አዳማ ከተማ የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል

በአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመሩት አዳማ ከተማዎች ከደቂቃዎች በፊት የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር አገባደዋል።

ቡድኑን የተቀላቀለው የመጀመሪያው ተጫዋች ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው ነው። የቀድሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ደደቢት፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ መከላከያ፣ ጅማ አባ ቡና፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ፋሲል ከነማ እና ወልቂጤ ከተማ የግብ ዘብ የነበረው ጀማል ከቀናት በፊት መዳረሻው አዳማ ሊሆን እንደተቃረበ ዘግበን ነበር። የሁለቱ አካላት ድርድር ፍሬ አፍርቶም ተጫዋቹ በዛሬው ዕለት የ2 ዓመት ውሉን ፈርሟል።

ሁለተኛው ደግሞ ሁለገቡ ተጫዋች ምንተስኖት አዳነ ነው። 2001 ላይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተስፋ ቡድን ወደ ዋናው ቡድን ያደገው ምንተስኖት ክለቡን በአማካይ እና ተከላካይነት ቦታ ማገልገሉ አይዘነጋም። አሁን ደግሞ ውሉ መጠናቀቁን ተከትሎ ከአሳዳጊ ክለቡ ጋር ተለያይቶ ጉዞውን ወደ አዳማ ከተማ አድርጓል።