የዛሬው የኢትዮጵያ እና ዚምባቡዌ ጨዋታ ለምን የቀጥታ ስርጭት አላገኘም?

ዛሬ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የኢትዮጵያ እና ዚምባቡዌ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ በፊፋ የዩቲዩብ ቻናል ያልተላለፈበት ምክንያት ምን ይሆን ስንል ጠይቀናል።

ኳታር ለምታስተናግደው የ2022 ዓለም ዋንጫ ለማለፍ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ብሔራዊ ቡድኖች የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታቸውን በያሉበት አህጉር እያከናወኑ እንደሆነ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በምድብ ሰባት ከጋና፣ ዚምባቡዌ እና ደቡብ አፍሪካ ጋር ተደልድሎ ጨዋታዎችን እያደረገ ይገኛል። ብሔራዊ ቡድኑ በዛሬው ዕለት የዚምባቡዌ አቻውን በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም አስተናግዶ አንድ ለምንም አሸንፏል።

ጨዋታው ለደጋፊዎች ክፍት አለመሆኑን ተከትሎ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት እንደሚተላለፍ የሚጠይቁ የስፖርት ቤተሰቦች በፊፋ የዩቱብ ቻነል ጨዋታውን እንዲያዩ ቀድሞ ቢገለፅም እንደታሰበው እና እንደታቀደው ጨዋታው በተባለው አማራጭ የቀጥታ ሽፋን ሳያገኝ ቀርቷል። ይህ ለምን ሆነ ብላ የጠየቀችው ሶከር ኢትዮጵያም ተከታዩን ምላሽ ከሚመለከታቸው አካላት አግኝታለች።

ጨዋታውን የማስተላለፍ መብት ያለው ፊፋ እንደ ሌሎቹ የአህጉሪቱ ጨዋታዎች የዛሬውንም ፍልሚያ ለማስተላለፍ በትናንትናው ዕለት ባህር ዳር ገብቶ ነበር። ከአስር በላይ ባለሙያዎችን እና ለቀጥታ ስርጭት የሚሆኑ የካሜራ መሳሪያዎችን ይዞ ባህር ዳር የደረሰው የፊፋ ልዑክም ጨዋታው እየተቀረፀ በቀጥታ ምስሉ ወደ አውሮፓ የማሰራጫ ማዕከል እንዲደርስ የሚያደርገውን የሳተላይት መሳሪያ በክልሉ ከሚገኘው የቴሌቪዥን ተቋም (አማራ ቲቪ) ለመውሰድ እና በጋራ ለመስራት ንግግር ላይ ነበር። ድረ-ገፃችን ባህር ዳር ከሚገኙ የፊፋ ባለሙያዎች ጠይቃ እንደተረዳችውም በጋራ ለመስራት የተስማማው የቴሌቪዥን ጣቢያው እስከ ትናንት ድረስ ውሳኔ አስተላልፎ መሳሪያውን ባለመስጠቱ መንጓተቶች እንደተፈጠሩ ተጠቁሟል።

በጋራ የመስራት ስምምነት ሊገኝ የነበረው ሳተላይት በትናንትናው ዕለት ደርሶ የሙከራ ስርጭት መፈፀም ቢገባም መሳሪያው በዛሬው ዕለት በቦታው መገኘቱን ተከትሎ ከጨዋታው በፊት ሙከራ ሳይደረግ ቀርቷል። በዛሬው ዕለት ግን የአማራ ቴሌቭዢን ሳተላይቱን በመልቀቁ ጨዋታው የሚተላለፍበት ዕድል ዳግም ተስፋ አግኝቶ ነበር። ነገርግን መሳሪያው ባለቀ ሰዓት መድረሱን ተከትሎ ሙከራ ሳይደረግ የጨዋታው መጀመሪያ ሰዓት ደርሷል። ጨዋታው ሊጀመር ሲል ከስታዲየሙ ወደ አውሮፓ የፊፋ ሚዲያ መድረስ የነበረበት የምስል ሲግናልም በስታዲየሙ ያለው እና ዙሪክ (ዋና ማሰራጫ) ያለው ሳተላይቶች ባለመጣጣማቸው ምክንያት ጨዋታው ሳይተላለፍ ቀርቷል።

ምንም እንኳን ፊፋ ጨዋታውን በቀጥታ ባያሰራጨውም ሙሉ ምስሉን በዩቱብ ቻናሉ እንደሚለቅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።