ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ነገ ከሰዓት በሚደረገው ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ሀሳቦች አንስተናል።

አዳማ ከተማ ቀድሞ መውረዱን ቢያረጋግጥም ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለተኛ ደረጃ ፉክክር ውስጥ መገኘቱ ጨዋታው ተጠባቂ እንዲሆን ያደርገዋል። የዛሬውን የሰበታን ውጤት ተከትሎ ደረጃው ወደ አምስተኛነት የወረደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነገ ድል ካደረገ ነጥቡን ከከተማ ተቀናቃኙ ጋር ማስተካከል እና ለኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ ባለው ፉክክር ውስጥ እስከ ቀጣዩ የሊጉ የመጨረሻ ሳምንት ድረስ ራሱን ማቆየት ይችላል። ሌሎቹ የቦታው ፈላጊዎች ኢትዮጵያ ቡና እና ሀዲያ ሆሳዕና እርስ በእርስ መገናኘታቸውም የነገው ጨዋታ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ያለውን አስፈላጊነት ይጨምረዋል። አዳማ ከተማም ቢሆን ተጨማሪ ነጥቦችን ማግኘት ቢያንስ አንድ ደረጃ እንዲያሻሽል ስለሚረዳው ጨዋታውን በቀላይ ይመለከተዋል ተብሎ አይጠበቅም።

የቅዱስ ጊዮርጊስ የዚህ የውድድር ዓመት ጉዞ ደካማ ቢሆንም የሰሞኑ አቋሙ ደግሞ የባሰ ሆኗል። ድሬዳዋን በሽንፈት የተሰናበተው በድኑ በሀዋሳው ውድድር ከጥሩ አቋም ጋር ድል አድርጎ ቢጀምርም ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች አግኝተውታል። እርግጥ ነው በሁለተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ የሚፎካከሩ ሌሎች ክለቦች ሁሉ በየተራ ነጥብ እየጣሉ ዕድላቸውን እያሳለፉ ቢሆንም ቢያንስ ሜዳ ላይ ባላቸው እንቅስቃሴ መጠነኛ መነሳሳት እና ፍላጎትን ያሳያሉ። ይህ ባህሪ በጊዮርጊስ እየታየ አለመሆኑ ግን አስገራሚ ነው። በየዓመቱ ለቻምፒዮንነት እና ለአፍሪካ መድረክ ውድድሮች ትልቅ ትኩረት የነበረው ክለቡ በዘንድሮው ውድድር ቢያንስ አህጉራዊ ውድድር ላይ ለመካፈል ያለውን ዕድል ጨርሶም የዘነጋው ይመስላል። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አሸንፎ ከሜዳ ለመውጣት የታየበት የቡድን መንፈስ የተዳከመ መሆንም ለዚህ ዋነኛ ምስክር ነው። ይህ ነገር በነገው ጨዋታም ተሻሽሎ ካልቀረበ ምንም እንኳን ተጋጣሚው ደካማ ቢሆንም ለሦስተኛ ሽንፈት እንደማይዳርገው እርግጠኛ መሄን አይቻልም።

በሊጉ እንደማይቀጥል የታወቀው አዳማ ከተማ እንደቡድን መሻሻለን እያሳየ እዚህ ደርሷል። ያለጫና በነፃነት ባደረጋቸው ጨዋታዎችም እንቅስቃሴው ከቀደመው ጊዜ ጋር ሲነፃፀር ጥሩ ነው ሊባል የሚችል ነው። ከዚህም መነሻነት ነገ ደፍሮ በማጥቃት ላይ የተመሰረተ አጨዋወትን የሚመርጥ ቡድን ይዞ እንደሚቀርብ መገመት ይቻላል። ይህ ነጥብ በመጨረሻ ጨዋታው በጥልቅ የሚከላከል ቡድን ገጥሞት ለነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሻለ የመጫወቻ ቦታ ሊሰጠው እንደሚችል የሚያሳይ ነው። ነገር ግን ከመስመር ለሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች አብዝቶ ትኩረት ሲሰጥ የሚታየው የፈረሰኞቹ የማጥቃት አማራጭ ደካማ ለሆነው የአዳማ የኋላ ክፍል ምን ያህል ፈተና ሊሆን ይችላል የሚለውን ጉዳይ ከጨዋታው የምንጠብቀው ይሆናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ጊዮርጊስ እና አዳማ እስካሁን በሊጉ 37 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 19 በማሸነፍ የበላይ ሲሆን አዳማ 7 ጨዋታ አሸንፏል። 11 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

– በግንኙነቶቹ ጊዮርጊስ 49 ፤ አዳማ ከተማ 26 አስቆጥረዋል።