የሴንትራል ሀዋሳ ዋንጫ ፍፃሜውን አገኘ

በሁለት የዕድሜ እርከኖች በአርባ አምስት ቡድኖች መካከል ለሀያ አራት ቀናት ሲደረግ የነበረው የሴንትራል ሀዋሳ ዋንጫ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

በየዓመቱ በሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል አስተናጋጅነት የሚደረገው የሴንትራል የታዳጊዎች ዋንጫ ውድድር ዘንድሮ በአርባ አምስት ቡድኖች መካከል ከነሀሴ 10 ጀምሮ ለተከታታይ 24 ቀናት በሀዋሳ ቄራ ሜዳ ሲደረግ ሰንብቶ ፍፃሜውን በሁለት መርሀግብሮች አግኝቷል፡፡

እጅግ ደማቅ በነበረው የመዝጊያ ጨዋታዎች ላይ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬን ጨምሮ የሲዳማ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍሬው አሬራ ፣ የደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ የሺዋስ አለሙ ፣ ወ/ሮ ደርጊቱ የሀዋሳ ከተማ ባህል ቱሪዝም እና ስፖርት ሀላፊ የከተማው የስፖርት ኮሚሽነር አቶ ጥላሁን ሀሜሶ እንዲሁም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት እና የሴንትራል ሀዋሳ ሆቴል ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ፍትህ ወልደሰንበት እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ሁለቱም ጨዋታዎች ተከናውነዋል፡፡

አስራ ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረው እና በርካታ ስመጥር ስፖርተኞችን ያፈራው ይህ የታዳጊዎች ውድድር ያለፉትን ሁለት አመታት በተለያዩ ምክንያቶች ሳይደረግ ቆይቶ ዘንድሮ በድጋሚ ተካሂዶ ተጠናቋል፡፡ 32 ቡድኖችን ባቀፈው ከ15 አመት በታች ውድድር በፍፃሜው ትናንት ረፋድ ላይ ፍፁም አልሙኒየም እና ኤሉ ቪዲዮ ሴንተር ተገናኝተው ፍፁም አልሙኒየም 1ለ0 በማሸነፍ የዋንጫ ባለ ድል መሆኑን ሲያረጋግጥ 13 ቡድኖችን አቅፎ ሲደረግ የነበረው ከ13 አመት በታች ውድድር መታፈሪያ ስፖርት ለሁሉም ሀይቅ ዳር ቃለ ህይወትን 1ለ0 በማሸነፍ የዚህን የዕድሜ እርከን ዋንጫን ከፍ በማድረግ አንስቷል፡፡

ከፍፃሜ ጨዋታዎቹ በመቀጠል በሁለቱም የዕድሜ እርከኖች በኮከብ ተጫዋችት ፣ በከፍተኛ ግብ አግቢነት ፣ በምርጥ ግብ ጠባቂነት እና በምርጥ አሰልጣኝነት ለተመረጡ እና ለውድድሩ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የተዘጋጁ የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክተዋል፡፡በክብር እንግድነት በመዝጊያው መርሀግብር ላይ የተገኙት የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ በውድድሩ ላይ ተሳትፈው ሻምፒዮን መሆን ለቻሉት ቡድኖች እንኳን ደስ አላችሁ በማለት በመግቢያ ንግግራቸው የገለፁ ሲሆን ውድድሩ የሚደረግበትን የቄራ ሜዳ በርካታ ስፖርተኞችን ያፈራ በመሆኑ ሜዳውን በሁለት ወራት ውስጥ ወሰኑ ተከብሮ ምቹ እንዲሆን ለማድረግ ከተማ አስተዳደሩ ማቀዱን ገልፀው በዛሬው የፍፃሜ ጨዋታ ላይ ለተወዳዳሩ አራቱን ክለቦች ሙሉ ትጥቆች እና ውድድሩን ለዳኙ እና ቡድኖችን ይዘው ላሰለጠኑ አሰልጣኞች ምቹ ስልጠናዎችን እንደሚያመቻቹ ከንቲባው በንግግራቸው ጠቁመዋል፡፡ የደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽነር ለተሳታፊ ቡድኖች የኳስ ስጦታን ያበረከቱ ሲሆን የሴንትራል ሀዋሳ ሆቴል ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ፍትህ ወልደሰንበት በበኩላቸው ይህ ውድድር በየአመቱ መደረጉ ለከተማው ፣ ለክልሉ እና አልፎም ለሀገር የሚበጁ ስፖርተኞችን የሚያበቃ በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀው ለውድድሩ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋናን አቅርበዋል፡፡

በውድድሩ ላይ በኮከብነት ለተመረጡ ስፖርተኞች የሻሎም ቢዝነስ እና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ እንዲሁም የኢንፎሊንክ ኮሌጅ በኮሌጃቸው የስኮላርሺፕ የዲፕሎማ እና ዲግሪ ትምህርት በነፃ እንዲያገኙ እድልንም ጭምር አመቻችቷል። በስፍራው የተገኙ የተለያዩ አካላትም ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ለሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል እና ለሆቴሉ ባለቤት ወ/ሮ አማረች ታላቅ ምስጋናን አቅርበዋል፡፡