“እግርኳስ ለሰላማችን” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጁትን ፕሮግራሞች አስመልክቶ መግለጫ ተሰጥቷል

👉”ያለን እግርኳስ ሀገርን ማዳን የማይችል ከሆነ ጥንቅር ብሎ ሊቀር ይችላል” ባህሩ ጥላሁን

👉 “አርቲስቶች እንዲያውቁ የምንፈልገው ነገር ከዋናው ጦርነት የምናመጣው ልምድ እንዳለ ነው” ኮሎኔል ደረጄ መንግስቱ

👉”ዋና ዓላማውም ለሀገር ህይወቱን ሰጥቶ እየተዋጋ ያለውን የመከላከያ ሠራዊት ለመደገፍ ነው” አርቲስት ቴዎድሮስ ፍቃዱ

👉”ለዚህ ትልቅ ዓላማ የኪነ ጥበብ ባለሙያው እንዲጋበዝ በመደረጉም ደስ ብሎናል” አርቲስር ሰለሞን ተካ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን፣ የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት እና የኢፌዴሪ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከዋቢ ኢቨንትስ ጋር በመሆን በአሁኑ ሰዓት ለሀገር ሠላም እየተዋደቀ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ለማድረግ የገቢ ማሰባሰቢያ እና የደም ልገሳ መርሐ-ግብር አዘጋጅተዋል። መስከረም 8 እና 10 የሚካሄዱት መርሐ-ግብሮች ላይ የሚከወኑ ተግባራትን በተመለከተ ደግሞ ዝግጅቱን ያሰናዱት አካላት ዛሬ ከሰዓት በቤስት ዌሰስት ፕላስ ሆቴል መግለጫ ሰጥተዋል። ይጀመራል ተብሎ ከተነገረው ሰዓት 60 ደቂቃዎችን ዘግይቶ የተጀመረውን ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የማርኬቲንግ ክፍል ኃላፊ አቶ ኢሳይያስ ታፈሠ፣ ኮሎኔል ደረጄ መንግስቱ፣ ሻለቃ አማረ አራጌ፣ አርቲስት ሰለሞን ተካ እና አርቲስት ቴዎድሮስ ፍቃዱ ሰጥተዋል። በቅድሚያም የዝግጅቱ አስተባባሪ አርቲስት ቴዎድሮስ በሁለቱ ቀናት የሚከወኑትን ተግባራት አብራርቷል።

“ይህ ዝግጅት እግርኳሳችን ለሠላማችን በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ መርሐ-ግብር ነው። ዋና ዓላማውም ለሀገር ህይወቱን ሰጥቶ እየተዋጋ ያለውን የመከላከያ ሠራዊት ለመደገፍ ነው። በዚህም በሁለት ቀናት የተዘጋጁ ዝግጅቶች አሉ። በቅድሚያ መስከረም 8 ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች (አርቲስቶች) ጋር አዝናኝ የእግርኳስ ጨዋታ ያደርጋሉ። ከዚህ የእግርኳስ ጨዋታ በኋላ ደግሞ በሴት የመንግስት ኃላፊዊች (ሚኒስትሮች) እና አርቲስቶች መካከል የገመድ ጉተታ ውድድር ይኖራል። በስታዲየሙ ውድድሮቹ እየተከናወኑ የደም ልገሳ ፕሮግራም ጎን ለጎን ይካሄዳል።

“ከሁለት ቀን በኋላ መስከረም 10 ላይ ደግሞ በስካይ ላይት ሆቴል ከ11 ሰዓት ጀምሮ ታላላቅ የሀገራችን ባለ ሀብቶች በተገኙበት የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ይካሄዳል። በዕለቱም የተለያዩ ፎቶ ግራፎች፣ ስዕሎች (ተስለው የሚመጡም ሆነ እዛው መድረክ ላይ የሚሳሉ) በጨረታ መልክ ቀርበው የቴሎቶን ድጋፍ እንዲደረግ ይሆናል።” በማለት ዝግጅቶቹ አብራርቷል።

ከአርቲስት ቴዎድሮስ መድረኩን በቀጣይነት የተረከቡት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ተቋማቸው ለዝግጅቱ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አውስተው ሀገር ሰላም ካልሆነች እግርኳስም እንደማይኖር ይህንን ተከትሎ ለሀገር ሰላም የበኩላቸውን ለማድረግ እንደተነሱ አጽዕኖት ሰትተው ተናግረዋል።

“እግርኳስ ፌዴሬሽናችን ይህንን ዝግጅት በመሪነት እየሰራ ነው የሚገኘው። ዝግጅቱ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወንም 2.2 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ለመከላከያ ሰራዊቱ የሚደረገውን ድጋፍ ለማዘጋጀት እና ከሰራዊቱ ጎን መሆኑን ለማሳየት ቁርጠኝነቱን አሳይቷል። ሀገር ስትኖር እና እንደ ሀገር አንድ ስንሆን ነው እግርኳስ መካሄድ የሚችለው። ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ዋቢ ኢቨንትስ ያቀረበውን ፕሮፖዛል በማፀደቅ ነው ወደ እንቅስቃሴ ከአንድ ወር በፊት የገባው።

