“ለከነማዬ እሮጣለው” በሚል መሪ ቃል ለአርባምንጭ ከተማ ክለብ የገቢ ማስገኛ ሩጫ ዛሬ ተካሄደ

የአርባምንጭ ከተማ እግር ኳስ ክለብን በገቢ ለማጠናከር የተለያዩ የገቢ ማስገኛ መርሀግብሮች እየተደረጉ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ “ለክለቤ እሮጣለሁ” በሚል ስያሜ በከተማዋ ሩጫ ተካሂዷል፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ጉልህ ድርሻ ካላቸው አካባቢዎች መሐል አርባምንጭ አንዱ ነው፡፡በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከዚህ ቀደም ተሳታፊ የነበረው እና ወደ ከፍተኛ ሊጉ ወርዶ በድጋሚ ከሦስት ዓመታት በኋላ ወደ ሊጉ የተመለሰው አርባምንጭ ከተማ በፕሪምየር ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ እንዲሆን እና በድጋሚ የመውረድ ስጋት እንዳይገጥመው በገቢ መጠናከር ይኖርበታል በማለት ክለቡ ራሱን በፋይናንስ ከሰሞኑ ማጠናከር ላይ ተጠምዷል፡፡ ከቀናቶች በፊት በአርባምንጭ እና አካባቢ የሚገኙ ባለሀብቶችን በማስተባበር የገቢ ማስገኛ የእራት መርሀግብር ያከናወነ ሲሆን በዛሬው ዕለት ቅዳሜ ጠዋት ደግሞ በርካታ የክለቡ ደጋፊዎች፣ የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ፣ ተጫዋቾች፣ የክለቡ ወዳጆች እንዲሁም ከፍተኛ የመንግሥት አካላት እና ሌሎችም ጭምር የተሳተፉበትን “ለከነማዬ እሮጣለው” በሚል ስያሜ የሩጫ መርሀግብርን አካሂዷል፡፡

የሩጫ መርሀግብሩ ከተጠናቀቀ በኋላ የጋሞ ዞን ምክትል አስተዳደሪ እና የክለቡ የበላይ ጠበቂ አቶ ብርሀኑ ዘውዴ ክለቡን ለመደገፍ ሁሉም አካላት ተሳትፎ ማድረግ በመቻላቸው ምስጋናን ያቀረቡ ሲሆን የክለቡ ፕሬዝዳንት እና የከተማው ከንቲባ ሰብስቤ ቡናቤ በበኩላቸው በተመሳሳይ ለተሳታፊዎች ምስጋናን አቅርበው ልክ በሩጫው የታየውን ርብርብ በተለያዩ ወቅቶች ከክለቡ ጎን በመሆን እንዲደግሙት በንግግራቸው ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻም በሩጫው ተሳትፈው ከአንድ እስከ ሦስት በሁለቱም ፆታ ለወጡት የተለያዩ ሽልማቶች ተሰጥቶ ሥነ ስርዓቱ ተጠናቋል፡፡