የአርሰናሉ አማካይ ከኢትዮጵያው ጨዋታ ውጪ ሆኗል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የሚገጥመው የጋና ስብስብ ውስጥ የነበረው ቶማስ ፓርቲ ባጋጠመው ጉዳት ከጨዋታው ውጪ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ2022 ለሚከናወነው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከጋና፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዚምባቡዌ ጋር መደልደሉ ይታወሳል። ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታውንም ነሐሴ 28 በኬፕ ኮስት ስታዲየም ከጋና ጋር ያከናውናል። በአሠልጣኝ ቻርለስ አኮኖር የሚመራው የጋና ብሔራዊ ቡድንም ከቀናት በፊት ለኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካው ጨዋታ 30 ተጫዋቾችን ጠርቶ እንደነበር ገልፀን ነበር። አሁን የጋና ብዙሃን መገናኛዎች እያወጡት ባሉት መረጃ ደግሞ የቡድኑ አምበል ቶማስ ፓርቲ ባጋጠመው ጉዳት ከወሳኞቹ የምድብ ጨዋታዎች ውጪ እንደሆነ ይጠቁማሉ።

አሠልጣኝ ቻርለስ አኮኖር በጠሩት የ30 ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ ስሙ የነበረው የ27 ዓመቱ አማካይ ከቀናት በፊት ክለቡ አርሰናል ከቼልሲ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አከናውኖ 2-1 ሲረታ ጉዳት አስተናግዶ ነበር። ይህ ጉዳትም ተጫዋቹን ለሁለቱ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች እንደማያደርሱት አሠልጣኝ ቻርለስ ኦኮሮር ተናግረዋል።