“እንደምታውቁት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከመከላከያ ጎን መሆኑን ሲያሳይ አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ከዚህ ቀደም በግዳጅ ወቅት ህይወታቸው ላለፈ የሰራዊቱ አባላት በክልል ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር ላይ የህሊና ፀሎት አድርገን ሰራዊቱን አስበናል። ይህ በቂ ስላልሆነ ደግሞ ደም ለመለገስ እና ገንዘብ ለማሰባሰብ በማሰብ ነው ወደዚህኛው እንቅስቃሴ የገባነው።

“እግርኳስ ፌዴሬሽኑ ወደዚህ አይነት ነገር ለምን ገባ ተብሎ አይጠየቅም። ሀገር ስትፈርስ ቆሞ የሚያይ ማንም የለም። ያለን እግርኳስ ሀገርን ማዳን የማይችል ከሆነ ጥንቅር ብሎ ሊቀር ይችላል። ፌዴሬሽናችን ሀገርን ለማዳን በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ አሁን እየተሳተፈ እንገኛል። ወደፊትም እየተሳተፈ ይቀጥላል።” ብለዋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊትን ወክለው በስፍራው የተገኙት ኮሎኔል ደረጄ መንግስቱ በበኩላቸው “የሀገር ጉዳይ የሁሉም ጉዳይ ነው። ሀገር ሰላም ሲሆን ነው ሁሉም ነገር መሆን የሚችለው። ስፖርቱም የሚቀጥለው ሀገር ሰላም ሲሆን ነው። ህዝቡም እንደ ህዝብ ተቋማትም እንደ ተቋም ለሰራዊቱ የተቻላቸውን እያደረጉ ነው። አሁንም ለሰራዊቱ ለሚደረገው ነገር በጣም ነው የምናመሰግነው።” ብለዋል። ኮሎኔሉ አክለውም ከአርቲስቶች ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ በተመለከተ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

“እግርኳስ የሰላም ውጊያ ነው። ዋናው ጦርነት ደግሞ ህይወትን የሚቀጥፍ ነው። ከአርቲስቶች ጋር የምናደርገው ጨዋታ ላይ ጠንክሮ ለመቅረብ ዝግጅት እያደረግን ነው። ስለዚህ አርቲስቶች እንዲያውቁ የምንፈልገው ነገር ከዋናው ጦርነት የምናመጣው ልምድ እንዳለ ነው። መከላከልም ሆነ ማጥቃት እንችላለን። ግጥሚያው ኳስ ቢሆንም እኛ መሸነፍ ስለማንወድ እናሸንፋለን።”

በማስከተል ንግግር ያደረጉት አርቲስት ሠለሞን ተካ በበኩላቸው “አሁን እዚህ ያሰባሰበን ጉዳይ የሰላም ጉዳይ ነው። እኛ የኪነ ጥበብ ሰዎችም ሰላማችን ካልተረጋገጠ ምንም ስራ አንሰራም። ለዚህም ነው ሰላማችንን የሚሰጠንን የመከላካያ ሰራዊታችን ለማገዝ የተነሳነው። ለዚህ ትልቅ ዓላማ የኪነ ጥበብ ባለሙያው እንዲጋበዝ በመደረጉም ደስ ብሎናል። እኔም በመሳተፌ በጣም እድለኛ ነኝ። ይሄንን ሁሉ ዓመት የኖርኩት መከላከያ ሰራዊት ለእኔ ብዙ ስለለፋ ነው።” በማለት ከተናገሩ በኋላ ከመከላከያ ጋር ለሚደረገው አዝናኝ ጨዋታ ይህንን ብለዋል።

“በውድድሩ እኛ እንደምናሸንፍ እርግጠኛ ነኝ። እነሱ የሚያምርባቸው መሳሪያውን ሲይዙ ነው። እኛ ደግሞ ኳሱን ስንይዝ ያምርብናል። ስለዚህ መከላከያዎች በሜዳ ላይ ለሚገጥማቸው ነገር ይዘጋጁ። መታወቅ ያለበት ነገር ግን መከላከያን በሙያም ማሸነፍ አንችልም።”

መስከረም 8 በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚካሄደውን አዝናኝ ዝግጅት ለመከታተልም የስፖርት ቤተሰቡ እና አጠቃላይ ሰራዊቱን መደገፍ የሚፈልግ ግለሰብ የተዘጋጁትን 15 ሺ
የባለ 100፣ 500 እና 1000 ብር ትኬቶች በኢትዮጵያ እግርኳስ ደጋፊዎች ማኅበር በኩል እንዲገዛ ጥሪ ተላልፏል።

ያጋሩ