ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

የውድድር ዘመኑ የማሳረጊያ በነበረው የጨዋታ ሳምንት የታዘብናቸው አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች በዚህኛው ፅሁፋችን ተዳሷል።

👉 የቅድመ እና ድህረ ጨዋታ አስተያየቶች

ሊጋችን የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ማግኘቱን ተከትሎ አሰልጣኞች ከጨዋታዎች መጀመር አስቀድሞ እና መጠናቀቅ በኃላ ቅድመ ጨዋታ እና ድህረ ጨዋታ አስተያየቶችን በዘመነ ሱፐር ስፖርት እየተመለከትን እንገኛለን።

እርግጥ ድህረ ጨዋታ አስተያየቶች በሀገራችን እግርኳስ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ጀምሮ እየተዘወተሩ የመጡ ቢሆንም የዘንድሮዎቹን የቅድመ ጨዋታ እና ድህረ ጨዋታ አስተያየቶች ግን ከመቼውም ጊዜ በተሻለ እግርኳሳዊ ሀሳቦች የተነሱበት ነበር።

በቀደሙት ዓመታት ከእግርኳሳዊ ጉዳዮች ይልቅ ሰበብ አስባብ መደርደርያ እና ወቀሳዎችን ማሰሚያ የነበረው መድረክ አሁን ላይ ግን የተሻለ እምርታን አሳይቷል። ነገርግን አሁን ከዚያ አስተሳሰብ ያልተላቀቁ ጥቂት አሰልጣኞችን ይህን ዕድል መሰል የብሶት እና የመቃቀሻ መድረክ ሲያደርጉት ተመልክተናል።

ሌላው በዚህ ሒደት የታዘብነው አብዛኞቹ አሰልጣኞች በሚባል መልኩ ሀሳባቸውን ለመግለፅ የማይቸገሩ በጨዋታው ስላሰቡት እና ስለታዘቡት ጉዳይ በግልፅ የማይሰረዳት አቅማቸው በጣም የሚያስገርም ሆኖ የተመለከትን ሲሆን ጥቂቶቹ ግን አሁንም ራሳቸውን ከሚዲያ ፊት ይዘው ለመቅረብ ማሻሻል የሚገባቸው ጉዳይ መኖሩን ተመልክተናል።

👉 ኮንትራታቸው የሚጠናቀቁ አሰልጣኞች

አብርሃም መብራቱ፣ ዘላለም ሽፈራው፣ ገብረመድህን ኃይሌ እነዚህ አሰልጣኞች አንድ የሚያደርጋቸው የጋራ ጉዳይ አለ። በመጪው ሰኔ 30 ከየክለቦቻቸው ጋር ያላቸው ኮንትራት መጠናቀቁ ነው።

እርግጥ ሌላው የሚያመሳስላቸው ጉዳይ ሁሉም ሲቀጠሩ እናሳካዋለን ያሉትን ግብ አሳክተዋል። አብርሃም መብራቱ ወድድር ዘመኑን ሲጀምር ሰበታን በሊጉ የማቆየት ተቀዳሚ ግብን ከእቅድ በላይ በሚባል መልኩ ቡድኑን በአምስተኛ ደረጃ እንዲበቃ አስችለዋል። በተመሳሳይ በውድድር ዘመኑ አደጋ ውስጥ የነበሩት ወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡናን ተረክበው ወደጥሩ መንገድ የመሩት ገብረመድኅን ኃይሌ እና ዘላለም ሺፈራው ቡድኖቹ ከወራጅ ቀጠና ስጋት እንዲላቀቁ በማስቻል ስኬታማ ጊዜያትን ማሳለፍ ችለዋል።

ታድያ አጭር ጊዜ ውል ቡድኖችን እንደመረከባቸው አሰልጣኞቹ በየቡድኖቻቸው ያላቸውን ውል አራዝመው በቀጣይ የጀመሩትን ሥራ ያጠናቅቃሉ ወይ የሚለው ጉዳይ በትኩረት የሚጠበቅ ጉዳይ ነው።

👉 የአብርሃም መብራቱ መልካም ተግባር

የሰበታ ከተማ ዋና አሰልጣኝ የሆኑት አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ከጨዋታ መጀመር በፊት አሰልጣኞች የሚኖራቸው ቅድመ ጨዋታ ቃለመጠይቅ ወቅት አንዳች የተለየ ነገርን አድርገዋል።

ለወትሮው አስገዳጅ ሁኔታ እስካልተፈጠረ ድረስ በዋና አሰልጣኞች ብቻ ይሰጥ የነበረውን የቅድመ ጨዋታ ቃለ መጠይቅን በመጨረሻው የፋሲል ጨዋታ እርሳቸው ከመስጠት ይልቅ እድሉን ለምክትላቸው ይታገሱ እንዳለ የሰጡበት መንገድ የሚያስመሰግናቸው ነበር።

በአንዳንድ ታላላቅ የአውሮፓ ሊጎች ጭምር ምክትል አሰልጣኞች ለማበረታት የቅድመ ጨዋታ አስተያየትን እንዲሰጡ እድሎች ሲያመቻቹ ይስተዋላል። ይህን አስመልክቶም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ እንዲሁ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

