ለሉሲዎቹ ድጋፍ ተደረገላቸው

ለኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የስፖርት ብራ (ቦዲ ኬር) ድጋፍ በአቶ ዳዊት ጌታቸው እንደተደረገ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በጨዋታ ጊዜ በሚከሰት ግጭት በጡት ላይ የሚገጥም አደጋን ለመከላከል የሚረዳ የጡት መከላከያን በቦስተኔ ነዋሪ በሆኑት አቶ ዳዊት ጌታቸው አማካኝነት በፌዴሬሽኑ አዳራሽ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ አቶ ባሕሩ ጥላሁን፣ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው እና የሉሲዎቹ አምበል ሎዛ አበራ በተገኙበት መበርከቱንም ፌዴሬሽኑ ባሰራጨው መረጃ ገልጿል።

አቶ ዳዊት በዕለቱ በሰጡት አስተያየት “ይህ የስፖርት ብራ /ቦዲ ኬር/ ስጦታ የተለያየ መጠን ያለው ለ30 የቡድን አባላት አገልግሎት የሚውል ሲሆን ለሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከጉዳት መከላከያ እና በጨዋታ ጊዜ በራስ መተማመን እንዲኖራቸው የሚረዳ ነው፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን ያስመዘገበው ውጤት ለብሔራዊ ቡድን ልጆቻችን የሞራል ስንቅ የሚሆን ነው፡፡ ሎዛ አበራ ወደ ሀገሯ ተመልሳ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር መቀላቀሏ ትልቅ ነገር አስገኝቷል፤ ለዚህም የበኩሌን ጥረት አድርጌለሁ፡፡ ይህንን መሰል ስጦታ ከዛሬ 8 ዓመታት በፊት ለብሔራዊ ቡድኑ ድጋፍ በማድረግ ቢያንስ በሁለት ዓመት አንድ ጊዜ ለመደገፍ ጥረት እያደረኩ ነው ፤ ይህ ለአራተኛ ጊዜ ያደረኩት ሲሆን ወደፊትም በደስታ ቡድኑን ለመደገፍ ጥረት አደርጋለሁ። የሴቶች ብሔራዊ ቡድናችንም በዘንድሮ ዓመት ጥሩ ውጤት እንደሚያስመዘግብ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ። “ በማለት ሃሳባቸውን ገልፀዋል፡፡   

የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ አቶ ባሕሩ ጥላሁን በበኩላቸው “ ይህንን መሰል የስፖርት ድጋፎች ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በጣም አስፈላጊ ናቸው፡፡ ብሔራዊ ቡድናችን የሚገነባው በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጥረት ብቻ ሳይሆን እንደዚህ ዓይነት እድሎችን በማመቻቸት ነው። ሌሎችም ባለሃብቶች እኛ ማግኘት የማንችላቸውን እነሱ ግን ለማግኘት ቀላል የሆኑ በርካታ ነገሮች ይኖሩዋቸዋል፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ቡድኑን ከመደገፍ አንፃር መሰል ድጋፎችን በዚህ አጋጣሚ ለብሔራዊ ቡድኖቻችን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ እኛም በራችንን ክፍት በማድረግ እንጠብቃለን።” ሲሉ መልዕክታቸውን ከምስጋና ጋር አስተላልፈዋል፡፡  

የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው በበኩሉ “አቶ ዳዊት ይህ አይነቱ ቁስ ለሴቶች ብሔራዊ ቡድን ያስፈልጋል በሚል በተደጋጋሚ በግሉ አስቦ ድጋፍ በማድረጉ ከልብ እያመሰገንኩ ሀገራችን ላይ ያሉ በርካታ ባለሃብቶች እንዲሁ ድጋፍ ቢያደርጉ ተጫዋቾቻችን ከክለብ እና ከፌዴሬሽን ውጭ ሌሎች ደጋፊዎች ይኖራሉ። ይህ ጥሩ መነሳሳት የሚፈጥር ነገር ነው።” በማለት አቶ ዳዊትን አመስግነዋል፡፡

በመጨረሻም የሉሲዎቹ አምበል ሎዛ አበራ “ አቶ ዳዊት ከዚህ በፊትም ድጋፍ አድርገውልናል፡፡ ይህ ደግሞ እንዲህ አይነት ሰዎች ከጎናችን በመኖራቸው ለቡድኑ ጥሩ መነቃቃት ይፈጥራል ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ አይነቱ ሥጦታ ሴቶች እንደመሆናችን መጠን በጣም አስፈላጊያችን ነው፡፡ ይህንን ለብሶ መጫወቱ ጥሩ በራስ መተመመን ይፈጥርልናል ፡፡ ስለዚህ በጣም እናመሰግናለን ፡፡ ወደፊትም አቶ ዳዊት ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች አካላትም ሉሲዎቹን በተቻላቸው አቅም እንዲደግፋ ጥሪዬን አቀርባለሁ።“ ብላለች።