ፅዮን መርዕድ ከጣና ሞገዶቹ ጋር ተለያይቷል

የአንድ ዓመት ውል የሚቀረው ግብ ጠባቂው ፅዮን መርዕድ በስምምነት ከባህር ዳር ከተማ ጋር መለያየቱ እርግጥ ሆኗል።

በአርባምንጭ ከተማ የተወለደው የግብ ዘቡ ፅዮን መርዕድ በትውልድ ከተማው ክለብ ባሳየው ምርጥ ብቃት 2012 ላይ ወደ ባህር ዳር ከተማ ማቅናቱ ይታወቃል። በኮቪድ-19 ምክንያት የተሰረዘውን እና የዘንድሮውን የውድድር ዘመን ያጠናቀቀው ተጫዋቹም የአንድ ዓመት ውል ከባህር ዳር ጋር ቢቀረውም ከክለቡ ጋር በስምምነት መለያየቱ ተረጋግጧል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አስራ አንድ ጨዋታዎችን (990) ያደረገው ፅዮን ይህንን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ መልቀቂያ ባይወስድም ወደ ሌላ ክለብ ለማምራት ንግግር ላይ መሆኑን ተረድተናል።

ከቀናት በፊት በተጠናቀቀው የሴካፋ ከ23 ዓመት በታች ውድድር ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ከነበረው ፅዮን በተጨማሪ ባህር ዳርን ዓምና ተቀላቅሎ የነበረው አጥቂው ባዬ ገዛኸኝ በተመሳሳይ የአንድ ዓመት ውል ቢኖረውም ክለቡ እንዲለቀው ያስገባው ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱን ሰምተናል። ይህንን ተከትሎም ከቀናት በፊት ከሀዲያ ሆሳዕና እና ሰበታ ከተማ ጋር እንደተስማማ የተገለፀው ባዬ በቀጣይ የውድድር ዘመን በአዲስ ክለብ ማየታችን እርግጥ ሆኗል።