የመዲናይቱ ክለቦች የወዳጅነት ጨዋታ ሊያደርጉ ነው

የቅድመ ውድድር ዝግጅት ላይ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና እርስ በእርስ የወዳጅነት ጨዋታ ሊያደርጉ ነው።

የሀገሪቱ የከፍተኛ የሊግ እርከን (ፕሪምየር ሊግ) ክለቦች ለ2014 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ፍልሚያ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን እንደጀመሩ ይታወቃል። አህጉራዊ የቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች የሚጠብቃቸው ፋሲል እና ቡና ደግሞ ቀደም ብለው ለወሳኞቹ ግጥሚያቸው ዝግጅት ከጀመሩ ሰነባብተዋል።

ከሁሉም ክለቦች ቀድሞ ዝግጅት የጀመረው የአሠልጣኝ ካሣዬ አራጌ ስብስብ ደግሞ ቢሾፍቱ ላይ ዝግጅቱን ሲሰራ የነበረ ሲሆን በነገው ዕለት ከሌላኛው የመዲናው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ለማድረግ ቀጠሮ እንደያዘ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። በአሠልጣኝ ዝላትኮ ክራምፖቲች የሚመሩት ፈረሰኞቹም እንደ ኢትዮጵያ ቡና ቢሾፍቱ ላይ ዝግጅታቸውን እየሰሩ ሲሆን ባሳለፍነው ረቡዕ ከመከላከያ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ አከናውነው ነበር። ነገ ደግሞ ረፋድ አራት ሰዓት በይድነቃቸው አካዳሚ ከቡናማዎቹ ጋር ጨዋታ እንደሚያደርጉ ታውቋል።

የሚዲያ አካላት ጨዋታውን ለመከታተል እንደማይችሉ እና ዝግ መሆኑን ሰምተናል።