ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

ሊጠናቀቅ አንድ የጨዋታ ሳምንት በቀረው የ2013 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 25ኛ የጨዋታ ሳምንት የተጫዋች ትኩረታችንን እነሆ ብለናል።

👉 ሳልሀዲን በርጌቾ ወደ ሜዳ ተመልሷል

ባለፉት ጥቂት የውድድር ዘመናት ከቅዱስ ጊዮርጊስ መደበኛ ተሰላፊ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የነበረው ሳልሀዲን በርጌች የተሰረዘው እና በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የዘንድሮው ውድድር ዘመን በእግርኳስ ህይወቱ ፈታኞቹ ነበሩ ብሎ መናገር ይቻላል።

ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመጣበት ጊዜ አንስቶ ጥሩ ብቃቱን ባሳየበት ቅዱስ ጊዮርጊስ የመሐል ተከላካይ ስፍራ የመሰለፍ እድሉን ለማግኘት ተቸግሮ የነበረው ተጫዋቹ በተሰረዘው የውድድር ዘመን ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋሲል ከነማ ጋር ሁለት አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ጉዳት አስተናግዶ ከሜዳ ከወጣ በኋላ ለአንድ አመት የሚጠጋ ጊዜን ከጨዋታ ርቆ ለማሳለፍ ተገዷል።

ተጫዋቹ ከጉዳቱ አገግሞ የጨዋታ ዕለት ስብስብ አካል መሆን ከጀመረ ቢሰነብትም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ አዳማ ከተማን 2-0 በረታበት ጨዋታ ከአንድ አመት ቆይታ በኃላ ዳግም በቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ ይፋዊ ጨዋታ ሲያደርግ ተመልክተነዋል።

ረጃጅም ኳሶች መገለጫው የሆነው ተጫዋቹ ዳግም ወደ ሜዳ በተመለሰበት የአዳማው ጨዋታ ሳልሀዲን ሰዒድ ላስቆጠራት የመጀመሪያ ግብ መነሻ የሆነች አስደናቂ ረጅም ኳስን በማቀበል ወደ ሜዳ የተመለሰበትን ጨዋታ ልዩ አድርጎታል።

👉 የስንታየሁ መንግሥቱ ያልተገባ ድርጊት

በዘንድሮው የውድድር ዘመን በወላይታ ድቻ
ዳግም ራሱን እያስተዋወቀ የሚገኘው አጥቂው ስንታየሁ መንግሥቱ እስካሁን አስር ግቦችን በማስቆጠር በሊጉ ከፍተኛ አስቆጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ በአራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በከፍተኛ ሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ባጠናቀቀበት የ2011 የውድድር ዘመን በአርባምንጭ ከተማ መለያ ያሳየውን አስደናቂ ብቃት ተከትሎ በተሰረዘው የውድድር ዘመን ወደ በባህር ዳር ከተማ ያመራው አጥቂው በማሊያዊው አጥቂ ማማዱ ሲዴቤ ጥላ ሥር የሚጠበቅበትን ማድረግ ሳይችል መቅረቱ ይታወሳል።

ከጉዳት ነፃ ሆኖ ቡድኑን ባገለገለባቸው ጨዋታዎች በሜዳ ላይ ባሳየው እንቅስቃሴ በመልካሙ ስሙ ይነሳ የነበረው ተጫዋቹ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን ባሳየው ያልተገባ ድርጊት መነሻነት ስሙ ከአላስፈላጊ ጉዳይ ጋር እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል።

ወላይታ ድቻ ባህር ዳር ከተማን በረታበት ጨዋታ በ86ኛው ደቂቃ በቢኒያም ፍቅሬ ተቀይሮ የወጣው ስንታየሁ መንግሥቱ ተቀይሮ ከወጣ በኃላ የተጠባባቂ ተጫዋቾች መቀመጫ ወንበሩን በብስጭት ስሜት ሆኖ በተደጋጋሚ እየደበደበ ሲያሰሳይ የነበረው ያልተገባ ድርጊት ተገቢ ያልሆነ ነበር።

