የነገውን የዋልያው የአቋም መለኪያ ጨዋታ የሚመሩ ዳኞች ታውቀዋል

ነገ ዘጠኝ ሰዓት የኢትዮጵያ እና ሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድኖች የሚያደርጉትን የአቋም መፈተሻ ጨዋታ የሚመሩ ዳኞች ታውቀዋል።

ለኳታሩ የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ከፊቱ የሚጠብቁት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅት እያደረገ ሲገኝ አቋሙንም ለመፈተሽ ነገ እና እሁድ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ያከናውናል። ለእነዚሁ ሁለት ጨዋታዎች ትናንት ከመጀመሪያ ተጋጣሚው ሴራሊዮን ጋር ባህር ዳር የገባው ቡድኑም ዛሬ የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቷል። የሴራሊዮን አቻውም እንደ ዋልያው ሁሉ በስታዲየሙ በመገኘት ከጨዋታው በፊት የመጨረሻ ልምምዱን አከናውኗል።

ነገ ዘጠኝ ሰዓት የሚደረገውን የሁለቱ ሀገራት የአቋም መለኪያ ጨዋታም ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ለሚ ንጉሤ በመሐል ዳኝነት እንደሚመሩት ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል። የመሐል ዳኛውም ከረዳቶቻቸው (ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኞች) ክንዴ ሙሴ እና ይበቃል ደሳለኝ ጋር በመሆን ጨዋታውን እንደሚመሩትም ታውቋል። የጨዋታው አራተኛ ዳኛ ደግሞ ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው መሆኑ ተረጋግጧል።

ያጋሩ