“ሜዳ ውስጥ ለወጣቶች ዕድል ይሰጣል። በተመሳሳይ ደግሞ በማደግ ላይ ያሉ፣ ተስፋ ያላቸው እና መማር የሚፈልጉ አሠልኞችን የማብቃት ስራ ከእኛ ይጠበቃል። ስለዚህ ይሄንን ያደረኩት በእንደዚህ አይነት ትላልቅ ውድድሮች ላይ ራሱን መግለፅ እንዲችል እና ስለ ቡድኑ መናገር እንዲችል ዕድል መስጠት ስለፈለኩኝ ብቻ ነው።”

👉 ዓበይት አስተያየቶች

*ካሣዬ አራጌ ስለቀጣይ ዓመት

“የሚሰሩትን ስህተቶች ብናርም የተሻለ ነገር ማድረግ ስለሚቻል ማረም የግድ ነው የሚሆነው። መቀነስ አለብን ፤ ምንአልባት አንዳንድ ጊዜ በእግር ኳስ ውስጥ መቶ በመቶ ስህተቶችን ማስወገድ ከባድ ሊሆን ይችላል። ግን መቀነስ የምንችላቸው ስህተቶች ስላሉ እነሱን መቀነስ አለብን ብዬ አስባለሁ። ያ ከሆነ የተሻለ ነገር ይኖራል።”

* ሥዩም ከበደ ስለቻምፒየንስ ሊግ ዝግጅት?

“ቡድናችን ዘንድሮ ያሳየው ብቃት እንዳለ ሆኖ ክፍተት ባለባቸው ቦታዎች ላይ ማጠናከሪያ ለማድረግ ፍላጎት አለ። ለዚህም ውድድር ጥሩ ቅድመ ዝግጅት እናደርጋለን። ቢቻል ደግሞ የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ቢገኙ መልካም ነው። እኔም በግሌ ጨዋታ ለማግኘት እየሞከርኩ ነው። ይሄ ቢሳካ መልካም ነው። ዞሮ ዞሮ በቻምፒየንስ ሊጉ ጥሩ ጉዞ ለማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ እናደርጋለን።”

* ገብረመድኅን ኃይሌ ስለ ቀጣይ ዓመት ቆይታው?

“በህጉ ላይ የተቀመጠ አስገዳጅ ነገር አለ። ሲዳማ ለ6 ወር ነው የፈረምኩት። ይሄንን የፈረምኩበት ምክንያትም የትግራይ ክለቦች ይመጣሉ አይመጡም የሚለው ነገር ታሳቢ ተደርጎ ነው። እንግዲህ የእኔን እጣ ፈንታ የሚወስነው በቀጣይ ጊዜያት በሚፈጠሩት ነገሮች ነው። ግን ከሲዳማ ጋር ልቀጥል እችላለሁ ብዬ አስባለሁ።”

* ዘላለም ሽፈራው ስለ ቀጣይ የውድድር ዘመን ዝግጅት?

“ይሄ ከባድ ጥያቄ ነው። ለማንኛውም እኔ የውል ዘመኔ ሀምሌ 30 ይጠናቀቃል። ከዛ በኋላ እንግዲህ እነዚህ ታዳጊዎች ላይ መስራት አንድ ነገር ነው። ምክንያቱም አካባቢው ጥሩ አቅም ያላቸው ልጆች ስላሉበት። አሠልጣኝም 50 ቦታ ከሚሄድ በአንድ ቦታ ቢቆይ ስኬታማ ለመሆን መነሻ ይሆነዋል። ረጅም ጊዜ ቆይታ በማድረግ ማለት ነው። ስለዚህ በቀጣይ የሚሆኑ ነገሮች ቆይታዬን ይወስኑታል።”

* ፍራንክ ናታል ለቀጣዩ ዓመት አዲስ ተጫዋቾችን ስለማስፈረም

“ቡድኑን የተሻለ የሚያደርጉ ከሆኑ አዳዲስ ተጫዋቾችን ታመጣለህ። እሱ በጣም ወሳኝ ነው። ግን ለማምጣት ብቻ ብለህ አዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድንህ አትቀላቅልም። ካሉት የተሻሉ መሆን ስላለባቸው ትክክለኛዎቹን ተጫዋቾች ለማግኘት ምርጫችን ላይ ጥንቁቅ መሆን አለብን።”

* ሙሉጌታ ምህረት በቀጣይ ዓመት የውጪ ግብ ጠባቂዎችን ስለመጠቀም

“እኔ የማስበው እንደ ሀገር ነው። ለሀገር የሚበጀውን ነገር ማድረግ ነው የመጀመሪያው አላማዬ። ደጋግሜ በረኞቼንም የማየው ቀጣይ ዓመታት ላይ ኢትዮጵያዊ በሆኑ ግብ ጠባቂዎች ለማሰራት ነው። ሊበራታቱ እና ሊደገፉ ይገባል። እኔም በዚሁ ሀሳብ እጓዛለሁ።”