አማካዩ በግል ጉዳይ ከብሔራዊ ቡድኑ ውጪ ሆኗል

በቅርቡ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሪ የተደረገለት የአማካይ ስፍራ ተጫዋች በግል ጉዳይ ብሔራዊ ቡድኑን አይቀላቀልም፡፡

ከሰሞኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ ከጋና እና ከዚምባብዌ ጋር ለምታደርገው የማጣሪያ ጨዋታዎች ለሀያ ስምንት ተጫዋቾች ጥሪ ሲያደርጉ ሰባቱ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የተጠሩ መሆናቸው አይዘነጋም። ከእነኚህ መካከል አንዱ ደግሞ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ሀይደር ሸረፋ ይገኝበታል፡፡ እስከ አሁን ከተጠሩት ተጫዋቾች መካከል ሀያ አምስቱ እስከ ትናንት ድረስ በካፍ የልዕቀት ማዕከል በመገኘት ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን ተከላካዩ ረመዳን የሱፍ እና አማካዩ ታፈሰ ሰለሞን በቀጣይ ብሔራዊ ቡድኑን ይቀላቀላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተመላክቷል።

የቅዱስ ጊዮርጊሱ አማካይ ሀይደር ሸረፋ ግን የፊታችን ቅዳሜ በሚፈፅመው የጋብቻ ሥነ-ስርዓት ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር በመነጋገር ከብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ ውጪ መሆኑን ሶከር ኢትዮጵያ ማረጋገጥ ችላለች፡፡