የስፖርት ዞን የዓመቱ ኮከቦች ሽልማትን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠ

በስድስት ዘርፎች የስፖርት ዞን የዓመቱ የዕዉቅና ፕሮግራም አሰጣጥ አስመልክቶ ዛሬ በቤዝ ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

ያለፉትን ስድስት ዓመታት በሀገር ውስጥ እግርኳስ ላይ ትኩረቱን በማድረግ በፋና ኤፌም 98.1 ከሰኞ እስከ አርብ በጋዜጠኛ ሰዒድ ኪያር እና ጋዜጠኛ መኳንንት በርሄ ዋና አዘጋጅነት ተሰናድቶ የሚቀርበው ስፖርት ዞን በእግርኳሱ ዘርፍ ኮከቦችን ለመሸለም ከወራት በፊት እየተንቀሳቀሰ መቆየቱ ይታወቃል። በዛሬ ዕለትም አራት ሰዓት ላይ በቤዝ ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ሆቴል በስድስት ዘርፍ የመጨረሻዎቹን ሦስት እጩዎች እነማን እንደሆኑ በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አሳውቋል።

የሽልማቱ ዋና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ መኳንንት በርሄ ሽልማቱን ለማበርከት ምክንያት የሆናቸውን ነገር ካብራራ በኃላ በሚዲያ ዘርፍ በስድስት የዲሲፕሊን ዓይነት ኮከቦችን ለመሸለም የተዘጋጀ የመጀመርያ ሚዲያ መሆኑን ገልፆ ምርጫው የተካሄደው የአድማጮች እና የአንባብያን 25% ድምፅ እንዳለ ሆኖ የስፖርት ዞን ኤዲቶሪያል፣ የክለብ አምበሎች፣ አሰልጣኞች እንዲሁም የብሔራዊ ቡድን አምበል እና አሰልጣኞች በኢትዮጵያ እግርኳስ የላቀ አስተዋፆኦ ያበረከቱ እግርኳስ ተጫዋቾች የሚገኙበት ሲሆን በተጨማሪም በሀገር ውስጥ እግርኳስ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ሚዲያዎች መሆናቸውን አሳውቋል።

በድምቀት ይካሄዳል በተባለው በዚህ የኮከቦች መድረክ ልዩ የሆኑ ሽልማቶች እንደሚሰጡ ገልፆ የመጨረሻዎቹ ሦስት ዉስጥ የገቡት እጩዎች የቅድመ ምርጫዉን በተሻለ የጨረሱ መሆናቸው ተብራርቷል። በዚህም መሠረት በስድስቱ ዘርፍ የመጨረሻዎች የሚከተሉት መሆናቸውን ገልፀዋል።

ምርጥ ግብ ጠባቂ ዘርፍ
ሚኬል ሳማኬ፣ ባህሩ ነጋሽ እና አቡበከር ኑሪ

ምርጥ ዋና ዳኛ ዘርፍ
ቴዎድሮስ ምትኩ፣ በላይ ታደሰ፣ ኤፍሬም ደበሌ

ተስፋ የተጣለበት ተጫዋች ዘርፍ
አቡበከር ኑሪ፣ ቸርነት ጉግሳ፣ ዊልያም ሰለሞን

ምርጥ አሰልጣኝ ዘርፍ
ሥዩም ከበደ፣ ካሣዬ አራጌ፣ ዘላለም ሽፈራዉ

ተጓዥ ደጋፊ ዘርፍ
ፋሲል ከነማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና

ምርጥ ተጫዋች
ያሬድ በየህ፣ አቡበከር ናስር፣ ሽመክት ጉግሳ

ይህ የኮከቦች የዕውቅና አሰጣጥ ፕሮግራም ሐምሌ 10 ቀን በካፒታል ሆቴል ምሽት ላይ የሚካሄድ ይሆናል።