የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 0-1 ሰበታ ከተማ

በ25ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ ሰበታ ከተማ ቶማስ ስምረቱ በራሱ መረብ ላይ ባስቆጠራት ግብ በማሸነፍ ደረጃን ካሻሻለበት ድል በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

አብርሃም መብራቱ – ሰበታ ከተማ

ስለጨዋታው

“የዛሬው ጨዋታ በጠበቅነው መልክ ሄዶልናል። ማግኘት የሚገባንን ነጥብ አግኝተን ደረጃችንን አሻሽለናል። ከነበረን የጨዋታ ብልጫ አንፃር ያገኘነው ግብ በራሳቸው የተቆጠረ ቢሆንም ብዙ የሳትናቸው ኳሶች መኖራቸውን ተመልክተናል።”

ከተጋጣሚያቸው ወቅታ ሁኔታን ሳይመለከት ቡድን ስለመጫወቱ

“በትክክል ወልቂጤ ላለመውረድ ነው የሚጫወተው። ግን ለእኛ 12ቱም የሊጉ ቡድኖች እኩል ናቸው። የእግርኳስ ሙያው የሚፈቅደው አቅምህ የፈቀደውን በሙሉ ሜዳ ላይ አድርገህ የተገኘውን ውጤት በፀጋ መቀበል ነው። ዛሬ በነበረን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ተሸንፈን ከሜዳ ብንወጣ እንኳን ወልቂጤን እንኳን ደስ አላችሁ ብዬ ተጫዋቾቼን አመሰግን ነበር። እንደትምህርት ሊወሰድ የሚገባው ነገር ለሁሉም ቡድኖች እኩል ግምት ሰጥቶ ለማሸነፍ መንቀሳቀስ ከሁሉም ክለቦች ይጠበቃል ብዬ አስባለሁ።”

ቀጣይ እቅዳቸው እስከ አምሰተኛ ባለው ደረጃ ማጠናቀቅ ወይንስ ለሁለተኝነት መፎካከር ?

“አላማችን ምርጥ አምስት ውስጥ ሆኖ ለማጠናቀቅ ነው። ነገርግን ቡድኖች ነጥብ እየጣሉ ከሄዱ እና እኛ የምናሸንፍ ከሆነ ለሁለተኛ ደረጃ እንናፍቃለን። ይህን ለማሳካት ጥረት እናደርጋለን።”

ሲሳይ አብርሃ – ወልቂጤ ከተማ

ስለ ጨዋታው 

“ጨዋታው ጥሩ ነበር፤ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ተጭነን ለመውጣት ሞክረናል። በመጀመሪያው አጋማሽ ሃያ አምስቷን ደቂቃ የተሻለ ለመንቀሳቀስ ሞክረናል። ብዙ የግብ አጋጣሚዎችን ፈጥረን መጠቀም አልቻልንም። ይህ እግርኳስ ነው፤ ምናልባት ልጆቹ ጫና ላይ ስለሆኑ ሊከሰት ይችላል። ከጨዋታው በፊት በነበረን ልምምድም ሆነ በክፍል ውስጥ በነበረን ቆይታ ተጫዋቾቻችን የተሻለ መነሳሳት እና ፍላጎት ነበራቸው። ነገርግን ሜዳ ላይ አጋጣሚ ሆኖ ግብ ተቆጥሮብናል። ይህን ምንም ማድረግ አንችልም፤ በእግርኳስ የሚኖር ነገር ስለሆነ። ተጫዋቾቼ የሚችሉትን አድርገዋል። ለፍተዋል፤ ነገርግን ፈጣሪ ስላልፈቀደው አልተሳካም።

ስላመውረድ ተስፋቸው

“አዎ እኛ እስከመጨረሻው ተስፋ አለን። የሁሉንም ጨዋታ አይተን ወርዳችኋል እስክንባል ድረስ ተስፋ እናደርጋለን።”