የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 0-2 ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማ ከተማን 2-0 ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

ፍራንክ ናታል – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ጨዋታው እንዴት ነበር?

“በማሸነፋችን ፍፁም ደስተኛ ነን። ለባለፈው ጨዋታ ጥሩ ምላሽ ሰጥተናል።”

ግብ ሳያስተናግዱ ስለመውጣታቸው

“ሁሌም ቢሆን ተጫዋቾቼ ግብ እንዳያስተናግዱ አጠይቃለሁ። በዛሬ ጨዋታ ተጫዋቾቼ የትኩረት ደረጃ እና ቁርጠኝነታቸው በጣም የተለየ ነበር። ያላቸውን በሙሉ በመስጠታቸው ውጤቱ የሚገባን ነበር።”

ስለሁለተኝነት ደረጃ

“ዋነኛ ትኩረታችን በቀጣዮቹ ቀናት ተጫዋቾቻችን ለመጨረሻው ጨዋታ እንዲያገግሙ ማድረግ ነው። በነገው ጨዋታ የሚፈጠረው አይታወቅም። ውጤቱ በተለያየ አቅጣጫ ሊወስደን ይችላል። ስለዚህ አሁንም ቢሆን እድሉ ስላለን በእነዚህ ነገሮች ላይ እናተኩራለን።”


ዘርዓይ ሙሉ – አዳማ ከተማ

በጨዋታው የሚፈልገውን ስለማግኘቱ

“ስንጀምር በሠራናቸው ስህተቶች ተሸንፈን ወጥተናል። በረጃጅሙ በሚጣሉ ኳሶች ሊያጠቁን እንደሚችል ገምተን ሰርተንም ተነጋግረን ነበር የመጣነው። ነገርግን በበረኛችን እና በተከላካዮቻችን የጊዜ አጠባበቅ ችግር ተሸንፈን ወጥተናል። እንደዚያም ቢሆን ግን ኳሱን ተቆጣጥረን ተጫውተናል። በእንቅስቃሴ ደረጃ ከባፈለው የተሻልን ነበርን። እንደአጠቃላይ መጥፎ አልነበርንም።”

ወጣቶችን በመጠቀም ረገድ ቡድን የሚጠበቅበትን ስለማድረጉ

“አዎ ወጣቶች ሲባል መጫወት ያለባቸውና ለመጫወት የደረሱትን ሁለት ሦስት ልጆችን ለማየት ሞክረናል። ጥሩ እንቅስቃሴንም አሳይተውናል። ወደፊት የመጫወቱን ዕድል ሲያገኙ የተሻለ ነገር መሥራት ይችላሉ ብዬ ስላሰብኩ ተጠቅሜያቸዋለሁ። በእንቅስቃሴያቸውም ደስተኛ ነኝ።”

ስለውድድር ዘመኑ ምርጦቹ

“በዘንድሮው የውድድር ዘመን በግብ ብቻ ሳይሆን በእንቅስቃሴ ደረጃ ቡድኑ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ በማስቻል ረገድ አቡበከር ናስር ምርጡ ነው። ሁለተኛ ያሬድ ባዬ እንዲሁም በሦስተኛ ደረጃ ለራሴ ማዳላት ሳይሆን አብዲሳ ጀማል በግሉ ቡድኑን እዚህ ስላደረሰ መርጬዋለሁ።”