አራት ኢትዮጵያውያን ሴት ዳኞች የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎችን ይዳኛሉ

በኬንያ አስተናጋጅነት የፊታችን ቅዳሜ በሚጀምረው የሴካፋ ዞን የሴቶች የቻምፒየንስ ሊግ የቅደመ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ለመምራት አራት ኢትዮጵያዊያን ሴት ዳኞች ተመርጠዋል።

በግብፅ አዘጋጅነት ስምንት ክለቦች ይሳተፋሉ ተብሎ በሚጠበቀው እና በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚደረገው የካፍ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ላይ ለመሳተፍ በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ ክለቦች የቅድመ ማጣሪያ የዞን ጨዋታዎቻቸውን በኬንያ ከነሀሴ 22 ጀምሮ ማድረግ ይጀምራሉ፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ወደ ቻምፒዮንስ ሊጉ ለማለፍ የ2014 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮኑ ንግድ ባንክ ተካፋይ ሲሆን አሁን ደግሞ በዚህ ውድድር ላይ በዳኝነት ለማገልገል በካፍ አራት ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ተመርጠዋል፡፡

በዋና ዳኝነት አስናቀች ገብሬ እና መዳብ ወንድሙ በረዳት ዳኝነት ረዘም ያለ ልምድ ያላቸው ወይንሸት አበራ እና ይልፋሸዋ አየለ የተመረጡ ዳኞች ሲሆኑ በነገው ዕለት ረፋድ 5፡00 ላይ ወደ ኬንያ እንደሚያመሩ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል፡፡