ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ኢንስትራክተሮች ወደ ቢሾፍቱ አምርተዋል

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ወንድ እና ሴት የካፍ ኢንስትራክተሮች ለአምስት ቀን ቆይታ ከነገ ጀምሮ በቢሾፍቱ ከተማ ሊከትሙ ነው።

የአፍሪካ እግርኳስ የበላይ አካል የሆነው ካፍ የአባል ሀገራቱን የአሠልጣኞች ስልጠና ደረጃ ከፍ ለማድረግ ከወራቶች በፊት እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወቃል። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ክፍልም ካፍ በሰጠው መመሪያ መሠረት በሀገራችን ከሚገኙ የካፍ ኢንስትራክተሮች ጋር በመሆን የአሠልጣኞችን ስልጠና የሚሰጥበትን ማኑዋል በማዘጋጀት ላይ ይገኝ ነበር። በአትኩሮት ሲዘጋጅ የነበረው የአሠልጣኞች ስልጠና ማኑዋልም ተዘጋጅቶ አልቆ ለካፍ መላኩ ይታወቃል። ካፍ በሰጠው ግብረ መልስም የተዘጋጀው ማኑዋል “እጅግ ጥሩ” መሆኑን አውስቶ ስልጠናው የሚሰጥበት ፕሮግራም እንዲዘጋጅ አቅጣጫ አስቀምጧል።

በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ሦስቱ እንስቶችን (መሠረት ማኒ፣ ሰላም ዘርዓይ እና በኃይሏ ዘለቀ) ጨምሮ በአጠቃላይ በሀገራችን የሚገኙት አስር የካፍ ኢንስትራክተሮች ለአሠልጣኞች በየደረጃው የሚሰጠውን ስልጠና ፕሮግራም ለማውጣት ዛሬ አመሻሽ ቢሾፍቱ ከተማ ገብተዋል። የኢንስትራክተሮቹ ፓነልም ጉዳዩን በበላይነት ከሚመራው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ክፍል ጋር በመሆን ለአምስት ቀን ፕሮግራሙን እንደሚቀርፁ እንዲሁም ከፕሮግራሙ ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ ግብዓቶች ለማግኘት ስራዎች እንደሚሰሩ ሰምተናል።

ይህ ሂደት ደግሞ ለረጅም ጊዜ በብዙዎች ዘንድ ሲጠየቅ የነበረውን የአሠልጣኞችን የስልጠና ይሰጠን ጥያቄ በአጭር ጊዜ መልስ እንደሚሰጥ ይታሰባል። ፕሮግራሙም ተሰርቶ ለካፍ ከተላከ በኋላ ሲፀድቅ በአራቱም ደረጃዎች (A,B,C,D) የሚሰጡት ስልጠናዎች መቼ መሰጠት እንደሚጀምሩ የሚገለፅ ይሆናል።