ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አዳማ ከተማ ሦስት ተጫዋቾችን ሲያፈርም የአራት ነባሮችን ውል አድሷል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ተካፋዩ አዳማ ከተማ የሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲፈፅም አራት ነባር ተጫዋቾቹን ውል ደግሞ አድሷል።

የዋና አሰልጣኙ ሳሙኤል አበራን ውል ያራዝማል ወይንስ አዲስ አሰልጣኝ ይሾማል የሚለው ጉዳይ ሳይጠናቀቅ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ተወዳዳሪው አዳማ ከተማ በሌሎች የቡድኑ አሰልጣኞች መሪነት አዳዲስ ተጫዋቾችን ማስፈረም እና ነባሮችን ውል ማራዘምን ጀምሯል፡፡

ደመቀች ዳልጋ የአዳማ የመጀመሪያዋ ፈራሚ ተጫዋች ሆናለች፡፡ የቀድሞዋ የንግድ ባንክ እና ያለፈውን የውድድር ዓመት ደግሞ በጌዲኦ ዲላ ያሳለፈችው አጥቂዋ ማረፊያዋ አዳማ ሆኗል፡፡የአዲስ አበባ ከተማዋ ፈጣን የመስመር አጥቂ በሻዱ ረጋሳ እና በተመሳሳይ ከአዲስ አበባ ከተማ የመስመር ተከላካዩዋ የውብዳር መስፍንም አዳማን የተቀላቀሉ አዲስ ፈራሚዎች ናቸው፡

አዳማ ከተማ ከሦስቱ አዳዲስ ተጫዋቾች በተጨማሪ የአራት ነባር ተጫዋቾቹን ውልም ለተጨማሪ ሁለት ዓመት አራዝሟል፡፡ የቀድሞዋ የደደቢት፣ አአ ከተማ፣ ንግድ ባንክ እና መቐለ 70 እንደርታ አማካይ ቅድስት ቦጋለ፣ የቀድሞዋ የሀዋሳ ከተማ አጥቂ ምርቃት ፈለቀ፣ ፈጣኗ የመስመር አጥቂ ሰርካዲስ ጉታ እና ሰላማዊት ላዕከም በክለቡ ለተጨማሪ ዓመት ለመቆየት ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