ዓመታዊው የሀዋሳ ቄራ ዋንጫ በዛሬው ዕለት ተጠናቀቀ

የሀዋሳ ቄራ ዋንጫ የ20ኛ ዓመት ውድድሩን ከሐምሌ 8 ጀምሮ በ32 ቡድኖች መካከል ሲያካሂድ ቆይቶ በዛሬው ዕለት በበርካታ ደጋፊዎች ፊት በቢ ቤስት ቡድን አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ከተሞች ክረምት በመጣ ቁጥር የተለያዩ የእግር ኳስ ውድድሮች ይደረጋሉ፡፡ በተለይ በአብዛኛው በወጣቶች የራስ ተነሳሽነት የሚደረጉ ውድድሮች ደግሞ ላቅ ያለውን ቦታ ይይዛሉ፡፡ ከእነኚህ በክረምት ከሚደረጉ የእግርኳስ ውድድሮች መካከል 20ኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘው የሀዋሳ ቄራ ዋንጫ ውድድር ሁለት ዓመታትን በተለያዩ ምክንያቶች ሳይደረግ ቆይቶ ዘንድሮ ከሐምሌ 8 ጀምሮ በ32 ቡድኖች መካከል ለአንድ ወራት ያህል ተካሂዶ በዛሬው ዕለት በርካታ ተመልካች በተገኘበት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

እጅግ ለቁጥር የላቁ ተጫዋቾች የፈሩበት እና በየዓመቱ በተመልካቾች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቀው ይህ ውድድር ዛሬ ረፋድ 5፡00 ላይ ለዋንጫ የቀረቡት ቢ ቤስት እና መታፈሪያ ክፍሌ ኮንስትራክሽንን አገናኝቶ ነበር፡፡ በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ብሩክ ዘውዱ ለቢ ቤስት ምንተስኖት ማቲዮስ ለመታፈሪያ ኮንስትራክሽን አስቆጥረው 1ለ1 በሆነ አቻ ከተጠናቀቀ በኃላ በተሰጠው የመለያ ምት ጨዋታውን ቢ ቤስት 4 ለ 3 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የ2013 የሀዋሳ ቄራ ዋንጫ አሸናፊ መሆን ችለዋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በርካታ የሽልማት ሥነ ስርዓት መርሀግብር ተካሂዷል፡፡ በውድድሩ የተካፈሉ ዳኞች ክለቦች፣ ውድድሩን በተለያየ ዘርፍ የመሩ ኮሚቴዎች ፣ የስራ ኃላፊዎች ፣ የፀጥታ አካላት እና ለውድድሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የሰርተፍኬት እና የማበረታቻ ገንዘብ የተበረከተ ሲሆን በመቀጠል በውድድሩ ምርጥ ለሆኑት የገንዘብ እና የቁሳቁስ ሽልማት ተሰጥቷል፡፡ 

በኮከብ ዳኝነት ማሞ ሴባ በረዳት ዳኝነት በተመሳሳይ ነጥብ በረከት ባሌ እና በዛብህ ካቲሶ የተመረጡ ሲሆን የዛሬው ጨዋታ ኮከብ ተብሎ የተመረጠው የቢ ቤስቱ ብሩክ ዘውዱ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ተብሎም ተሸላሚ ሆኗል፡፡ በኮከብ ግብ አግቢነት አሁንም ከቢ ቤስት ተመስገን አሸብር በግብጠባቂነት በተመሳሳይ ከሻምፒዮኑ ክለብ ዮሐንስ ዮሴፍ፣ ወጣቱ የቢ ቤስት አሰልጣኝ አመሀ ዘውዴ ደግሞ በኮከብ አሰልጣኝነት የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ተቀብለዋል፡፡

ሀቫና ላውንጅን 3ለ1 የረቱት የውድድሩ በእድሜ ትንንሽ ተጫዋቾችን የያዘው ቢ ኤፍ ቲ ምስራቅ ሶስተኛ በመውጣቱ የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሲሆኑ በቡድኑ ውስጥ ጎልቶ የታየው ታዳጊው ሀብታሙ ክስተት በሚል ልዩ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁት መታፈሪያ ክፍሌ ኮንስትራክሽን የብር ሜዳሊያ የ15 ሺህ ብር እና የፀባይ ዋንጫ ፣ ሻምፒዮኑ ቢ ቤስት የ20 ሺህ ብር የወርቅ ሜዳሊያ እና የዋንጫ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን ተጨማሪ የ10 ሺህ ብር ሽልማትም ከመደበኛው በተጨማሪ የሀይቅ ዳር ክፍለ ከተማ አበርክቷል፡፡

በርካታ ቡድኖችን በማሳተፍ የሚታወቀው እና የፕሪምየር ሊግ እና የተለያዩ አሰልጣኞች ታድመው ተጫዋች የሚመለከቱበት ይህ ውድድር ዘንድሮም በተመሳሳይ አሰልጣኞች ይህን ውድድር ሲከታተሉት አስተውለናል፡፡ ውድድሩን ለመታደም ከየቤቱ ወንበር ይዘው የሚመጡ ተመልካቾችን በተደጋጋሚ መመልከት የተለመደበት ይህ የቄራ ዋንጫ በቀጣይ ጊዜያት ሜዳው ካለበት ደረጃ የተለያዩ ማሻሻያዎች ሊሰሩበት እንደሆነም አቶ ጥላሁን ሀሚሶ የሀዋሳ ከተማ ስፖርት መምሪያ ሀላፊ በመዝጊያው ሥነ ስርዓት ላይ ተገኝተው ገልፀዋል፡፡