የሙጂብ ቃሲም ዝውውር ዕክል ገጥሞታል

ወደ አልጄሪያው ክለብ እንደሚያመራ የተነገረለት ሙጂብ ቃሲም የዝውውሩ ሂደት መስተጓጉል እንዳጋጠመው ተሰምቷል።

ከፋሲል ከነማ ጋር ቀሪ ኮንትራት እያለው በቅርቡ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ በማጠናቀቅ ውሉን አፍርሶ ወደ አልጄሪያው ክለብ ጄይኒስ ስፖርቲቭ ዲ ካቢሌ ለሦስት ዓመት ለመጫወት መስማማቱን ይታወሳል። የዝውውሩ አብዛኛው ሒደት የተጠናቀቀ ቢሆንም የሙጂብ ፈላጊ ክለብ በቀጥታ ለማስፈረም የነበረውን ስምምነት በመቀየር በሙከራ ለመውሰድ ወስኗል።

ክለቡ ይህ አዲስ ሀሳብ ይዞ የመጣው አዲስ የውጭ አሰልጣኝ በቅርቡ ከመሾሙ ጋር ተያይዞ መሆኑን ወኪሉ ጠቁሞናል። ይህ የስምምነት ለውጥ ክለቡ ማቅረቡን ተከትሎ ሙጂብንም ሆነ ኤጀንቱን ሊያስደስት አልቻለም። አስቀድሞ በነበረው ስምምነት መሠረት በቀጥታ ሙጂብን ማስፈረም በሚቻልበት መንገድ ዙርያ በወኪሉ በኩል በድጋሚ የማሳመን ድርድር እየተደረገ ይገኛል።

የድርድሩን ውጤቱን ክለቡ ዛሬ እንደሚያሳውቅ ሲጠበቅ ሙጂብ በሚፈልገው መልኩ የሚሳካ ከሆነ ወደ አልጄሪያ መሄዱ ነገር እውን ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። አለበለዚያ ግን ክለቡ በአቋሙ የሚፀና ከሆነ የሙጂብ ወደ አልጄሪያ የመሄዱ ነገር የማይሳካ መሆኑን ሰምተናል።

ሙጂብ ወደ አልጄሪያው ክለብ ጄይኒስ ስፖርቲቭ ዲ ካቢሌ የማይጓዝ ከሆነ በሌላ ክለብ ማልያ እንመለከተዋለን ወይ የሚለው ጉዳይ እጅግ ተጠባቂ ነው።