ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለሴካፋ ውድድር በቅርቡ ዝግጅቱን ይጀምራል

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ለሚጀምረው የሴካፋ ውድድር የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በቅርቡ ዝግጅቱን የሚጀምር ይሆናል።

የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ውድድር ዕድሜያቸው ከ23 ዓመት በታች በሆኑ ተጫዋቾች በሚዋቀሩ 12 ብሔራዊ ቡድኖች መካከል (አንድ ተጋባዥ ጨምሮ) በኢትዮጵያ አዘጋጅነት ቅዳሜ ሰኔ 26 በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም መካሄድ እንደሚጀምር ይጠበቃል። የዚህ ውድድር አዘጋጅ ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ በአሰልጣኝ ውበቱ እና ምክትሎቻቸው በመመራት በቀጣይ ቀናት ስብስቧን ይፋ እንደምታደርግ ሲጠበቅ የሊጉ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎችን በሀዋሳ ከተማ በአካል በመገኘት የተከታተሉት አሰልጣኝ ውበቱ እና ረዳቶቻቸው የሚመርጧቸው ተጫዋቾችን ለይተው እንዳጠናቀቁና ከዚህ ቀደም በየትኛውም የዕድሜ እርከን በብሔራዊ ቡድን ምርጫ ውስጥ ያልነበሩ አዳዲስ ተጫዋቾች በስብስቡ ከሚካተቱት መካከል እንደሚሆኑ ሰምተናል።

በቅርቡ ይፋ የሚደረገው የተጫዋቾች ስም ዝርዝር ከታወቀ በኋላ የቡድኑ አባላት ወደ ባህር ዳር በማቅናት ዝግጅታቸውን በዛው በማድረግ የውድድሩን መጀመር ይጠባበቃሉ ተብሏል።