ኢትዮጵያ ቡና ማክሰኞ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ይጀምራል

በተጠናቀቀው የ2013 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተካፋይ መሆኑን ያረጋገጠው ኢትዮጵያ ቡና ለውድድሩ ይረዳው ዘንድ ከመጪው ማክሰኞ አንስቶ በቢሾፍቱ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን የሚያደርግ ይሆናል።

በአሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ የሚመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጪው የውድድር ዘመን ላሉባቸው አህጉራዊ እና ሀገራዊ ውድድሮች ስብስባቸውን አጠናክሮ ለማቅረብ ከወዲሁ በዝውውር መስኮቱ በንቃት እየተሳተፉ የሚገኙ ሲሆን እስካሁን የአምስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲያጠናቅቁ የአሥራት ቱንጆ እና ኃይሌ ገ/ተንሳይን ጨምሮ የወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን ውል በማራዘም ላይ ይገኛሉ።

ከአስር ዓመት በኋላ ወደ አህጉራዊ ውድድር የተመለሱት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከጳጉሜ 5 እስከ መስከረም 2 ባሉት ቀናት የመጀመሪያውን፤ እንዲሁም ከመስከረም 7 እስከ 9 ባለው ጊዜ ውስጥ ሁለት የደርሶ መልስ የቅድመ ማጣርያ ጨዋታዎች የሚጠብቃቸው ሲሆን ቡድኑ በቀጣዩቹ አስራ አራት ቀናት ለውድድሩ የሚጠቀምባቸውን ተጫዋቾች እንዲያሳውቅ በካፍ የጊዜ ገደብ የተቀመጠለት እንደመሆኑ የተጫዋቾችን ዝውውርን በፍጥነት ማጠናቀቅ ይጠበቅበታል።