እስራኤል እና ኢትዮጵያ አቻ ወጥተዋል

የኢትዮጵያ እና እስራኤል ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖች ሁለተኛ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ዛሬ ተደርጎ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በኢትዮጵያ እና እስራኤል እግርኳስ ፌዴሬሽኖች እግርኳሳዊ ግንኙነት የተገኘው ሁለት የ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የአቋም መለኪያ ጨዋታ ማክሰኞ እና ዛሬ ተደርጓል። ማክሰኞ አመሻሽ በተደረገው ጨዋታ ላይ ቡድኖቹ ያለ ጎል ነጥብ ተጋርተው መውጣታቸው ሲታወስ ዛሬ ደግሞ አንድ አንድ ጎል አስቆጥረው ሳይሸናነፉ ተለያይተዋል።

በአሠልጣኝ እንድሪያስ ብርሃኑ የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ በዛሬው ጨዋታ ኳስ በመቆጣጠርም ሆነ የጠሩ የግብ ማግባት ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ከእስራኤል ተሽሎ ታይቷል። እርግጥ ቡድኑ በመጨረሻው የሜዳ ክፍል ላይ ሲደርስ የውሳኔ እና ያለመናበብ ክፍተቶች ቢስተዋሉበትም ከተጋጣሚው በተሻለ ሜዳውን አካሎ ሲጫወት ተመልክተናል። በመጀመሪያው አጋማሽም ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ ጥሩ ጥቃቶችን ቢፈጥሩም ኳስ እና መረብ ሳይገናኙ አጋማሹ ተገባዷል።

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ሻል ብለው ወደ ሜዳ የገቡት ባለሜዳዎቹ እስራኤሎች ገና አጋማሹ አስር ደቂቃ ሳይሞላው መሪ ሆነዋል። በዚህም በ54ኛው ደቂቃ ከመዓዘን የተሻገረን ኳስ በመጠቀም ኢትዮጵያ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። ወደ ጨዋታው ለመመለስ መታተር የያዙት የኢትዮጵያ ተጫዋቾች በ65ኛው ደቂቃ ወደ ግብ አምርተው አቻ ሊሆኑ የሚችለውን ሁነት ፈጥረዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ቡድኑ ኳስን ከመረብ ጋር ለማዋሀድ ሲጥር የእስራኤሉ ግብ ጠባቂ ከክልሉ ውጪ ኳስ በእጅ በመንካቱ በቀይ ካርድ እንዲወጣ ሆኗል። የዕለቱ ዳኛ የግብ ዘቡን ከሜዳ ካስወጡ በኋላ ለኢትዮጵያ የቅጣት ምት ሰጥተዋል። የተገኘውንም የቅጣት ምት ሚራጅ ነጋሽ በ68ኛው ደቂቃ ከቡድን አጋሮቹ ጋር በፈጠረው ጥሩ መናበብ የእስራኤልን ተጫዋቾች በማስከፈት የአቻነት ጎል አስቆጥሯል።

እስራኤሎች ግብ ጠባቂያቸውን በቀይ ካርድ ሲያጡ ተከላካያቸውን በግቦቹ መሐከል ሆኖ እንዲጫወት ቢያደርጉም ውሳኔያቸውን በ78ኛው ደቂቃ በመቀልበስ በቦታው የሚጫወት ተጫዋት በማስገባት ቀሪውን ደቂቃ ተጫውተዋል። አቻ የሆኑት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በበኩላቸው ያገኙትን የቁጥር ብልጫ በመጠቀም መሪ ለመሆን ቢንቀሳቀሱም ውጥናቸው ሳይሰምር ጨዋታው በአቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።

ብሔራዊ ቡድኑም ዛሬ ለሊት 7 ሰዓት ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ በረራ እንደሚጀምር ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።