እርግጥ ማንኛውም እግርኳስ ተጫዋች በሜዳ ላይ ዘጠናውንም ደቂቃ መጫወት እንጂ ከሜዳ ተቀይረው መውጣት እንደማይፈልጉ ቢታመንም በአሰልጣኞች ቡድን አባላት ፍላጎት ከሜዳ እንዲወጡ በሚደረግበት ሒደት ደስተኛ ባይሆኑ እንኳ ውሳኔዎቹ ለቡድኑ ጥቅም መወሰናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ውሳኔዎችን በፀጋ መቀበል ይጠበቅባቸዋል።

ይህን ታሳቢ በማድረግ ስንታየሁ መንግሥቱ ያሳየው ተግባር በቀጣይ ሊታረም የሚገባ መሆኑን ልናስገነዝብ እንወዳለን።

👉 አቡበከር ናስር ግብ ማምረቱን ቀጥሏል

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ሲዳማ ቡና ላይ ሐት ትሪክ በመሥራት ለአራት ዓመታት በጌታነህ ከበደ ተይዞ የነበረውን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ ጎል አስቆጣሪነት ክብርን የተረከበው አቡበከር ናስር በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት እንዲሁ ሁለት ተጨማሪ ወሳኝ ግቦችን አስቆጥሮ በአጠቃላይ ያስቆጠራቸውን የግብ ብዛት 29 ማድረስ ችሏል።

በክለቡ የቡድን አባላት ተጫዋቹ ሪከርዱን በመስበሩ የእንኳን ደስ አለህ እና የውዳሴ ቃላት የሰፈሩበት ቲሸርት በመልበስ የተቀበሉበት መንገድ ሊበረታታ የሚገባውና ታሪክ ለሚሰሩ ተጫዋቾች ዕውቅና መስጠትን ባልለመደው እግርኳሳችን ላይ በጎ ተፅዕኖን የሚፈጥር ነው።

በቡድን አባላቱ የተደረገለት አቀባበልን አፀፋ በሁለት ጎሎች የመለሰው አጥቂውን መቆጣጠር ለሊጉ ተከላካዮች እጅግ ፈታኝ እንደሆነ በዚህ ሳምንት ያስመለከተ ሲሆን የኢትዮጵያ ቡና ውጤታማነት ዋነኛው መሳርያ መሆኑን ዳግም አስመስክሯል። ክለቡ በጥቅሉ በሁለተኛ ዙር ካስቆጠራቸው አስራ አራት ግቦች አስራ ሁለቱን ማስቆጠሩም ይህን የሚያመለክት ነው።

አቡበከር ናስር አንድ ቀሪ የሊግ ጨዋታ እንደመቅረቱ ተጨማሪ ግቦችን አስቆጥሮ ክብረ ወሰኑ በቅርቡ በቀላሉ እንዳይሰበር አድርጎ አርቆ ሊሰቅለው ይችል ይሆን የሚለው ተጠባቂ ጉዳይ ነው።

👉 ዕድለ ቢሱ ቶማስ ስምረቱ

በሊጉ ጥሩ አጀማመርን ቢያደርግም በሁለተኛው ዙር በገባበት የውጤት አልባ ጉዞ ከሊጉ ለመሰናበት በተገደደው ወልቂጤ ከተማ ውስጥ በግላቸው ነጥረው መውጣት ከቻሉ የቡድኑ ተጫዋች በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሰው ቶማስ ስምረቱ ለቡድኑ በውድድር አመቱ የቻለውን ሁሉ ሰጥቷል ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ግዙፉ የመሀል ተከላካይ በሁለተኛው ዙር በቅጣት ካመለጡት ጨዋታዎች ውጭ በሜዳ ላይ በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ሁሉ በግሉ ማድረግ የሚችለውን በሙሉ አድርጓል። በጥቅሉ ሲታይ መከላከልም ሆነ ማጥቃት እንደቡድን የሚከወን ቢሆንም እንደ ቶማስ ያሉ ተጫዋቾች ተፅዕኖን ግን በጉልህ መመልከት ይቻላል።

በ25ኛ የጨዋታ ሳምንት ላለመውረድ እየታገሉ የነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች ሰበታን በገጠሙበት ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታው መገባደጃ በተቃረበበት ወቅት እንዳለመታደል ሆኖ የሰበታው ኦሲ ማውሊ ወደ መሀል ያሳለፈውን ኳስ ለማውጣት ባደረገው ጥረት በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሮ ቡድኑ በፕሪምየር ሊጉ የመቆየት ዕድሉን ያሟጠጠች ግብን አስቆጥሯል። ይህች አጋጣሚ ለተጫዋቹ ሆነ ለክለቡ ደጋፊዎች መሪር ሀዘንን የፈጠረች ከመሆኗ በላይ ዓመቱን ሙሉ በግሉ በጥሩ ብቃት ቡድኑን ባገለገለው ተጫዋች የተቆጠረች መሆና ይበልጥ ልብ ሰባሪ ያደርገዋል።

