹ የተሰለፈበትን መስመር የተቆጣጠረበት ብቃት ምርጥ ቡድናችን ውስጥ እንዲገባ አስችሎታል።

ሱራፌል ጌታቸው (ድሬዳዋ ከተማ)

ከኳስ ጋር ጥሩ ምቾት የሚሰማው የድሬዳዋ ከተማው የአማካይ መስመር ተጫዋች ሱራፌል ቡድኑ እጅግ ወሳኝ ድል ፋሲል ሲቀዳጅ የነበረው የሜዳ ላይ ተሳትፎ ትልቅ ነበር። በጨዋታው ሜዳውን በማካለል ጥሩ የነበረው ሱራፌል በተለይ የአማካይ መስመሩን ከአጥቂ መስመሩ ጋር በማገናኘት ረገድ የተዋጣለት ስራን ከውኗል። በመስመሮች መካከል (በአማካይ እና ተከላካይ መሐከል) እየገባም ለአጥቂ ተጫዋቾች ኳሶችን ሲመግብ ተይቷል። ከዚህ በተጨማሪ ራሱ ግብ የሚሆኑ ኳሶችን ሲሞክር የተስተዋለ ሲሆን ለአንድ ጎል መቆጠር የፋሲልን ኳስ የማስጀመር እንቅስቃሴን አቋርጦ ማመቻቸትም ችሏል።

ሚካኤል ጆርጅ (ሀዲያ ሆሳዕና)

እንደባለፈው ሳምንት ሁሉ በአማካይ ስፍራ የተጫወተው ሚካኤል ለተከላካዮች ሽፋን በመስጠት እና የቅዱስ ጊዮርጊስን ጥቃት በማቋረጥ ረገድ (አንዳንዴ ኃይል ቢጠቀምም) ጥሩ ቀን አሳልፏል። ቡድኑ በመልሶ ማጥቃት የፈጠራቸው እድሎች ላይ የተሳፈው ሚካኤል አንድ ኳስ ከርቀት ሞክሮ ግብ ጠባቂ ባያድንበት በተከታታይ ጨዋታ ጎል አስቆጥሮ ለመውጣትም ተቃርቦ ነበር።

መሐሪ መና (ሲዳማ ቡና)

ሲዳማ ቡናን ከተቀላቀለ ወዲህ በጥሩ አቋም ቡድኑን እያገለገለ የሚገኘው መሐሪ መና ከኢትዮጵያ ቡና አቻ በተለያዩበት ጨዋታ በግራ መስመር በተለይ በማጥቃት እንቅስቃሴ ጥሩ ቀን አሳልፏል። ቡድኑ አንድ አቻ የሆነበት ጎል አስቆጥሮ የነበረው ተከላካዩ በተሻጋሪ ኳሶች እና የማጥቃት ሩጫዎች አደጋ ለመፍጠር ጥሯል። ከዚህ ውጪም ዋናውን የመከላከል ሥራም በጥሩ ታታሪነት ሲከውን ታይቷል።

አጥቂዎች

ኦኪኪ አፎላቢ (ሲዳማ ቡና)

ፈርጣማው የአጥቂ መስመር ተጫዋች ኦኪኪ አፎላቢ ቡድኑ አጥብቆ በሚፈልገው ወቅት ሳያረፍድ እየተገኘ ይገኛል። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንትም ቡድኑ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ ሲጋራ የእርሱ መኖር ወሳኝ ነበር። በዋናነት ደግሞ ተጫዋቹ የኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮችን ኳስ የማስጀመር ሒደት ለማምከን ሲጥር ከመዋሉ ባሻገር የጎል ዕድሎች ሲፈጠሩ የነበሩት በሱ መነሻነት ነበር። ከተቆጠሩት ሦስት ጎሎች ሁለቱን ለማማዱ እና ይገዙ ያቀበለውም እርሱ ነው።

አቡበከር ናስር (ኢትዮጵያ ቡና)

