ተጨማሪ ተጫዋች ከብሔራዊ ቡድኑ ውጪ ሆኗል

እንደ ሀይደር ሸረፋ ሁሉ በግል ምክንያት የአጥቂ መስመር ተጫዋች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውጪ ሆኗል።

ከሦስት ቀናት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከፊታቸው ላለባቸው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ለ28 ተጫዋቾች ጥሪ ማቅረባቸው አይዘነጋም። ጥሪ የደረሳቸው ተጫዋቾችም በትናንትናው ዕለት ሲ ኤም ሲ አካባቢ በሚገኘው የካፍ የልዕቀት ማዕከል እየተገኙ ሪፖርት በማድረግ እየተሰባሰቡ ይገኛሉ። ሶከር ኢትዮጵያ ከደቂቃዎች በፊት ባወጣችው ዘገባ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የተመረጠው የአማካይ መስመር ተጫዋቹ ሀይደር ሸረፋ በሳምንቱ መጨረሻ ጋብቻ ስለሚፈፅም ከአሠልጣኙ ጋር በመነጋገር ከስብስቡ እንደወጣ አትታ ነበር።

ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በተያያዘ ሌላ ዜና ደግሞ ከቀናት በፊት ለሦስት ዓመታት ግልጋሎት ከሰጠበት ፋሲል ከነማ ጋር የተለያየው እና ወደ አልጄሪያ ለማምራት ሂደት ላይ የሚገኘው አጥቂው ሙጂብ ቃሲም በተመሳሳይ ስብስቡን እንደማይቀላቀል ተገልጿል። ተጫዋቹ ወደ አዲሱ የአልጄሪያ ክለቡ ጄ ኤስ ካቢሌ ለመዘዋወር እንቅስቃሴ ላይ በመሆኑ ምክንያት ስብስቡን ሊቀላቀል እንዳልቻለም ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ከጠሯቸው ተጫዋቾች ሁለቱን እንደማያገኙ ያወቁት አሠልጣኝ ውበቱ አባተም ያላቸውን ስብስብ በማየት ምናልባት ለአዳዲስ ተጫዋቾች ጥሪ ሊያቀርቡ እንደሚችሉ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።