👉 ዳግም እያንፀባረቀ የሚገኘው ቸርነት ጉግሳ

በሀገራችን እግርኳስ በተለይ ባለፉት ጥቂት አመታት ከታችኞቹ የእድሜ እርከን ቡድኖች ወደ ዋናው ቡድን የሚያድጉ ተጫዋቾች መጀመሪያ የመሰለፍ እድልን ባገኙባቸው ጥቂት ወራት ያለ የሌለ አቅማቸውን አሳይተው አስደማሚ አጀማመር ቢያደርጉም በቀጣይ ባሉ የውድድር ዘመኖች ግን እድገታቸው ሲገታ ብሎም ስለማንነታቸው እስክንጠራጠር ድረስ ፍፁም ተዳክመው መመልከት አየተለመደ መጥቷል።

ቸርነት ጉግሳም ለረጅም ጊዜያት የዚህ ሂደት ሰለባ የሆነ ይመስል ነበር። ነገርግን በዘንድሮው የውድድር ዘመን ግን በተለይ ወላይታ ድቻዎች የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረጉ ወዲህ ተጫዋቹ የእግርኳስ ዘመኑ ምርጡ ብቃቱ እያሳየ ይገኛል። ራሱን መልሶ ያገኘው ተጫዋቹ በቀጣይም ይህን አስደናቂ ብቃቱን ጠብቆ እራሱን ወደ ከፍታ ማሸጋገር ቀጣይ ትልቁ የቤት ሥራው ነው።

👉 የአምሳሉ ጥላሁን ተገቢ ያልሆነ ድርጊት

ፋሲል ከነማ ዋንጫ ባነሳበት የሀዋሳ ከተማው ጨዋታ ባጋጠመው ጉዳት መነሻነት በተመልካችነት ጨዋታውን ተከታተለው የፋሲል ከነማው የግራ መስመር ተከላካይ አምሳሉ ጥላሁን ቡድን ለረጅም ደቂቃ 1-0 በመራበት ጨዋታ በመጨረሻ ደቂቃ ሀዋሳ ከተማዎች አቻ የሆኑበት የፍፁም ቅጣት በተሰጠበት መንገድ ደስተኛ አልነበረም። ታድያ በዚህ ደስተኛ ያልነበረው ተጫዋቹ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ወደ ሜዳ ወርዶ የዕለቱን ጨዋታ በዳኝነት ከመሩት ኢንተርናሽናል አልቢትር በላይ ታደሰ ጋር የፈጠረው አምባጓሮ ተጫዋቹን ለትዝብት የዳረገ ክስተት ነበር።

ፋሲል ከነማዎች በሁለት ሺህ ደጋፊዎቻቸው ፊት በተደረገው እና ዋንጫውን በተረከቡበት በዚሁ ጨዋታ ጨዋታውን በድል በመወጣት ድላቸውን ደማቅ ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበራቸው ቢታመንም የአምሳሉን ድርጊት ትክክል ሊያደርግ የሚችል አመክንዮ ግን ፈልጎ ለማግኘት እጅግ ከባድ ነው።

ተጫዋቹም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበረው ቆይታ በተፈጠረው ድርጊት ማዘኑን ገለፆ ለስህተቱም በይፋ ይቅርታ ጠይቋል።

