ኤርትራ በሰፋ የድምር ውጤት ጂቡቲን ረታ ወደ ቀጣይ ዙር አልፋላች

በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የተደረገው የኤርትራ እና ጂቡቲ የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ቡድኖች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በኤርትራ 6-1 የድምር ውጤት አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።

በኮስታሪካ አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የሴቶች የዓለም ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸው የአፍሪካ ሀገራት የመጀመሪያ ዙር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎችን እያከናወኑ እንደሆነ ይታወቃል። የዚህ ዙር አካል የሆነው እና በወቅታዊ ጉዳዮች ምክንያትም አዲስ አበባ ላይ እንዲከናወን የተወሰነው የኤርትራ እና ጂቡቲ ጨዋታ የመጀመሪያው መርሐ-ግብር ከሁለት ቀናት በፊት አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ ተከናውኖ በኤርትራ 3-1 አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል። ዛሬ ደግሞ የመልሱ ጨዋታ ተከናውኖ በተመሳሳይ ኤርትራን አሸናፊ አድርጓል።

ተመጣጣኝ ፉክክር ያስመለከተው የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ በጅማሮው ላይ ከግብ ማግባት ሙከራዎች የራቀ ቢሆንም ጥሩ የኳስ ፍሰት ታይቶበታል። 23ኛው ደቂቃ ላይ ግን ኤርትራ የመጀመሪያውን የጨዋታው ሙከራ ሰንዝራለች። በዚህ ደቂቃ ላይም ከወደ ግራ ባዘነበለ ቦታ የተገኘውን የቅጣት ምት የቡድኑ አምበል ራህዋ ተወልደመድህን በቀጥታ ወደ ግብ የመታችው ቢሆንም ግብ ጠባቂዋ እንደምንም ጨርፋ አውጥታዋለች። 

3-1 ከተረቱበት ጨዋታ በአንፃራዊነት ተሻሽለው የመጡት ጂቡቲዎች በ29ኛው ደቂቃ በራሳቸው በኩል የመጀመሪያውን የሰላ ጥቃት ፈፅመዋል። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ የቀኝ መስመር አጥቂዋ ፌሩዝ ሙሐመድ ፍጥነቷን ተጠቅማ ወደ ሳጥን በመግባት የሞከረችው ኳስ መዳረሻው መረብ ሳይሆን ቀርቷል። አጋማሹም ያለ ተጨማሪ የጠራ ሙከራ 0-0 ተጠናቋል።

የሁለተኛውን አጋማሽ በጥሩ ተነሳሽነት የጀመሩት ኤርትራዎች ገና በጅማሮው በምስጋና ማህሪ አማካኝነት ኳስ እና መረብን አገናኝተው መሪ ሆነዋል። ከእረፍት መልስ ገና በጊዜ መሪነት የተወሰደባቸው ጂቡቲዎች ደግሞ ወደ ቀጣይ ዙር የሚያሳልፋቸውን ውጤቱ ወደ ራሳቸው ለማድረግ መታተር ቢይዙም እምብዛም ፍሬ ማፍራት አልቻሉም ነበር።

ጨዋታው 75ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስም ኤርትራ የጨዋታውን ሁለተኛ በአጠቃላይ አምስት ለአንድ የምትመራበትን ጎል አግኝታለች። በዚህም ጎቦችን ለማስቆጠር ግዴታ የሆነባቸው ጂቡቲዎች ለማጥቃት ትተውት በወጡት ቦታ ዲያና እስቲፋኖስ ከደሊና ሳህሌ ጋር ተናባ ያገኘችውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይራዋለች። 

እነዚህ ግቦች ያልበቃቸው ኤርትራዎች ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃዎች ሲቀሩት በግራ መስመር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል አምርተው የማሳረጊያውን ጎል አስቆጥረዋል። በዚህም ዲያና እስቲፋኖስ የራሷን ሁለተኛ የቡድኗን ደግሞ ሦስተኛ ኳስ ከመረብ ጋር አዋህዳለች። ጨዋታውን በኤርትራ ሦስት ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።

በድምር ውጤት 6-1 ያሸነፈው የኤርትራ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንም ወደ ሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታ ማለፉን አረጋግጧል። በቀጣይ ዙርም ኤርትራ የታንዛኒያ አቻዋን ትገጥማለች።