“በዚህ አዲስ ውድድር ላይ ታሪክ ሰርቼ መመለስ እፈልጋለሁ” ሎዛ አበራ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አምበል እና አጥቂ ሎዛ አበራ ክለቧ ለአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የማጣሪያ ውድድር ያደረገውን ዝግጅት እና በውድድሩ ስላላት የግል እቅድ ለድረ-ገፃችን ሀሳቧን ሰጥታለች።

ስምንት ሀገራትን ተሳታፊ በሚያደርገው የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የአህጉሩ የሊግ አሸናፊ ክለቦች በስድስት ዞኖች የማጣሪያ ውድድር በየቀጠናቸው እንደሚያደርጉ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የማጣሪያ ጨዋታውን ለማድረግ በትናንትናው ዕለት ወደ ኬንያ አምርቷል። የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው በትናንትናው ዕለት ከዝግጅት ክፍል ጋር ያደረጉትን ቆይታ ያስነበብን ሲሆን አሁን ደግሞ የቡድኑ አምበል ሎዛ አበራ ስለ ውድድሩ፣ ስለ ዝግጅታቸው እና ስለ ግል እቅዷ ያወጋችንን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

ዝግጅት እንዴት ነበር?

ዝግጅታችን በጣም አሪፍ ነው። ከጀመርንበት ቀን አንስቶ በጥሩ ሁኔታ እየተዘጋጀን ነው ያለነው። አሠልጣኞቻችን የሚሰጡንን ነገር በአግባቡ እየተገበርን ነገ ለሚጀምረው ውድድር እየተዘጋጀን ነው። በአጠቃላይ ቡድኑ ውስጥ ያሉት ሁሉም ተጫዋቾች በጥሩ ተነሳሽነት እና ፍላጎት ነው ልምምዳቸውን ሲሰሩ የነበረው።

በስብስቡ ውስጥ የምትገኙት ሁላችሁም ተጫዋቾች ጨዋታ ካደረጋችሁ በርከት ያሉ ቀናት ተቆጥረዋል። ታዲያ ወደ ጨዋታ ሪትል ለመግባት አልተቸገራችሁም?

እንዳልከው ከውድድር ከራቅን ቆየት ይላል። እርግጥ አንዳንዶቻችን የብሔራዊ ቡድን ዝግጅት በመሐል መጥቶ ስለነበር በዛ ጊዜ በተደራጀ መልኩ ልምምድ ሰርተን ጨዋታ አድርገናል። ይህ ቢሆንም አሁን የተወሰነ ጊዜ አርፈን ነው የመጣነው። እንደተባለው ይህ ጉዳይ ችግር ሊያመጣብን ይችላል። ግን እኛ በምንችለው ልክ ያለንን አቅም አሰባስበን በቶሎ ወደ ጨዋታ ሪትም ለመምጣት እየተዘጋጀን ነው።

እንደ አምበል ለተጫዋቾቹ አንቺ ትቀርቢያልሽና ስብስቡ ውስጥ ያለው የቡድን መንፈስ ምን ይመስላል?

እውነት ለመናገር በጣም ነው ደስ የሚለው። ምክንያቱም ሁሉም ተጫዋቾች ውድድሩን በጉጉት ስለሚጠብቁት። እኔ እንደማየው እና እንደተገነዘብኩት አብዛኞቹ ተጫዋቾች ዋናውን የቻምፒየንስ ሊግ ውድድር በጣም ነው እየጠበቁት ያሉት። ከዛ በፊት ደግሞ ኬኒያ ላይ ያለውን የማጣሪያ ውድድር ማለፍ ይጠበቅብናል። በልምምድ ላይ የሰራናቸውን ነገሮችም ሜዳ ላይ ለማሳየት እኔን ጨምሮ ሁላችንም ተዘጋጅተናል። ስለዚህ ስብስቡ ውስጥ በጣም ትልቅ ጉጉት እና ዝግጁነት ነው ያለው።

ቡድናችሁ በኬንያው ውድድር እስከ ምን እርቀት መጓዝ ይችላል?

እኔ ማስበው በውድድሩ ላይ ከፍተኛ ውጤት እንደምናመጣ ነው። ምክንያቱም ሁላችንም አቅም ያለን ተጫዋቾች ስለሆንን። ከዚህ ውጪ እርስ በእርስ ያለን መግባባትም በጣም ጥሩ ነው። እንዳልኩት አሠልጣኞቻችን የሚሰጡንን እየተቀበልን እየተገበር ነው። ይህ ደግሞ ውድድሩ ላይ የተሻለ ውጤት እንድናመጣ ይረዳናል። በአጠቃላይ በውድድሩ ላይ በጣም የተሻለ እና ጥሩ ቡድን ሆነን ነው የምንቀርበው።

አንቺስ በግልሽ…?

እኔም በግሌ በውድድሩ ላይ ብዙ ጎሎችን እንደማገባ አስባለሁ። እንደምታውቀው ውድድሩ አዲስ ውድድር ነው። በዚህ አዲስ ውድድር ላይ ደግሞ ታሪክ ሰርቼ መመለስ እፈልጋለሁ። እንደገለፅኩት ይህ መንፈስ እኔ ጋር ብቻ ሳይሆን ሁሉም ተጫዋች ጋር አለ። ስለዚህ ክለቤ በውድድሩ የተሻለ ነገር እንዲያመጣ ከአጋሮቼ ጋር በመተባበር እንሰራለን።