የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ውድድር ዘንድሮ ይካሄዳል

በየዓመቱ የሚደረገው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር የጎረቤት ሀገር ተጋባዥ ክለቦችን በማካተት እንደሚደረግ ይጠበቃል።

በአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የሊግ ውድድሮች ከመጀመራቸው በፊት በየዓመቱ የሚከናወነው የመዲናው የዋንጫ ውድድር ዘንድሮም በአይነቱ ለየት ባለ ሁኔታ እንደሚከናወን ታውቋል። ከመስከረም 15 እስከ 30 ድረስ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደሚደረግ የተገለፀው ውድድሩም በስምንት ክለቦች መካከል እንደሚከናወን ሰምተናል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚሳተፉ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ አዲስ አበባ ከተማ፣ መከላከያ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ አዳማ ከተማ እና ባህር ዳር ከተማ በዚህ ውድድር ላይ እንዲካፈሉ የቀረበላቸውን ጥያቄ መቀበላቸው ሲታወቅ ሁለት ተጋባዥ ክለቦችንም ከጎረቤት ሀገር ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳን ለማምጣት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መኮኑን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። ሙኑኪ ኤፍ ሲ የተባለው የደቡብ ሱዳኑ ክለብ በውድድሩ መሳተፉን ማረጋገጫ እንደሰጠ ሲገለፅልን የኤርትራው ክለብ ግን ዛሬ አልያም ነገ የመጨረሻ ምላሹን እንደሚሰጥ ተረድተናል።

በውድድሩ የሚሳተፉት ክለቦች ከነገ በስትያ ረፋድ 4 ሰዓት በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተገኝተው የደንብ ውይይት የሚያደርጉ ሲሆን በማግስቱ ዓርብ ደግሞ ቦሌ አካባቢ በሚገኘው ቤስት ዌስት ፕላስ ሆቴል ውድድሩን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ተመላክቷል።