ቅድመ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ ጅማ አባ ጅፋር

ሦስተኛውን ወራጅ ቡድን ሊጠቁም የሚችለውን ጨዋታ በዳሰሳችን ተመልክተነዋል።

ይህ ጨዋታ ለጅማ አባ ጅፋር የመርሐ ግብር ማሟያ ቢሆንም ለሲዳማ ቡና ግን እጅግ አስፈላጊ ነው። ቡድኑ ከዚህ ጨዋታ አንድ ነጥብ ብቻ ማግኘት ከቻለ ለከርሞው በሊጉ መቆየቱን ማረጋገጥ ሲችል ወልቂጤ ከተማ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱ ዕውን ይሆናል። በመሆኑም ተጠባቂነቱ ከጅማ ይልቅ ለወልቂጤ ያደላ ነው ማለት ይቻላል።

በዚህ ጨዋታ ለጅማ አባ ጅፋር ተነሳሽነት የሚፈጥር ነጥብ ፈልጎ ማግኘት ቀላል አይሆንም። ለሊጉ ክብር ያበቁትን የቀድሞው አሰልጣኙን እና በተመሳሳይ ጊዜ ወሳኝ አጥቂው የነበረው ኦኪኪ አፎላቢን በያዘው ሲዳማ ቡና እጅ እስካሁን በታሪክ ሽንፈት አለማስተናገዱ ለጅማ አንዱ ተነሳሽነትን የሚፈጥርለት ነጥብ ነው። በሌላ በኩል ዘንድሮ ድል ካደረገባቸው ጥቂት ጨዋታዎች ቀዳሚውን ሦስት ነጥብ ሲዳማ ላይ ማሳካቱ የመጨረሻውንም ድል ከዚሁ ቡድን ለማግኘት ሞራል ሊሆነው ይችላል። እርግጥ ነው የያኔው እና የአሁኑ ሲዳማ ቡና ወቅታዊ አቋም እጅግ የተለየ መሆን ለጅማ ጨዋታውን ሊያከብድበት ይችላል። በሌላ በኩል በመጨረሻዎቹ አራት ተጋጣሚዎቹ ሦስት ነጥብ አለመፍቀዱ እና በሁለቱ ደግሞ መረቡን ሳያስደፍር መውጣቱ ለጅማ አባ ጅፋር ቀላል ግምት እንዳንሰጠው እና ጨዋታው ላይ ጥሩ ፉክክር እንደምንመለከት የሚጠቁም ነው።

ሲዳማ ቡና ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ መምጣቱ በሊጉ ሁለት ጨዋታዎች እጁ ላይ ኖረው አንድ ነጥብ ብቻ እንዲያስፈልገው አድርጎታል። ከሰበታ ነጥብ በመጣል የጀመረውን የሀዋሳ ውድድር ከሁለቱ የአሲስ አበባ ክለቦች አራት ነጥብ በማግኘት ማሳመሩም ተስፋውን በእጁ እንዲያዲርግ አግዞታል። የዓመቱን ከባዱ ጉዞም ከነገው ጨዋታ እንዲያልፍ የሚፈቅድ አይመስልም። የቡድኑ መሻሻል ከመጨረሻው የቡና ጨዋታ ውጪ ከአንድ ግብ በላይ ሳያስተናግድ ተከታታይ ጨዋታዎችን በዘለቀው የኋላ ክፍሉ ጥንካሬ መግለፅ ቢቻልም የፊት መስመሩ ሁኔታ ግን ይበልጥ ትኩሩትን ይስባል። በመጨረሻዎቹ ሁለት ከባድ ጨዋታዎች አምስት ግቦችን ከመረብ ማገናኘቱ ደግሞ ለዚህ ሁነኛ ማስረጃ ነው። ለዚህ ውጤታማነቱ ዋነኛ ተዋናይ ሆነው የሰነበቱት ኦኪኪ አፎላቢ እና ማማዱ ሲዲቤ ተገማች ያልሆነ ጥምረትም ነገ ቡድኑን ወደ ሙሉ ነፃነት ሊያመራው እንደሚችል ይገመታል። በተለይም በእንቅስቃሴ አንዱ ለአንዱ የሚመጋገቡት መንገድ እና አንዱ የፊት አጥቂ ሲሆን ሌላኛው ከጀርባ ሆኖ ከአማካይ በመገናኘት የሚተገብሩት አጨዋወት እየተሻሻለ ከመጣው የጅማ የኋላ ክፍል ጋር የሚያደርጉትን ፍልሚያ እንድንጠብቅ ያደርገናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን አምስት ጊዜ ተገናኝተው ጅማ አባ ጅፋር ሦስቱን በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ሁለቱን ጨዋታዎች ያለ ጎል በአቻ ውጤት አጠናቀዋል። ጅማ 5 ፣ ሲዳማ 1 ጎል አስቆጥረዋል።