ስለእርሱ ለመፃፍ እስኪያቅት ድረስ ድንቅ ብቃቱን በሊጉ እያሳየ የሚገኘው አቡበከር በዚህኛው የጨዋታ ሳምንትም መነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ አልፏል። ተጫዋቹ በአንድ የውድድር ዘመን የተቆጠሩ የጎሎችን ሪከርድ በ27 ግቦች በያዘበት የሲዳማ ቡናው ጨዋታም ሐት ትሪክ ሲስራ ያሳየው ብቃት ድንቅ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ የመጫወቻ ቦታ እና ጊዜ እንደልብ በማይገኝበት የተጋጣሚ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ያለው ቅልጥፍና፣ ፍጥነት (አዕምሮም ሆነ አካል)፣ እና አይምሬነት ተጫዋቹን ውጤታማ እያደረገው ነው። ይህንንም ተከትሎ የምርጥ ቡድናችን አጋፋሪ አድርገነዋል።

ኢታሙና ኬሙይኔ (ድሬዳዋ ከተማ)

ከ18 ጨዋታዎች በኋላ የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ግብ ያስቆጠረው ናሚቢያዊው አጥቂ በዚህ የጨዋታ ሳምንት ዋና ስራውን በአግባቡ ሲከውን ታይቷል። ለወትሮው በጨዋታ ላይ ያለው ተሳትፎ እጅግ ወርዶ የነበረው ኬሙይኔ በፋሲሉ ጨዋታ ግብ ከማስቆጠሩ በተጨማሪ በተሰለፈበት መስመር የአደጋ መነሻ ሆኖ ነበር። በተለይ ደግሞ ከመስመር እየተነሳ ወደ መሐል በመግባት የፋሲል ከነማ ተጫዋቾች ላይ ጫና ሲያሳድርበት የነበረው መንገድ ለቡድኑ ፍሬ ያፈራ ነበር። በተጨማሪም ግቡን ሲያስቆጥር ራሱን ነፃ ያደረገበት እና ኳሱን የጨረሰበት ሒደት ጥሩ የአጥቂ ደመነፍስ እንዳለው የመሰከረ ነው።

አሰልጣኝ – ኢያሱ መርሐፅድቅ (ዶ/ር)

በውጥንቅጥ ውስጥ ይገኝ የነበረውን ቡድን በድንገት በዋና አሰልጣኝነት የተረከቡት ዶ/ር ኢያሱ ቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾቹን አጥቶ እንኳ ምንም የጎደለበት እንዳይመስል እያደረጉት ይገኛሉ። በዚህ ሳምንት በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ ፉክክሩ ቀጥተኛ ተፋላሚያቸው የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስን 1-0 ሲረታ የአሰልጣኙ የመከላከል አቀራረብ ስኬታማ ሆኖ ውሏል። ጊዮርጊሶች እንደልብ እንዳያጠቁ ብሎም የጎል ዕድል እንዳይፈጥሩ የገደቡት አሰልጣኙ ከምንም በላይ ግብ ጠባቂውን ጨምሮ አምስት ወጣቶችን ያቀፈው የመጀመርያ አሰላለፍ በሙሉ ትኩረት፣ ተነሳሽነት እና በራስ መተማመን እንዲጫወት ማድረጋቸው አድናቆት የሚያስቸረው ነው። በዚህ ሳምንት የፋሲል ከነማን 19 ተከታታይ ጨዋታ ያለሽንፈት ጉዞ የገቱት የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ለሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኝነት ዋነማ ተጠቃሽ ቢሆኑም ሀዲያ ሆሳዕና ካለበት ወቅታዊ ሁኔታ፣ የተጫዋች ስብስብ እና የጨዋታው ጥንካሬ አንፃር አሰልጣኝ ኢያሱ መርሐፅድቅን በሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኝነት አካተናል።

ተጠባባቂዎች

አቡበከር ኑሪ (ጅማ አባ ጅፋር)
አማኑኤል እንዳለ (ሲዳማ ቡና)
በረከት ወልደዮሐንስ (ሀዲያ ሆሳዕና)
ክብረአብ ያሬድ (ሀዲያ ሆሳዕና)
ዊልያም ሰለሞን (ኢትዮጵያ ቡና)
ኦሴ ማዉሊ (ሰበታ ከተማ)
ሪችሞንድ አዶንጎ (ድሬዳዋ ከተማ)