👉 ከሲዳማ በሊጉ መቆየት ጀርባ ያለው ቁልፉ ሰው – ኦኪኪ አፎላቢ

በውድድሩ አጋማሽ ሲዳማ ቡና ከተቀላቀለ ወዲህ ሰባት እጅግ ወሳኝ ግቦችን አስቆጥሯል። በግሉ ግቦችን ማስቆጠር ብቻ ሳይሆን ግብ ማምረት ተስኖት የከረመው የቡድኑ የአጥቂ መስመር ላይ ሌሎች ነባር የቡድኑ ተጫዋቾች ወደ አግቢነት እንዲመለሱ የፈጠረው በጎ ተፅዕኖውም በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ስለዚህ ግዙፉ ናይጄሪያዊ አጥቂ ብዙ መናገር ይቻላል። ወደ ሲዳማ ቡና ከተዘዋወረ ወዲህ በነበሩት የመጀመሪያ ጥቂት ጨዋታዎች ከእንቅስቃሴ ርቆ መቆየቱን በሚያሳብቅ መልኩ ደከም ያለ እንቅስቃሴን ቢያደርግም በባህር ዳሩ እና በድሬዳዋው ውድድር መካከል በነበረው የእረፍት ጊዜ እንደቡድን ፍፁም ተሻሽሎ በቀረበው ሲዳማ ቡና ውስጥ በግሉ ድንቅ መሻሻልን በማሳየት ባለፉት ቅርብ ዓመታት የምናውቀው ኦኪኪ አፎላቢን ዳግም አስመልክቶናል።

ከድሬዳዋው ውድድር ወዲህ በነበሩት እና ላለመውረድ አጣብቂኝ ውስጥ የነበረውን ቡድኑ ተስፋ ያለመለሙ ግቦችን በወሳኝ ጨዋታዎች ጭምር ማስቆጠር የጀመረው አጥቂው ማሸነፍ በሊጉ መሰንበቱን በሚያረጋግጥለት የዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የጅማ አባጅፋሩ ጨዋታ ሐት ትሪክ በመሥራት ቡድን በሊጉ እንዲቆይ አስችሏል።

ለአዲሱ ቡድኑ ባደረጋቸው 10 ጨዋታዎች ሰባት ግቦችን ሲያስቆጥር ሦስት ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል ቡድኑ በሊጉ እንዲቆይ ወሳኝ ሚና ተወጥቷል። የቀድሞ ክለቡ ላይ በዚህኛው ሳምንት የሰራው ሐት ትሪክ በ2013 የውድድር ዘመን በሊጉ ተፅዕኗቸው እየደበዘዘ ከመጡ የውጭ ሀገራት ዜግነት ካላቸው ተጫዋቾች ብቸኛ ሐት ትሪክ መስራት የቻለ እንዲሁም በአንድ ጨዋታ ሦስት ግቦችን ያስቆጠረ አምስተኛ ተጫዋች ያደርገዋል።

ቡድኑ በሊጉ መቆየቱን ካረጋገጠበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ ከጨዋታው አንድ ቀን አስቀድሞ የሲዳማ ቡድን አባላት ከሲዳማ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ጋር ባደረጉት ውይይት ቃል በተገባለት መሰረት ከኮሚሽነሩ የሰዓት ስጦታ ተበርክቶለታል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላም የቡድኑ አሰልጣኝ የሆኑት ገብረመድኅን ኃይሌ ይህን ሲሉ ተደምጠዋል።

“ኦኪኪ በደንብ ጠቅሞናል። እንዲጠቅመንም ነው ያመጣሁት። የወረቀት ሥራዎች ቶሎ ስላላለቁ ዘግየት ብሎ ነው የተቀላቀለን። ግን ተጫዋቹ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ ዛሬም ሆነ ባለፉት ጨዋታዎች ያገባቸው ጎሎች ምስክሮች ናቸው። በአጠቃላይ ኦኪኪ አንድ ለአንድ ተጫዋቾችን የማሸነፍ አቅሙም በጣም ጥሩ ነው። ከዚህ በተጨማሪ አጨራረሱም ጥሩ ነወ። ስለዚህ ቡድኑን በከፍተኛ ሁኔታ ጠቅሟል።”

👉 ተፅዕኖ ፈጣሪው ቅያሬ – ይገዙ ቦጋለ

የውድድር ዘመኑ ሲጀመር የሲዳማ ቡና የፊት መስመር እንዲመራ ተስፋ የተጣለበት ወጣቱ አጥቂ ይገዙ ቦጋለ በተደጋጋሚ ጉዳቶች ሳቢያ ቡድኑን በውድድር ዘመኑ በሚገባ ማገልገል ሳይችል ቀርቷል። በሁለተኛው ዙርም የኦኪኪ አፎላቢ መፈረምን ተከትሎ በቂ የመሰለፍ እድል ለማግኘት ተቸግራል።

ነገርግን ባለፉት ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሁለተኛው አጋማሽ መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ተቀይሮ የሚገባው አጥቂው በሦስቱም ጨዋታዎች ወሳኝ ሶስት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

