አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ለሦስት ተጫዋቾች ጥሪ አድርገዋል

በግል ምክንያታቸው ከብሔራዊ ቡድኑ የተገለሉትን ሁለት እንዲሁም በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ የወጡትን ሦስት ተጫዋቾች ለመተካት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ አዲስ ጥሪ ለሦስት ተጫዋቾች አቅርበዋል።

ከቀናት በኋላ በባህር ዳር ከተማ በሚደረገው የሴካፋ ውድድር ላይ የሚካፈለው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን በካፍ የልዕቀት ማዕከል እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ እያደረገ ይገኛል። በትናንትናው ዕለት ከኢትዮጵያ መድን ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ያደረገው ቡድኑ የግብ ዘቡን ምንተስኖት አሎ እና የአጥቂ መስመር ተጫዋቹ ይገዙ ቦጋለ ‘በግል ምክንያታቸው እና የኮቪድ-19 ክትባት ለመውሰድ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው’ መቀነሱን ዘግበን ነበር።

ከሁለቱ ተጫዋቾች በተጨማሪ ደግሞ ጉዳት ያስተናገዱት ፀጋሰው ድማሙ፣ አማኑኤል እንዳለ እና ኃይለሚካኤል አደፍርስ በዛሬው ዕለት የብሔራዊ ቡድኑን ስብስብ ለቀው መውጣታቸው ተሰምቷል። ከቡድኑ በወጡት ምትክ ተጫዋች ወደ ስብስባቸው ለመቀላቀል ያለሙት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ለሦስት ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጋቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ብሔራዊ ቡድኑን እንዲቀላቀል ጥሪ የቀረበለት የመጀመሪያው ተጫዋች የኢትዮጵያ ቡናው የመስመር ተከላካይ አሥራት ቱንጆ ነው። ሁለተኛው ተጫዋች ደግሞ በመጀመሪያው ዙር የተጫዋቾች ጥሪ ውስጥ ስሙ ተካቶ የነበረው ነገር ግን በጡንቻ ጉዳት ምክንያት ተቀንሶ የነበረው የኢትዮጵያ መድህኑ የግብ ዘብ ታምራት ዳኜ ነው። የመጨረሻው የብሔራዊ ቡድኑን ስብስብ የተቀላቀለው ተጫዋች የሰበታ ከተማው የመሐል ተከላካይ መሳይ ጳውሎስ ነው። ሦስቱ ተጫዋቾች ጥሪ ከቀረበላቸው በኋላ ዛሬ ቡድኑ መቀመጫውን ባደረገበት የካፍ የልህቀት ማዕከል በመገኘት መደበኛ ልምምዳቸውን መሥራት ጀምረዋል።