የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከነገ ጀምሮ ወደ ዝግጅት ይገባል

የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በሀያ ሰባት ተጫዋቾች ከነገ ጀምሮ የሴካፋ ውድድር ዝግጅት ይጀምራል፡፡

የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) ውድድር ዘንድሮ በተለየ የዕድሜ ዕርከን ዕድሜያቸው ከ23 ዓመት በታች ሆኑ ተጫዋቾች ከሰኔ 26 እስከ ሐምሌ 11 2013 ድረስ በባህር ዳር ከተማ ይካሄዳል፡፡ ለዚህ ውድድር ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከሰሞኑ ለሰላሳ አምስት ተጫዋቾች ጥሪ ያደረጉ ሲሆን ሀያ ሰባት ተጫዋቾች በዛሬው ዕለት ሪፖርት በማድረግ ወደ ካፍ አካዳሚ ለዝግጅት መግባታቸው ታውቋል፡፡ ተጫዋቾቹ በዛሬው ዕለት በፌዴሬሽኑ ተገኝተው ሪፖርት ካደረጉ በኋላ የኮቪድ 19 ምርመራ የከወኑ ሲሆን ውጤቱ ነገ ማለዳ ከደረሰ አመሻሹን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ ልምምድ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አሰቀድሞ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ 35 ተጫዋቾች ጥሪ ማድረግ የቻሉ ቢሆንም በሁለት ምክንያቶች ስምንት ተጫዋቾች ከብሔራዊ ቡድኑ ውጪ መሆናቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡ ከጅማ አባጅፋር የተመረጡት አቡበከር ኑሪ (ግብ ጠባቂ) እና ቤካም አብደላ (አጥቂ)፣ ከአዳማ ከተማ የተመረጠው አብዲሳ ጀማል (አጥቂ)፣ ከወልቂጤ ከተማ ረመዳን የሱፍ (ተከላካይ) እና አብዱልከሪም ወርቁ (አማካይ)፣ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የተመረጠው ተከላካዩ ወልደአማኑኤል ጌቱ የትግራይ ክልል ክለቦች ካልተሳተፉ ለመተካት ከሰኔ 18 ጀምሮ በሚደረገው ውድድር ለክለባቸው ተሰልፈው የሚጫወቱ በመሆኑ ከስብስብ ውጪ እንደሆኑ የተሰማ ሲሆን ከሲዳማ ቡና የተመረጡት ግብ ጠባቂው ፍቅሩ ወዴሳ እና አማካዩ ብርሀኑ አሻሞ በበኩላቸው የፓስፖርት ዕድሜያቸው ከሚጠይቀው የዕድሜ ገደብ በላይ በመሆኑ ከብሔራዊ ቡድኑ ውጪ መሆናቸውን ተረጋግጧል፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ የአንድ ሳምንት ዝግጅቱን በአዲስ አበባ ካደረገ በኋላ ለውድድሩ ወደ ባህርዳር የሚያቀና ይሆናል፡፡