የሴካፋው ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል

በሰኔ ወር መጨረሻ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የሴካፋ ውድድር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል።

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከሳምንታት በኃላ በሚካሄደው የሴካፋ ውድድር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በካፍ የልህቀት ማዕከል ማረፍያውን በማድረግ ከቅዳሜ ጀምሮ በዛው ሜዳ ልምምዱን እየከወነ ይገኛል። በዛሬው ዕለት 28 ተጫዋቾችን በመያዝ ከአስር ሰዓት ጀምሮ ልምምዱን ሲሰራ የተመለከትነው ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ተጫዋቾችን ለይቶ ለማወቅ በሚመስል መልኩ ለሁለት ተከፍለው ሙሉ ዘጠና ደቂቃ ሲጫወቱ ታዝበናል።

ጥሪ ከቀረበላቸው ተጫዋቾች መካከል የኢትዮጵያ ቡናው አማካይ ሬድዋን ናስር ከቡድን አባላት ጋር ልምምድ ሲሰራ አልተመለከትነውም። ምክንያቱ ደግሞ አስቀድሞ በኢትዮጵያ ቡና ያጋጠመው ጉዳት አገርሽቶበት በመሆኑ ሲሆን በዚህም ከብሔራዊ ቡድኑ ውጭ መሆኑን አረጋግጠናል።

ዕድሜያቸው የሚፈቅድላቸው የዋናው ብሔራዊ ቡድን አምስት ተጫዋቾች በቀጣይ ቀናት በስብሰቡ የሚካተቱ ሲሆን በተጨማሪም ዕድሜያቸው ከ23 ዓመት በላይ የሆኑ ተጫዋቾችን በምን ያህል ብዛት መጠቀም እንደሚቻል በቅርቡ ሴካፋ ሲያሳውቅ ተጨማሪ ተጫዋቾች ቡድኑን የሚቀላቀሉ እንደሆነ ሰምተናል።

በአዲስ አበባ ለቀናት የሚቆየው የቡድኑ ዝግጅት የመጨረሻ ስብስቡን በመያዝ ውድድሩ ወደሚስተናገድባት ከተማ ባህር ዳር የሚያቀና ይሆናል።