በዚህም ይገዙ በሊጉ የሀዲያ ሆሳዕናው ዱላ ሙላቱ እንዲሁም ከሰበታ ከተማው ዱሬሳ ሹቢሳ ሁሉ ከሊጉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተቀያሪ ተጫዋቾች ተርታ ማካተት ችሏል።

👉 ወጣቶች እድል ያገኙበት ሳምንት

በኢትዮጵያ እግርኳስ አስገዳጅ ሁኔታዎች ካልተፈጠሩ በቀር ከተስፋ ቡድን የሚያድጉ አልያም በእድሜ ለጋ የሆኑ ተጫዋቾችን በቀላሉ መመልከት አዳጋች ነው። በዚህ የውድድር ዘመን የተመለከትነውም ከዚህ የተለየ አልነበረም።

እንደ ሀዋሳ ከተማ ያሉ ወጣቶችን የማጫወት ልምድ ካላቸው ክለቦች ውጪ ዘንድሮ ወጣት ተጫዋቾች የመሰለፍ ዕድል ተነፍጓቸው የቆዩ ሲሆን በዚህ ሳምንት አመዛኞቹ ክለቦች ለመርሐ ግብር ማሟያነት ያህል ጨዋታ ማድረጋቸውን ተከትሎ ይመስላል በቡድኖቻቸው ውስጥ ለሚገኙ ወጣት ተጫዋቾች የመጫወት እድል ሰጥተዋል።

ባህር ዳር ከተማዎች በወላይታ ድቻ በተሸነፉበት ጨዋታ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ቡድኑን የተቀላቀሉት ይበልጣል አየለ (በቋሚነት)፣ ብሩክ ያለው እና ኃይለሚካኤል ከተማው (ተቀይረው በመግባት) መጫወት ሲችሉ በአዳማ ከተማ በኩል ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ፍራኦል ጫላ ቡድኑ በሰበታ በተሸነፈበት ጨዋታ ለመጀመርያ ጊዜ ተቀይሮ በመግባት ተጫውቷል።

ዋንጫ በተቀበለበት ዕለት ጨዋታ ያደረገው ፋሲል ከነማ ለዳንኤል ዘመዴ፣ ሄኖክ ይትባረክ እና አቤል እያዩ ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ የተሰላፊነት ዕድል ሲሰጡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ለያብስራ ሙሉጌታ (ተቀይሮ በመግባት) በተመሳሳይ ለመጀመርያ ጊዜ እድል ሰጥቷል።

አስራ አምስት ተጫዋቾቹ በማደማቸው ምክንያት አስር ተጫዋቾችን ከተስፋ ቡድኑ ያሳደገው ሀዲያ ሆሳዕና በዚህም ጨዋታ ያሬድ በቀለ፣ ቃለአብ ውብሸት፣ ክብረአብ ያሬድ፣ ደስታ ዋሚሾ፣ ናትናኤል ሄሬጎ እና ምንተስኖት አክሊሉን አጫውቷል።

ባሳለፍነው ክረምት በተለያዩ ምክንያቶች ሳይፀድቅ በቀረው እና በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን እንደቀረበው አይነት ከእድሜ እርከን ቡድኖች ለሚያድጉ ተጫዋቾች አስገዳጅ የጨዋታ ደቂቃዎች ኮታ ማስቀመጥ እስካልተቻለ ድረስ ቡድኖች በወጣት ተጫዋቾች ላይ እምነት አሳድረው እንዲጫወቱ በመፍቀድ ረገድ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ጭምር ያልተሻገረነው ማነቆ ሆኖ ቀጥሏል። በዚህ ሒደት ግን የሀዲያ ሆሳዕና አካሄድ ምንም እንኳን በአስገዳጅ ሁኔታ ቢሆንም የእድሜ እርከን የሌላቸው ሌሎች ክለቦች ወጣቶች ላይ እንዲሰሩ እንዲሁም ተጫዋቾች እድሉን ቢያገኙ ቡድንን በምን ደረጃ መጥቀም እንደሚችሉ ያሳዩበት አጋጣሚ ቡድኖች በተምሳሌትነት በመውሰድ ለወጣት ተጫዋቾች ያላቸውን ዕይታ ዳግም እንዲቃኙ ሊያስገድድ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።