አዲስ አበባ ከተማ ከከፍተኛ ሊጉ ስድስት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

ዛሬ ረፋድ አምስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ከፕሪምየር ሊጉ ወደ ስብስቡ የቀላቀለው አዲስ አበባ ከተማ አሁን ደግሞ ተጨማሪ ስድስት ተጫዋቾችን ከከፍተኛ ሊጉ አስፈርሟል፡፡

የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቹ ቢኒያም ጌታቸው አዲሱ የክለቡ ፈራሚ ተጫዋች ሆኗል፡፡ እግር ኳስን በሀምበሪቾ ዱራሜ የጀመረው ይህ የፊት መስመር ተጫዋች ወደ ስልጤ ወራቤ እና አክሱም ከተማ በማምራት ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን 2012 በድጋሚ ወደ ሀምበርቾ ዱራሜ ተመልሶ ቆይታን ማድረግ ችሏል፡፡ በከፍተኛ ሊጉ በተደጋጋሚ በግብ አስቆጣሪ ዝርዝር ውስጥ የማይጠፋው ይህ ተጫዋች በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ 12 ጎሎችን ማስቆጠሩም የሚታወስ ሲሆን ለቀጣዩ የ2014 የውድድር ዓመት አዲስ አዳጊው አዲስ አበባ ከተማን በአንድ ዓመት ውል መቀላቀል ችሏል፡፡

ፈጣኑ አጥቂ ፃዲቅ ተማም ሌላኛው አዲስ አበባ ከተማን የተቀላቀለ አዲሱ ፈራሚ ሆኗል፡፡ የቀድሞው የለገጣፎ እና የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጫዋች የተጠናቀቀውን የውድድር አመት በከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ስር በተወዳደረው ለገጣፎ ተመልሶ በመጫወት ያሳለፈ ሲሆን አሁን ደግሞ ወደ ፕሪምየር ሊጉ አዲሱ ተካፋይ አዲስ አበባ ከተማ ተዘዋውሯል፡፡

የመሐል ተከላካዩ ልመንህ ታደሰ ካፋ ቡናን ከለቀቀ በኋላ ረዘሞ ያሉ ዓመታትን በሀላባ ከተማ በመጫወት ያሳለፈ ሲሆን በርበሬዎቹን በመልቀቅ አሁን ደግሞ ወደ አዲስ የፕሪምየር ሊጉ አዳጊው ክለብ አዲስ አበባ ከተማ አምርቷል፡፡

ሙሉቀን አዲሱ ሌላኛው አዲሱ የክለቡ ፈራሚ ሆኗል፡፡ ይህ የቀድሞው የነቀምት ከተማ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት በገላን ከተማ ጥሩ ጊዜን ካሳለፈ በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ክለብ አዲስ አበባ ከተማ አምርቷል፡፡

አዲስ አበባ በተጨማሪም የቀድሞው የሀላባ ከተማ የግራ መስመር ተከላካዩ ቴዎድሮስ ሀሙን ከነቀምት ከተማ፣ የመሀል አማካዩ ብሩክ ግርማን ከአርሲ ነገሌ በአንድ ዓመት ውል ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል፡፡