የትግራይ ክልል ክለቦች ከጊዚያዊ አስተዳደሩ ጋር ሊወያዩ ነው

ሦስቱ የትግራይ ክልል ክለቦች ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጋር ለመወያየት ቀጠሮ መያዛቸው ታውቋል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በቤትኩንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ መሳተፍ ያልቻሉት መቐለ 70 እንደርታ ፣ ስሑል ሽረ እና ወልዋሎ በቀጣይ ዓመት ለመሳተፍ በሚችሉበት ሁኔታ ዙርያ በቅርቡ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ከተሾሙት አብርሀም በላይ (ዶ/ር) ጋር ለመወያየት ቀጠሮ መያዛቸው ታውቋል። በክለቦቹ የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ ላይ ወሳኝ ይሆናል በተባለው በዚህ ስብሰባ ላይ ከሦስቱ ክለቦች ውጭ የትግራይ ክልል እግርኳስ ፌደሬሽን እንዲሁም የመቐለ፣ ዓድግራት እና የሽረ እንዳሥላሰ ከተማ አስተዳደሮችም እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

ባለፈው የውድድር ዓመት በክልሉ በተፈጠረው ችግር በፕሪምየር ሊጉ ያልተሳተፉት እነዚህ ክለቦች በቀጣዩ የውድድር ዓመት ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ከሳምንት በፊት ከፌዴሬሽኑ ጋር ባደረጉት ውይይት ቢገልፁም የበጀት ጉዳይ ማነቆ እንደሆነባቸው ከክለቦቹ የሚወጡት መረጃዎች ያመላክታሉ። ክለቦቹ ወደ እግርኳሱ የመመለሳቸው ጉዳይም ቀን ባልተቆረጠለት እና በቅርቡ ይደረጋል በተባለው በዚህ ወሳኝ ውይይት ቁርጡ ይለይለታል ተብሎ ይጠበቃል።